ምዕራባውያንን እረፍት የነሳው የፑቲን የሰሜን ኮሪያ ጉብኝት እውን ሊሆን ነው?

ሩሲያን በዐይነ ቁራኛ የሚከታተሉ አገራት፤ ሰላዮችም ሆኑ ጋዜጠኞች የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የሰሜን ኮሪያ ጉዞን ሲጠባበቁ ቆይቷል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ጥይት በማይበሳው ባቡር ምሥራቃዊ ሩሲያን ከረገጡ በኋላ፤ ኪም ጆንግ ኡን ለፕሬዝዳንት ፑቲን ይፋዊ የጉብኝት ግብዣ አቅርበውላቸው ነበር።

ፑቲንም ከሰሜን ኮሪያው አምባገነን መሪ የቀረበላቸውን ግብዣ በአክብሮት ተቀብለውታል።

መቀመጫውን ሞስኮ ያደረገው የቢቢሲው ጋዜጠኛ ቤን ታቭነር ይህ ለወራት ሲጠበቅ የነበረው ጉዞ እውን የሚሆንበት ጊዜ የተቃረበ ይመስላል ይላል።

የደቡብ ኮሪያ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ፑቲን በቀናት ጊዜ ውስጥ ምናልባትም ማክሰኞ ሰኔ 11/2016 ዓ.ም. ፒዮንግያንግ ሊገኙ ይችላሉ።

የሳተላይት ምሥሎችም በሰሜን ኮሪያ ትልቅ እንግዳን ለመቀበል የሚደረጉ ዝግጅቶችን አሳይተዋል።

የፑቲን የሰሜን ኮሪያ ጉብኝነት ምን ትርጉም አለው?

የመጀመሪው ጥያቄ ፑቲን ለምን አሁን ወደ ሰሜን ኮሪያ መጓዝ አስፈለጋቸው ብለን መጠየቅ እንችላለን ይላል ቤን።

ፑቲን ወደ ፒዮንግያንግ የሚያመሩት ከ24 ዓመታት በኋላ ነው። ፑቲን እአአ 2000 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሲጓዙ በሥልጣን ላይ የነበሩት የኪም አባት፤ ታላቁ መሪ ኪም ጆንግ ሁለተኛው ነበሩ።

ይህ በሁለቱ አገራት መካከል እየዳበረ የመጣው የሁለትዮሽ ግንኙነት ምዕራባውያን አገራትን እረፍ የሚነሳ ጉዳይ ሆኗል።

ክሬምሊን በሩሲያ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል “ጥልቅ የሆነ ግንኙነት” መመሥረት የሚያስችል አጋጣሚ አለ ይላል።

አንዱ ከሌላኛው አገር ምን ይፈልጋል በሚለው ጉዳይ ብዙዎች የተለያየ ግምት ሲሰጡ ቆይተዋል። የብዙዎች ግምት ግን በአንድ ጉዳይ ላያ ያጠነጥናል - የጦር መሳሪያ ግብዓት።

ሩሲያ ተተኳሾችን፣ የግንባታ ሠራተኞችን ምናልባትም በዩክሬን ጦርነት የሚሳተፉ ወታደሮችን ከሰሜን ኮሪያ ትፈልግ ይሆናል ሲሉ የፖለቲካ ሳይቲስቱ ሰርጌይ ማርኮቭ ይናገራሉ።

በአንጻሩ የሰሜን ኮሪያው መሪ ረዥም ርቀት ተተኳ ሚሳኤሎች እና ሮኬቶች አፍቃሪ ናቸው። ፒዮንግያንግ ወታደራዊ ዓላማዎችን ማሳካት የሚያስችላትን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከሩሲያ ማግኘትን አጥብቃ ትሻለች።

ስለዚህም አሜሪካንን መምታት የሚችሉ የረዥም ርቀት ተመዘግዛጊ ሚሳኤሎች ፕሮግራም ግብዓቶችን ከሩሲያ ልታገኝ ትችላለች በማለት ማርኮቭ ይናገራሉ።

በቅርቡ ብሉምበርግ የደቡብ ኮሪያን የመከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ ሰሜን ኮሪያ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተተኳሾችን ወደ ሩሲያ ልካለች።

