ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ
የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፀጋይ ብርሃነ እና ምክትላቸው አቶ ገብረአምላክ የዕብዮ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ምክትል ፕሬዝዳንቱ እና የፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሁለቱ አመራሮች ከኃላፊነት ለመልቀቅ የወሰኑት፤ በአመራርነት ጊዜያቸው “የጀመሩትን የለውጥ አቅጣጫ ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ” ባለማግኘታቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።
ላለፉት ዘጠኝ ወራት የክልሉን ፍርድ ቤቶች ሲመሩ የነበሩት ሁለቱ ኃላፊዎች፤ ከሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት ሰኞ ሰኔ 17/2016 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ እንደሆነ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ገብረአምላክ ለቢቢሲ ገልጸዋል። አመራሮቹ ጥያቄያቸውን ያቀረቡበት ደብዳቤ የተጻፈው ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ነው።
የዶ/ር ፀጋይ እና አቶ ገብረአምላክ ፊርማ ያረፈበት ይህ ደብዳቤ፤ ሁለቱ አመራሮች የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለመምራት ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ የተሰጣቸውን “ሕዝባዊ እና መንግሥታዊ ኃላፊነት አቅም እና ሙያቸው በፈቀደው ሁሉ” ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ያስረዳል።
አመራሮቹ፤ “በከባድ የህልውና አደጋ ውስጥ ወድቆ የነበረው ሕዝባችንን እና የዳኝነት ሥርዓትን ለማቃናት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል” ሲሉም በኃላፊነት በቆዩበት ዘጠኝ ወራት ያደረጉትን ጥረት ጠቅሰዋል።
የክልሉን ፍርድ ቤቶች “ጥሩ ባልሆነ ቁመና” በነበሩበት ጊዜ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በደብዳቤያቸው ያስታወሱት አመራሮቹ፤ “አጭር” በሆነው የኃላፊነት ጊዜያቸው የፍርድ ቤቶችን ቁመና ለማሻሻል መሥራታቸውን ገልጸዋል።
በአመራርነት ቆይታቸው “ለፍርድ ቤቶች ውጤታማ አስተዳደር እና አገልግሎት አሰጣጥ ይጠቅማሉ” ያሏቸውን እርምጃዎች ሲወስዱ እና ማሻሻያ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በደብዳቤው አስረድተዋል።
ሁለቱ አመራሮች፤ “ይሁን እንጂ የተሰጠንን ከባድ ኃላፊነት እና ተልዕኮ አንግበን በአመራርነት ለመቀጠል እና የጀመርነውን የለውጥ አቅጣጫ ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ ማግኘት አልቻልንም” ሲሉ ከኃላፊነት ለመልቀቅ መወሰናቸውን አሳውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ እና ምክትላቸው ከኃላፊነት ለመልቀቅ የወሰኑት “በአጠቃላይ የፍትህ እና ዳኝነት አስተዳደር ሥርዓት ላይ ያሉ [እና] መሻገር ያልቻልናቸውን ተግዳሮቶች እና ማነቆዎች ለማስተካከል በሌላ መንገድ ለማገዝ እንደምንችል በመተማመን” እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አመራሮቹ ከኃላፊነት እንዲለቁ ያደረጋቸው አመቺ ያልሆነ ሁኔታ ምን እንደሆነ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ገብረአምላክ፤ ዝርዝር ጉዳዮችን ከማውራት እንደሚቆጠቡ ገልጸዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ በደብዳቤው ላይ የተጠቀሰውን ሀሳብ የሚያብራሩት ያቀረቡት የመልቀቂያ ጥያቄ “እልባት ካገኘ በኋላ” እንደሆነ አስረድተዋል።
ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የቀረበው ጥያቄ ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ በሥራ ላይ መሆናቸውን ምክል ፕሬዝዳንቱ አክለዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፀጋይም በተመሳሳይ ሥራ ላይ እንደሆኑ የፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መለስ አሸብር ለቢቢሲ ተናግረዋል።