ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የባሕረ ሰላጤው አገራትን በቀዳሚነት እንዲጎበኙ ያደረጋቸው ምክንያት ምንድን ነው?
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የውጭ አገር ጉዞውን ሲመርጥ እጅግ ጠቃሚ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የውጭ ፖሊሲው በምን አቅጣጫ የተቃኘ መሆኑን አመላካች ጭምር ነው።
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በአውሮፓውያኑ ግንቦት ወር 2017 ከቀደምት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ልምድ ያፈነገጠ የጉብኝት ሂደትን ተከትለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በሥልጣን ዘመናቸው ቅድሚያ ሰጥተው የሚጎበኙት ካናዳን፣ ሜክሲኮ እና አውሮፓን ነው።
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ለጉብኝት ቅድሚያ የሰጡት ግን በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችውን ሳዑዲ አረቢያን ነበር።
በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸውም ከዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 5 እስከ 8/2017 ዓ.ም. ድረስ የባሕረ ሰላጤው አገራትን መጎብኘትን መርጠዋል።
በዚህ ጉብኝታቸው ሳዑዲ አረቢያን፣ ኳታርን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን የሚጎበኙት ትራምፕ፤ ይህም የሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ይሆናል።
በእርግጥ ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምነት የሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ቀብር ላይ ለመገኘት ቫቲካን ተገኝተው ነበር።
ትራምፕ ዳግም የባሕረ ሰላጤው አገራትን አስቀድመው መጎብኘት የፈለጉበት ምክንያት ምን እንደሚያስቡ ፍንጭን ይሰጠናል።
በባሕረ ሰላጤ ጉዳዮች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው የሚመራመሩት ፕሮፌሰር አብዱላህ ባቦድ እንደሚሉት፣ ትራምፕ ከባሕረ ሰላጤው መሪዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመሥረት ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚያስገኝ ይገነዘባሉ።
አክለውም ይህም በአካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ እንዳለው እና ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን ወደ አሜሪካ በማምጣት ረገድ እምቅ አቅም እንደሆነ ስለሚረዱ ነው ብለዋል።
ትልልቅ ጉዳዮች
የመጀመሪያ ዕቅዳቸውን በመጋቢት ወር ይፋ ያደረጉት ትራምፕ ከባለጸጋ የአረብ አገራት ጋር የሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ ስምምነቶችን መፈጸም ቀዳሚ ጉዳያቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ውሳኔው የተደረሰው "በመቶ ቢሊየን የሚቆጠር ዶላር" ቃል ከተገባላቸው "ለሳዑዲ አረቢያ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ አገራት የጦር መሣሪያዎችን ከሚያመርቱ የአሜሪካ ኩባንያዎች" ጋር ስምምነት ከተደረገ በኋላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
"የባሕረ ሰላጤው አገራት ባላቸው የገንዘብ ክምችት፣ የሀብት ክምችት እና ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም በዓለም ምጣኔ ሀብት ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ" ብለዋል ፕሮፌሰር ባቦድ።
በአገር ውስጥ ካለው ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች አንፃር ትራምፕ ከባለጸጋ የባሕረ ሰላጤው አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚኖረውን ጥቅም ይገነዘባሉ ሲሉም አክለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 ትራምፕ የ110 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ መሣሪያዎችን ሽያጭ ጨምሮ ከ450 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ስምምነቶችን መፈረማቸውን ይጠቅሳሉ።
በዚህ የሥልጣን ዘመናቸው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እስከ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ የኢንቨስትመንት ስምምነት ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በተጨማሪም ዋይት ሐውስ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ 1.4 ትሪሊየን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ቃል ገብታለች ብሏል።
ትራምፕ ከዚህ ጉዞ የተገኙትን "አፋጣኝ ድሎች" ማሳየት እንደሚፈልጉ በዋሽንግተን የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአሜሪካ ጉዳዮች ተንታኝ ሐሰን ምንይምነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እነዚያን ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች፣ በተለይም ወታደራዊ ስምምነቶችን፣ በተቻለ ፍጥነት ተፈጻሚ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ።
ከዚያም የንግድ ፖሊሲያቸው ስኬት አድርገው እንደ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ያልተረጋጋው መካከለኛው ምሥራቅ
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዝርዝር ውስጥ ካሉ ቀዳሚ ነገሮች መካከል እስራኤል በጋዛ ከምታካሄደው ጦርነት በኋላ ያሉ ዕቅዶች እና ከኢራን ጋር ያላለቀው የኒውክኀየር ጦር መሳሪያዎች ድርድር ናቸው።
የባህረ ሰላጤ አጋሮቻቸው ደግሞ ለሁለቱም አጀንዳዎቻቸው ጠቃሚ ይሆናሉ ።
አዲሱ የሥልጣን ዘመናቸውን በጀመሩ የመጀመሪያ ቀናት ትራምፕ አገራቸው ጋዛን ወደ "መካከለኛው ምሥራቅ መዝናኛ" ቦታነት መቀየር ትፈልጋለች ሲሉ ዓለምን አስደንግጠዋል።
የፕሬዝዳንቱ ሃሳብ አብዛኛውን የግዛቲቱን 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወርን ያካተተ ሲሆን፣ ይህም "ትልቅ ሀብት ባላቸው ጎረቤት አገራት" ሊሸፈን ይችላል ብለዋል።
ዕቅዱ በዓለም ዙሪያ በስፋት የተወገዘ ሲሆን፣ ከጦርነቱ በኋላ ለጋዛ ሰርጥ መልሶ ግንባታ የአረብ አገራት ያቀረቡት አማራጭ ሃሳብ በዩናይትድ ስቴትስ እና በእስራኤል ውድቅ ተደርጓል።
በዚህ ጉዞ ላይ ትራምፕ በጦርነት በወደመው የጋዛ ሰርጥ ግዛት ለሚደረገው ማንኛውም የመልሶ ግንባታ ጥረት ከባሕረ ሰላጤው አገራት የገንዘብ ድጋፍ ሊፈልጉ እንደሚችሉ ፕሮፌሰር ባቦድ ገልጸው፣ ነገር ግን ይበልጥ አፋጣኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
"ለአሁን፣ ትራምፕ የባሕረ ሰላጤው አጋሮቻቸው በጋዛ ውስጥ የቀሩትን ታጋቾች ለማስለቀቅ በቅድሚያ እንዲረዷቸው ይወተውታሉ ተብሎ ይጠበቃል" ይላሉ ፕሮፌሰር ባቦድ።
በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቁ የአሜሪካ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር መገኛ የሆነችው ኳታር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚደረገውን ታጋቾችን የማስለቀቅ እና የተኩስ አቁም ስምምነቶችን በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።
አሜሪካ በቅርቡ በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩትን የየመን የሁቲ አማፂያንን ለማጥቃት በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ጦር ከፍ አድርጋለች።
ከትራምፕ ጉብኝት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ኦማን በዋሽንግተን እና በሁቲዎች መካከል እርቅ እንዲፈጠር አሸማግላለች።
ምንይምነህ ምናልባት ሳዑዲ አረቢያ ትራምፕ ከጉብኝታቸው በፊት አገራቸው የምታካሄደውን የአየር ድብደባ እንድታቆም ጠይቃ ይሆናል ብለው ያምናሉ።
ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ስምምነት ላይ መድረስ ካቃታት ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተዋል።
ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በመጋቢት ወር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ኢራንን የምናስተናግድበት መንገድ ሁለት ነው፤ በወታደራዊ መንገድ አልያም ስምምነት ላይ በመድረስ" ካሉ በኋላ እርሳቸው ግን "ስምምነት ላይ መድረስን" እንደሚመርጡ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዝያ 30 በሰጠው መግለጫ "የኢራን መንግሥት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ግጭት ማቀጣጠሉን እንዲሁም የኒውክሌር መርሃ ግብሩን በማስፋፋት እንዲሁም የአሸባሪ አጋሮቹን እና ተላላኪዎቹን መደገፉን ቀጥሏል" ብሏል።
ነገር ግን፣ ሁለቱም ወገኖች ጦርነትን ለማስወገድ ፍላጎት ያላቸው ይመስላሉ።
ኦማን በቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ዙሪያ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረገውን ድርድርን እያሸማገለች ነው።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ተጽእኖ
