በሳዑዲ አረቢያ የስደተኛ ሠራተኞች ሞት መጠን 'መጨመሩን' የሰብአዊ መብት ቡድኖች አሳሰቡ

ሳዑዲ አረቢያ የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ በምትደርገው ዝግጅት ወቅት በሚካሄዱ የግንባታ ሥራዎች ውስጥ የሚሳተፉ ስደተኛ ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው የሞት አደጋ "እንደሚያሻቅብ" የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አስጠነቀቁ።

በሳዑዲ ያለውን የውጭ አገር ሠራተኞችን ደኅንነት በተመለከተ ሪፖርት ያወጡት ሂማን ራይትስ ዋች እና ፌይርስኩዌር የተባሉት የመብት ቶቀርቋሪ ቡድኖች፤ ገና ካሁኑ መከላከል በሚቻሉ የሥራ ቦታ አደጋዎች የጉልበት ሠራተኞች እየሞቱ ነው።

ነገር ግን አብዛኞቹ ሞቶች የተከሰቱት በተፈጥሯዊ ምክንያት እንደሆኑ ተደርገው ስለሚመዘገቡ የሟች ሠራተኞች ቤተሰቦች ተገቢውን ካሳ እንዳያገኙ እንደሚደረግ ሪፖርቱ አመልክቷል።

"በ2034 የሚካሄደው የሳዑዲው የዓለም ዋንጫ ትልቁ እና ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበት ሲሆን፣ በግንባታ ላይ የሚሰማሩ ሠራተኞች ሕይወትን የሚያስከፍል ይሆናል" ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዋች ባለሥልጣኑ ሚነኪ ዎርደን ተናግረዋል።

ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ለሚካሄደው ዓለም አቀፉ ዋነኛ የእግር ኳስ ውድድር ዝግጅት ሳዑዲ አረቢያ 11 አዳዲስ ስታዲየሞችን፣ የባቡር እና ሌሎች የትራንስፖርት መስመሮችን እና 185 ሺህ የሆቴል ክፍሎችን ጨምሮ ለሌሎችም መሠረተ ልማቶች ግንባታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከውጭ አገራት የመጡ ሠራተኞች ይሰማራሉ።

ይህ የሰብአዊ መብት ቡድኖቹ ማስጠንቀቂያ የወጣው የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያን ኢንፋንቲኖ በአሜሪካ እና በሳዑዲ የኢንቨስትመንት መድረክ ላይ ከተገኙት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር አገሪቱን ከጎበኙ በኋላ ነው።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ስፖርት የበላይ አካል ፊፋ "በሥራዎቹ ውስጥ ሁሉ ለሰብአዊ መብት ጥበቃ እና መስፋፋት በማያወላውል ሁኔታ ቁርጠኛ" መሆኑን አስታውቋል።

ነገር ግን ሂዩማን ራይትስ ዋች በ2022 ከተካሄደው የኳታር የዓለም ዋንጫ ውድድር በፊት ከተከሰቱት የስደተኛ ሠራተኞች ሞቶች ፊፋ ምንም ዓይነት ትምህርት አልወሰደም ሲል ከስሷል።

የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች ለመንቀሳቀስ በማይችሉባት እና የሠራተኛ ማኅበራት በታገዱባት አገር ውስጥ የውጭ አገር ሠራተኞች ሞትን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አዳጋች ነው።

ነገር ግን ሂዩማን ራይትስ ዋች ከፎቅ ላይ የወደቁ፣ በከባድ ማሽኖች የተጨፈለቁ ወይም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እና በኤሌክትሪክ አደጋ የተጎዱ ሠራተኞች ቤተሰቦችን ከባንግላዴሽ፣ ከሕንድ እና ከኔፓል አነጋግሯል።

በአውሮፓውያኑ 2034 ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ዝግጅት የሚካሄዱ የግንባታ ሥራዎች በተጧጧፉበት በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ያለው የሙቀት መጠን ሌላኛው አሳሳቢ ነገር ነው።

የሳዑዲ መንግሥት በግንባታ ቦታዎች የሚደርሱ አደጋዎች ቀንሰዋል ቢልም የዓለም የግባታ ሠራተኞች ማኅበር እንዳለው ለመከላከል የሚቻሉ አደጋዎች "በአሳሳቢ ሁኔታ" መጨመራቸውን አመልክቷል።

ፊፋ ለሂዩማን ራይትስ ዋች በሰጠው ምላሽ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ከዓለም ዋንጫ ዝግጅት ጋር በተያያዘ የግንባታ ሥራዎች ላይ አስገዳጅ የደኅንነት ጥበቃ ሥርዓት በመዘርጋት ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ ለማመቻቸት ማቀዱን አስታውቋል።

ነገር ግን ፊፋ እነዚህ የሠራተኞችን የሥራ ላይ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ያስችላሉ ያላቸውን መመሪያዎች እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ዝርዝሩን ሳይገልጽ ቀርቷል።

ቢቢሲ ከሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድኖቹ በኩል የቀረበውን ስጋት በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።