ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ጥቃት ቢፈጸምባቸው በጋራ ለመቆም ስምምነት ተፈራረሙ
ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ከየትኛውም ወገን በአንዳቸው ላይ ጥቃት ቢፈጸም “ለመተባበር” መስማማታቸውን ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናገሩ።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ፕሬዝዳንት ፑቲንን ጠቅሰው እንደዘገቡት ፒዮንግያንግ እና ሞስኮ የተፈራረሙት ስምምነት “በአንድኛው ወገን ላይ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት” ሌላኛው ወገን ድጋፍ በመስጠት አብሮት እንደሚቆም ዘግበዋል።
ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ በወታደራዊ ጉዳይ ላይ ደርሰውታል የተባለው ስምምነት ዝርዝር እስካሁን አልታወቀም። ይሁን እንጂ የሰሜን ኮሪያው መሪ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት “ሙሉ በሙሉ” ትደግፋለች ስለማለታቸው ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ ፑቲን እና ኪም በሁለቱ አገራት አዋሳኝ ድንበር ላይ ድልድይ ለመገንባት እንዲሁም በጤና፣ በጤና ትምህርት እና በሳይንስ ዘርፎች አብሮ ለመሥራት የሁለትዮሽ ስምምነት መፈረማቸው የሩሲያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ፑቲን ሰሜን ኮሪያ ሲደርሱ በደማቅ ወታደራዊ ትዕይንት እና በርካታ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ አቀባበል ያደረገላቸው ሲሆን፤ እርሳቸውም የሰሜን ኮሪያው መሪ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ሞስኮ እንዲመጡ ጋብዘዋል።
ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆን ኡን በውይይታቸው ወቅት አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲያሞካሹ ነበር።
ኪም ጆንግ ኡን ሩሲያ የሰሜን ኮሪያ “ሃቀኛዋ ወዳጅ እና አጋር ነች” ካሉ በኋላ ፑቲንን ደግሞ “የኮሪያ ሕዝብ ውድ ወዳጅ” ብለው ስለመግለጻቸው የሩሲያ ዜና ወኪል ዘግቧል።
ፑቲንም ለሰሜን ኮሪያው ወዳጃቸው “የራሳቸው መገለጫ ናቸው” የተባለ ሙሉ ሻይ ማቅረቢያ ዕቃ፣ ሩሲያ ሠራሹን ቅንጡ ‘አውራስ’ የተሰኘ መኪና እና ጎራዴ በስጦታ መልክ ለኪም አበርክተዋል።
ሁለቱ መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው ለሁለት ሰዓታት መምክራቸውንም የተለያዩ ሪፖርቶች ጠቁመዋል።
የደቡብ ኮሪያ ቁጣ
የኪም እና የፑቲን የጠበቀ ወዳጅነት ደቡብ ኮሪያን አላስደሰተም።
የደቡብ ኮሪያ መሪዎች ሁለቱ መሪዎች ሲገናኙ ወታደራዊ ትብብር ላይ ሰምምነት እንደሚፈጽሙ የደኅንነት መረጃዎች ቀድሞ ደርሶናል ያሉ ሲሆን፣ ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ባላት ግንኙነት “ቀይ መስመር ማለፍ የለባትም” ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ቻንግ ሆ-ጂን ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ያለው ጦርነት ሲያበቃ ወዳጅነቷን ከሰሜን ኮሪያ ወይም ከደቡብ ኮሪያ ጋር ማስቀጠል እንዳለባት ማወቅ ይኖርበታል ብለዋል።
ዩክሬን ከሩሲያ ጦርነት ከተከፈተባት በኋላ ለደቡብ ኮሪያ ያቀረበችው ወታደራዊ ድጋፍ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።
ፑቲን የሰሜን ኮሪያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ቀጣይ መዳረሻቸው ቬይትናም እንደምትሆን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የቬይትናሟ መዲና ሃኖይ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ለመቀበል ትልቅ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች።
አርፋጁ ፑቲን
ቭላድሚር ፑቲን የሰሜን ኮሪያ ጉብኝታቸውን ዛሬ የሚያጠናቅቁ ቢሆንም ሰሜን ኮሪያ የደረሱት ብዙ ዘግይተው ስለመሆኑ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።
በእርግጥ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ከዚህ ቀደም በመዘግየት መሪዎችን ብዙ በማስጠበቅ ስም የወጣላቸው መሪ ናቸው በመባል ይታማሉ።
የቀድሞ የጀርመን መራሄተ መንግሥት አንጌላ መርክልን አራት ሰዓታት አስጠብቀው ነበር። ከቀድሞ የጃፓን ፕሬዝዳንት ሺንዞ አቤ ጋር ለነበራቸው ስብሰባ 3 ሰዓታት አርፈርደዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይም 80 ደቂቃዎችን አርፍደው ተገኝተው ያውቃሉ። አንድ ወቅት ደግሞ ፖፕ ፍራንሲስን ጭምር 50 ደቂቃ አስጠብቀዋል።
ፑቲን እስካሁን አርፍደው የማያውቁት አንድ መሪ ላይ ብቻ ነው። እርሳቸውም የቻይናውን ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ናቸው።