የካናዳዋ ፋይናንስ ሚኒስትር ትራምፕ ታሪፍ እጨምራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ከሥልጣናቸው ወረዱ

የካናዳዋ ፋይናንስ ሚኒስትር ክሪስቲያ ፍሪላንድ ከሥልጣናቸው መውረዳቸውን አሳውቀዋል።

ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ካናዳ ላይ ታሪፍ እጨምራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ እንዴት ምላሽ ይሰጥ በሚለው ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር ባለመስማማታቸው መውረዳቸውን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

ሰኞ ዕለት ለትሩዶ በላኩት ደብዳቤ "ለካናዳ የወደፊት ዕጣ ፈንታ" ከትሩዶ ጋር አለመስማማታቸውን ተናግረዋል።

የትራምፕ ፖሊሲ "ያፈጠጠ ምጣኔ ሀብታዊ ብሔራዊነት" ነው ያሉት ሚኒስትሯ ይህ ትልቅ "ፈተና ይጋርጣል" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ፍሪላንድ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ የወሰኑት ትሩዶ ባለፈው ሳምንት የመንግሥታቸው ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት አማካሪ ሆነው እንዲቀጥሉ እንደማይፈልጉ ካሳወቋቸው በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ ዓመታዊ ፊስካል ሪፖርት ለፓርላማው ያቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነው ከሥልጣናቸው መውረዳቸውን ያሳወቁት።

የፍሪላንድ ከሥልጣን መልቀቅ እየተንገዳገደ ላለው የጀስቲን ትሩዶ መንግሥት አደጋ አለው እየተባለ ነው።

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ከመንበራቸው እንዲወርዱ ጫና እየበረታባቸው ይገኛል።

የሊበራል ፓርቲ መሪው ተቀባይነታቸው ከ63 ወደ 28 በመቶ ዝቅ ማለቱን አንድ ጥናት አመልክቷል።

ፍሪላንድ ከሥልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ አምስት የሊበራል ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮች ትሩዶ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ በይፋ ጠይቀዋል።

"በቀናነት ሲያገለግሉ የነበሩትን የፋይናንስ ሚኒስትር ማባረር ትክክለኛ እርምጃ አይደለም" ሲሉ የፓርላማ አባሏ ሔሌና ጃሼክ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የፍሪላንድን ከሥልጣን መውረድ ተከትሎ የሊበራል ፓርቲው ኮውከስ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

የፐብሊክ ሴፍቲ ሚኒስትር የነበሩት ዶሚኒክ ሌብላንክ በሰዓታት ውስጥ ፍሪላንድን ተከተው የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

ዶሚኒክ የትሩዶ የልጅነት ጓደኛ ሲሆኑ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ደጋፊዎች አንዱ ናቸው።

አዲሱ የፋይናንስ ሚኒስትር ቃለ-መሐላ ሲፈፅሙ ትሩዶ ቢገኙም ንግግር አላሰሙም። የትሩዶ ቢሮ እና የፋይናንስ ሚኒስቴር ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

ፍሪላንድ ለሕዝብ ባጋሩት የመልቀቂያ ደብዳቤያቸው ካናዳ ትራምፕ ካናዳ ላይ ሊጭኑ ላሰቡት የታሪፍ ጭማሪ መዘጋጀት አለባት ብለዋል።

ትራምፕ ሥልጣን ሲይዙ ከካናዳ የሚመጡ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይህ ካናዳን የሚጎዳ ውሳኔ ነው ይላሉ።

ፍሪላንድ ይህን የትራምፕ ውሳኔ "ማስፈራራት ነው" ብለው ሀገራቸው ጉዳዩን "በአንክሮ እንድታጤነው" መክረው ነበር።

ፍሪላንድ እና ትሩዶ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ያቀረቡትን ፖሊሲ ተከትሎ አለመስማማት ላይ እንደነበሩ ተነግሯል።

ከፖሊሲዎቹ መካከል በዓመት ከ150 የካናዳ ዶላር በታች ገቢ ላላቸው ካናዳዊያን የ250 ዶላር ቼክ እንዲሰጥ የሚል ይገኝበታል። ይህን ለማሳካት መንግሥት 4.68 ቢሊዮን የካናዳ ዶላር መመደብ ይኖርበታል።

በበዓላት ወቅት ደግሞ አስፈላፊ የሚባሉ ቁሳቁሶች ላይ የግብር እፎይታ እንዲደረግም ታስቧል። ይህ ዕቅድ ሊፀድቅ እንደሚችል ሲጠበቅ የ250 ቼክ ጉዳይ ግን አከራካሪ ሆኗል።

የፋይናንስ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ፍሪላንድ የትሩዶ የቅርብ አጋር ነበሩ። ከ2020 ጀምሮ የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።