የባሕረ ሰላጤው አገራት በዓለም አቀፍ ቀውሶች ውስጥ ቀላል የማይባል ሚና አላቸው። ሳዑዲ አረቢያ በአሜሪካ፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ቁልፍ አሸማጋይ ሆናለች።
በየካቲት ወር በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል በሪያድ በከፍተኛ የልዑካን ቡድኖች መካከል የተደረገ ስብሰባ የዩክሬን ጦርነትን ለማቆም ተወያይቷል።
ስብሰባው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 ሩሲያ ሙሉ በሙሉ ዩክሬን ላይ ወረራ ከጀመረች በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ንግግር ሲሆን፣ ምዕራባውያን ሞስኮን ለማግለል የሚያደርጉትን ጥረት ማቆሙን አመልክቷል።
በመጋቢት ወር እንዲሁ የሳዑዲ መንግሥት በዩክሬን ስላለው ጦርነት ከሦስቱም አገሮች የተውጣጡ ልዑካን ያካሄዱትን ውይይት አስተናግዳለች።
በየካቲት ወር መገባደጃ ላይ በትራምፕ እና በዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ መካከል በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ውስጥ ከተፈጠረው አለመግባባት በኋላ በጅዳ የተካሄደው የአሜሪካ እና የዩክሬን ውይይት የመጀመሪያው ሲሆን፣ በዩክሬናውያን "ውጤታማ" ተብሎ የተገለጸው እና በሪያድ የተደረገው ተጨማሪ ንግግር አንዳንድ ግንኙነቶችን ለማስተካከል ረድቷል ።
ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሩሲያ እና ዩክሬን የጦር እስረኞችን እንዲለዋወጡ ድርድሮች እንዲደረጉ ማመቻቸት ችሏል ።
የባሕረ ሰላጤው አገራት "አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ቀውሶችን በማደራደር፣ እንዲሁም በገንዘብ አቅማቸው እና ሰፊ የነዳጅ እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝ ክምችታቸው የተነሳ" ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተፅእኖን መፍጠራቸውን ፕሮፌሰር ባቦድ ይናገራሉ።
ቻይና እና ሌሎች የአሜሪካ ተቀናቃኞች የባሕረ ሰላጤውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ይገነዘባሉ፤ ስለዚህም ዋሽንግተን ከአካባቢው አጋሮቿ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መቀጠል ትፈልጋለች።
የሳዑዲ እና የእስራኤልን ግንኙነት ማሻሻል
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በእስራኤል እና በአራት የአረብ አገራት በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ በባህሬን፣ በሞሮኮ እና በሱዳን መካከል ስምምነት እንዲደረስ በማድረግ ረገድ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ውጤት አግኝተዋል።
ሦስቱ አገራት ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመሥረት ብቸኛዎቹ የአረብ አገራት ሆነዋል።
በሱዳን እየተካሄደ በሚገኘው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመሥረት ሳትችል ቀርታለች።
የአረብ እና የሙስሊሙ ዓለም ቁልፍ መሪ የሆነችው ሳውዲ አረቢያ እስካሁን ለእስራኤል በይፋ እውቅና አልሰጠችም።
አንድ የሳውዲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ባለፈው ዓመት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሐማስ በእስራኤል ላይ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃት ከማድረሱ በፊት ስምምነት ላይ ለመድረስ "ተቃርበው" ነበር።
ነገር ግን ትራምፕ በቅርቡ ሳውዲ አረቢያ ነፃ የፍልስጤም መንግሥት መመሥረትን እንደ ቅድመ ሁኔታ ላትጠይቅ እንደምትችል ሃሳብ ካቀረቡ በኋላ መንግሥት "ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት" እንደማይኖር በድጋሚ አስታውቃለች።
ታዛቢዎች ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ለሳዑዲ አረቢያ የበለጠ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል ብለው ያምናሉ።
ፕሮፌሰር ባቦድ አሁንም በጋዛ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ሳዑዲ አረቢያ በጉብኝቱ ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ለመወያየት ዝግጁ አትመስልም ብለዋል።
ትራምፕ በእስራኤል እና በሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል ለማድረግ እንደሚሠሩ ይጠበቃል።
ነገር ግን በእስራኤል እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ወደፊት የሚኖር ማንኛውም ስምምነት እጅግ የላቀ ወሳኝ ምዕራፍን ያሳያል።