ሞስኮ በምዕራባውያን ስለተጣለባት ማዕቀብ ቁብ የማትሰጥ እንዲሁም ለምዕራባውያን ጭፍን ጥላቻ ያላትን አገርን ወዳጅ ማድረግ አዋጪ ነው።

ጋዜጠኛ ቤን ሁለቱ አገራት በዓለማችን በምዕራባውያን በርካታ ማዕቀብ የተጣለባቸው አገራት መሆናቸውንም መዘንጋት የለብንም ይላል።

ከወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ ሊያስተላለፍ የነበረውን የማዕቀብ የውሳኔ ሃሳብ ሩሲያ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ አድርጋዋለች።

ይህም ሞስኮ ለፒዮንግያንግ ያላትን ወዳጅነት በአደባባይ ያስመሰከረችበት ውሳኔ ተደርጎ ተወስዷል።

ወዳጅነቱ በሁለቱ አገራት ብቻም ሳይሆን በመሪዎች መካከል እንዳለ በግልጽ እየታየ ነው።

ፑቲን ከአምስት ወራት በፊት የመንግሥታቱ ድርጅት ማዕቀብን በተመተላለፍ ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሩሲያ ሰራሽ ቅንጡ ሊሞዚን በስጦታ መልክ አበርክተው ነበር።

ፑቲን ሰሜን ኮሪያን በመጎብኘት የፈለጉትን ነገር ማድረግ እንደሚችሉ ለምዕራባውያን ማስመስከር ይችላሉ።

በምዕራባውያን የተጣሉ ማዕቀቦች ሩሲያ ላይ ይህ ነው የሚባል ጫና እንደማያሳድሩ በሰሜን ኮሪያ ጉብኝታቸው ማሳየት ይሻሉ።

ጉብኘቱ ከዚህም በላይ ሌላም ትርጉም ይኖረዋል። ሌሎች አገራትም ማዕቀቦችን ተላልፈው ለሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን ቢሸጡ ምንም እንደማይመጣ ፑቲን በፒዮንግያንግ ጉብኝታቸው ማረጋገጫ ይሰጣሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፑቲን በአሜሪካ በሚዘወረው የዓለም ሥርዓት ደስተኛ ያልሆነ ወዳጃችን ነው በሚል ፍልስፍና ከእስያ፣ ከላቲን አሜሪካ እና ከአፍሪካ ወዳጆችን እያሰባሰቡ ነው።

ፑቲን በምዕራባውያን ከባድ ማዕቀብ ስር ከምትገኘው እና በመካከለኛው ምሥራቅ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆነችው ኢራን ጋርም እንደ ሰው አልባ አውሮፕላን ያሉ ወታደራዊ ቁሶችን እስከ መገበያየት የደረሰ ወዳጅነት መሥርተዋል።

በዚህ መካከል ተራ ሩሲያውያን አገራቸው ከተቀረው ዓለም ከተገለለችው ከሰሜን ኮሪያ ጋር እየመሠረተች ስላለው ግንኙነት ምን ሊሰማቸው ይችላል ሲል ቤን ይጠይቃል።

ምናልባት ሩሲያውያን በባሕል እና በኑሮ ዘያቸው ከሚመስሏቸው አውሮፓውያን ይልቅ በብዙ መልኩ ከሚለዩት ከሰሜን ኮሪያውያን ጋር የሚዳብረውን ወዳጅነት እንደ ፖለቲከኞቹ በአዎንታዊነት ላይመለከቱት ይችላሉ።

ምንም ሆነ ምን ከጉብኝቱ መጨረሻ በኋላም በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረሰውን ስምምነት ዝርዝር ላናውቅ እንችላለን።

አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው፤ ፑቲንን ወደ ፒዮንግያንግ የሚወስዳቸውን አውሮፕላን ሲሳፈሩ ለምዕራባውያኑ ከፈለጉት አገር ጋር ካሻቸው ፖለቲካም ሆነ ንግድ መዋዋል እና መሥራት እንደሚችሉ በግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ።