በኡጋንዳ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ በደረሰ የመብረቅ አደጋ 13 ህጻናት ሞቱ

የፓላቤክ የስደተኞች ጣብያ ከ80 ሺህ በላይ ስደተኞች ተጠልለውበታል

የፎቶው ባለመብት, Oxfam

በኡጋንዳ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ በደረሰ የመብረቅ አደጋ 13 ህጻናት እና አንድ ወጣት መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የመብረቅ አደጋው የደረሰው ተጎጂዎቹ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የቤተክርስትያን አገልግሎት ላይ እያሉ ነበር ብሏል።

ሌሎች 34 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

አደጋው የደረሰው በአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኘው ፓላቤክ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አካባቢው ነጎድጓድ እና መብረቅ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ አስተናግዷል።

የኡጋንዳ ፖሊስ ቃል አቀባይ ኪቱማ ሩሶኬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቅዳሜ ህይወቱ ያለፈው ወጣት 21 ዓመቱ ነው።

የሌሎቹን ልጆች ትክክለኛ ዕድሜ ግን አልገለጹም።

የፓላቤክ የስደተኞች ጣብያ ከ80 ሺህ በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚገኙበት መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።

ብዙዎቹ ስደተኞች ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን የመጡ ናቸው።

ከአራት ዓመት በፊት በሰሜን ምዕራብ ኡጋንዳ በምትገኘው አሩዋሰ ከተማ በደረሰ የመብረቅ አደጋ 10 ህጻናት ህይወታቸውን አጥተዋል።

ልጆቹ ህይወታቸው ያለፈው እግር ኳስ ተጫውተው በእረፍት ላይ እያሉ ነበር።