የአዲስ ዓመት አከባበር ሥርዓቶች በተለያዩ የዓለም አገራት

ዝናባማው የክረምት ወቅት አብቅቶ፣ ቅዝቃዜው እየተገፈፈ፣ ብርሃን መታየት ሲጀምር፣ ምድር በልምላሜ እና በአደይ አበባ ስትፈካ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመታቸውን አንድ ብለው ይጀምራሉ።

አሮጌው ዓመት አብቅቶ በአዲስ መተካቱን በሚያበስረው በአደይ አበባ ምድር ትዋባለች።

የክረምቱን ማብቃት እና የአዲስ ዘመን መግባትን የምታበስረው የመስቀል ወፍም በአዲስ ላባዋ ደምቃ ብቅ ትላለች።

ኢትዮጵያውያን ከሌላው ዓለም ሕዝቦች ልዩ የሚያደርጋቸውን 13 ወራት አጠናቅቀው መስከረም አንድ ላይ አዲስ ዓመታቸውን ያከብራሉ።

አዲሱን ዓመትም በልጃረዶች የአበባዮሽ ጭፈራ፣ በወንድ ታዳጊዎች የመልካም ምኞት መግለጫ ሥዕል ማጀብ የተለመደ ነው።

ከዚህ ባሻገርም እንደ ቤተሰቡ አቅም ዶሮ ወይንም በግ ማረድ፣ ጠላ መጥመቅ፣ ድፎ ዳቦ መቁረስ የዕለቱ ማድመቂያዎች ናቸው።

ቤትን በተለያየ ነገር ማሰዋብ ቄጤማ ከአደይ አበባ ጋር አድርጎ ጎዝጉዞ አዲሱን ዓመት መቀበል የበርካታ ኢትዮጵያውያን ልማድ ነው።

ምሽት ላይም ችቦ ለኩሶ "እሰይ መስከረም ጠባ" እያሉ እየዘመሩ አዲስ ዓመትን መቀበል የባሕሉ አካል ነው።

ከምድር ልምላሜ እና የአደይ አበባ ፍካት ጋር ተደማምሮ የሚከበረው አዲስ ዓመት እንደ የአካባቢው እንደየ ባህሉ የተለያየ የአከባበር መልክ ሊኖረው ይችላል።

በተለያዩ አካባቢዎች የአዲስ ዓመት መቃረብን የሚያመለክቱ የተለያዩ ክብረ በዓሎች አሏቸው።

ወንዶች ሆያ ሆዬን በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በመጨፈር ክረምቱ እያበቃ መምጣቱን ያበስራሉ። 'ዶሮ ከጮኸ የለም ለሊት ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት' ሲሉም በተረት ያጅቡታል።

በትግራይ አሸንዳ፣ በሰቆጣ አካበቢ ሻደይ፣ በላሊበላ ደግሞ አሸንድዬ፣ እንዲሁም በቆቦ አካባቢ ሶለል በመባል የሚታወቁትም በዓላት የአዲስ ዓመት መምጣትን መጠቆሚያ ናቸው።

ከዚህ በኋላ ይኸው የልጃገረዶች ጭፈራ በአበባዮሽ በሚል የልጃገረዶች ጭፈራ ይተካል።

አበባዮሽ ልጃገረዶች በየሠፈራቸው በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ቤት ለቤት እየዞሩ በጭፈራ ሰውን እያወደሱ ገንዘብ በመሰብሰብ የሚቦርቁበት ባህል ነው።

ለቀሪው ማኅበረሰብ ደግሞ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ፣ የአዲስ ዘመን መጀመሪያ ዜማ ነው።

ኢትዮጵያዊያን የአዲስ ዓመት ጅማሯቸውን ተሰባስበው፣ በደስታ እና በፍቅር "እንኳን አደረሰህ፣ አደረሰሽ"፤ "መልካም አዲስ ዓመት" እየተባባሉ ከፊታቸው ያሉት 13 ወራት በጎ እንዲሆኑ እርስ በእርሳቸው መልካም ምኞታቸውን ይገላለጻሉ።

ሌሎች አገራትስ አዲስ ዓመታቸውን እንዴት ያከብሩታል?

በዓለም ላይ ያሉ የተለያዩ አገራት ሕዝቦች አዲስ ዓመታቸውን የሚያከብሩት በተለያየ ጊዜ ነው።

በርካታ የምዕራባውያን እና ከእነሱ ጋር ትስስር ያላቸው አገራት ጥር ወር ላይ አዲስ ዓመታቸውን የሚጀምሩ ሲሆን፣ አንዳንድ የእስያ አገራት ደግሞ ከዚህ የተለየ የአዲስ ዓመት አከባበር አላቸው።

ኢራን በዓለም ላይ የራሳቸው የቀን አቆጣጠር ሥርዓት ካላት አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ አዲስ ዓመቷንም ከሌሎች የዓለም አገራት በተለየ መልኩ የምታከብር ናት።

ኢራን ፀሐይን ወይም የሂጅራ ዘመን አቆጣጠርን መሠረት ያደረገ ሥርዓት ሲኖራት፣ አዲስ ዓመትን ሁሌ መጋቢት ወር ላይ ታከብራለች።

ቻይናም አንዲሁ የራሷ የሆነ የዘመን አቆጣጣር ያላት ሲሆን ሉናር የተሰኘ ዘመን አቆጣጠር ሥርዓትን ትከተላለች።

የቻይና አዲስ ዓመት የሚከበርበት ወር በየአራት ዓመቱ የሚቀያየር ቢሆንም አዲስ ዓመቱ የካቲት ወር ላይ ይከበራል።

የካቲት ላይ አዲስ ዓመቷን የምታከብረው ሌላኛዋ አገር ሰሜን ኮሪያ ናት። ይህች ከምዕራባውያኑ ጋር የተኳረፈች አገር ሶላል የተሰኘ የራሷን የዘመን አቆጣጠር ትከተላለች።

ሌላኛዋ የእስያ አገር ሕንድ ደግሞ ሚያዝያ ወር ላይ አዲስ ዓመቷን ታከብራለች።

በየዓመቱ ጥቅምት ወር ላይ አዲስ ዓመቷን አንድ ብላ የምትጀምረው ደግሞ እስራኤል ስትሆን የሂብሩ የዘመን አቆጣጠርን ትከተላለች።

በመላው ዓለም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ አዲስ ዓመት ሲከበር ርችት መተኮስ የተለመደ ሆኗል።

ትልልቅ የርችት ትርዒቶች የሚከናወኑት በአብዛኛው እኩለ ሌሊት ላይ ነው።

በኒው ዚላንድ፣ ኦክላንድ ስካይ ታወር ብዙውን ጊዜ አስደናቂ የሆነ የርችት ትርዒት ማሳያ ስፍራ ነው።

በአውስትራሊያ እንዲሁ በሲድኒ የባሕር ዳርቻ ላይ በተመሳሳይ ግዙፍ የርችት ትርዒት ይታያል።

በካናዳ ቶሮንቶ፣ በናታን ፊሊፕስ አደባባይ፣ በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ፣ በከተማዋ ታዋቂ በሆነው የኮፓካባና የባሕር ዳርቻ ከዕኩለ ሌሊት ጀምሮ ሰማዩ በርችት በርቶ ያመሻል።

በዴንማርክ አዲስ ዓመት በሚከበርበት ወቅት ሳህን መስበር የተለመደ ነው።

ዴንማርካውያን ከዕኩለ ሌሊት በኋላ በቤታቸው በራፍ ላይ ሳህን በመስበር አዲሱን ዓመት ብሩህ እንዲሆን ይመኛሉ።

ይህ ሳህን የመስበር ባሕል ግን በራስ ቤት በር ደጃፍ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም።

ወዳጅ፣ ዘመድ እና ጓደኛ ቤት በር ላይ ሄዶ ሳህን በመስበር መጪዎቹ 12 ወራት የስኬት እንዲሆኑ የመልካም ምኞት መግለጫ ማድረስም ይቻላል።

ምስር መብላት

በብራዚል በአዲስ ዓመት ምስር መብላት የመልካም ዕድል መግለጫ፣ አዲሱ ዓመት በገንዘብ የሚንበሸበሹበት እንደሚሆን መተንበያ ተደርጎ ይቆረጣል።

ኳስ መጣል

በአሜሪካን ኒውዮርክ ደግሞ የአዲስ ዓመት አከባበር ፍጹም የተለየና ደማቅ ነው።

11ፓውንድ ክብደት ያለው ኳስ ከፍተኛ የብረት ማማ ላይ በማንጠልጠል አሮጌው ዓመት ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በየእያንዳንዱ ሴኮንድ ዝቅ እያለ መውረድ ይጀምራል።

በስፍራው የሚገኝ ታዳሚ የአዲሱን ዓመት መግባት በእያንዳንዱ ሰከንድ አብሮ እየቆጠረ ያከብራል።

ልክ ዕኩለ ሌሊት ሲሆን፣ ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ላይ የአዲሱ ዓመት መግባት ማብሰሪያ የሆነው ርችት ይተኮሳል።

ይህ ግዙፍ ኳስ የመጣል (ball drop) ሥነ ሥርዓት የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

የወይን ፍሬ መብላት

በአውሮፓዊቷ ስፔን ደግሞ ልክ ዕኩለ ሌሊት ሲሆን ሰዎች የወይን ፍሬ መብላት ይጀምራሉ።

ይህም ዕኩለ ሌሊት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በእያንዳንዱ ሰዓት ልዩነት አንዳንድ የወይን ፍሬ መመገብ የባህላቸው አካል ነው።

በየሰዓቱ ልዩነት የሚበሏቸው ፍሬዎች በአዲሱ ዓመት መልካም ነገር ይዘው ይመጣሉ ተብሎ ይታመናል።

በድብ አምሳል የተሠራ ልብስ መልበስ

በሮማኒያ በድብ አምሳል የተሠራ ልብስ ለብሶ መደነስ እና ክፉ መንፈስን ማባረር በአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ወቅት የሚዘወተር ተግባር ነው።

ይህም በሮማኒያ ጥንታዊ ባህል መሠረት ድቦች ሰዎችን ከክፉ መንፈስ የመጠበቅ እና የመፈወስ ኃይል አላቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው።

ደወል መደወል

እንደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ አገራት አዲስ ዓመትን ለመጀመር ደወል ይደውላሉ።

በጃፓን 108 ጊዜ የሚደወል ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ በአዲስ ዓመት በየአካባቢው የደወል ድምጽ ጎልቶ ሊሰማ ይችላል።

በደቡብ አፍሪካ የማይፈለጉ ዕቃዎችን አውጥቶ በመጣል አዲስ ዓመትን በአዲስ ዕቃ መቀበል የተለመደ ሲሆን፣ በአንዳንድ የደቡብ አሜሪካ አገራት ደግሞ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ባዶ ሻንጣ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ይታያሉ።

አንዳንዶች "ሻንጣዎችን ተሸክሞ በጎዳና ላይ መንቀሰቀቀስ" በአዲሱ ዓመት በተለያዩ ጀብዱዎች የተሞላ እንደሚሆን ያምናሉ።