ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል ሲሉ የነዳጅ ላኪዎች ህብረት መሪ አስጠነቀቁ
ለሃይል አቅርቦት ያለው ፍላጎት በመጨመሩ የነደጅ ዋጋ እንዳሻቀበ ይቀጥላል ሲሉ ‘ኦፔክ ፕላስ’ ዋና ጸሀፊ ተናገሩ።
‘ኦፔክ ፕላስ’ የ23 ነዳጅ ላኪ ሀገራት ህብረት ሲሆን በዓለም ገበያ ላይ የሚቀርበውን የድፍድፍ ነዳጅ መጠን የሚወስን ነው።
ዋና ጸሃፊው ሄይታም አል ጋሂስ “በቀን የነዳጅ ፍላጎት ወደ 2.4 ሚሊዮን በርሜል ሲያድግ እየተመለከትን ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሳዑዲ አረቢያ ዋጋን ከፍ ለማድረግ የድፍድፍ ነዳጅ ምርቷን በቀን በአንድ ሚሊዮን በርሜል ልትቀንስ እንደምትችል ገልጻለች።
ሁለቱ ዋነኛ የነዳጅ አምራችና ‘ኦፔክ ፕላስ’ አባል የሆኑት ሳዑዲና ሩሲያ የወሰኑት ውሳኔ በዚህ ዓመት መጨረሻ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት ያስከትላል ሲል ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።
“ይህ ሁለት ሉአላዊ ሀገራት ሳዑዲ አረቢያና ሩስያ በፍቃደኝነት የወሰኑት ነው። ይህ ውሳኔ እርግጠኛ ልንሆንበት በማንችልበት ሁኔታ ምክንያት የተደረገ ጥንቃቄ ወይም ቅድመ ዝግጅት ብለን ልንገልጸው እንችላል” ሲሉ የ‘ኦፔክ ፕላስ’ ዋና ጸሃፊ ተናግረዋል።
ሩስያ ዩክሬን መውረሯን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የአንድ በርሜል ነዳጅ ከ120 ዶላር በላይ ከፍ ብሏል። ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ እስከ 70 ዶላር ወርዶ የነበረ ቢሆንም ነዳጅ ላኪ ሀገራት ምርት በመቀነስ ገበያውን ለመቆጣጠር በመሞከራቸው ምክንያት ዋጋው ማሻቀብ ጀምሯል።
ዛሬ ማክሰኞ በምርት እጥረት ምክንያት የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 95 ዶላርን ያለፈ ሲሆን ዋጋው 100 ዶላርን ሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ይህ የዋጋ ለውጥ በሚቀጥሉት 10 ወራት ውስጥ የነደጃው ዋጋ ሊያሻቅብ እንደሚችልና በወሳኝ የኢኮኖሚ መስኮች ያለው የዋጋ ግሽበት ለረዥም ጊዜ እንዲቀጥል ምክንያት ይሆናል የሚል ስጋትን አጭሯል።
ሆኖም ‘ኦፔክ ፕላስ’ ዋና ጸሀፊ የሚመሩት ህብረት የሚያሳስበው ለደፍድፍ ነዳጅ ኢንቨስትመንት የተሰጠው ዝቅተኛ ቦታ ነበር።
“አንዳንዶች ነዳጅ ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት እንዲቆም ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር። ይህ በጣም አደገኛ እንደሆነ እናምናለን። ይህ በወደፊቱ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ አጥረት የሚያስከትል አደጋ ይፈጥራል። ስለዚህ እኛ የኦፔኮች በነዳጅ ምርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስተመንት እናበረታታለን። በተጨማሪም እኛ እራሳችን የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ኢንቨስት እያደረግን በታዳሽ የሃይል አማራጮች ለመዘዋወር እንሰራለን” ብለዋል ‘ኦፔክ ፕላስ’ ዋና ጸሀፊ።
የነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በላይ ሲሆን በዓለም ዙሪያ የዋጋ ግሽበት ላይ ያለውን ተጽዕኖ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ደግሞ “ነገሮችን በአጭር እይታ መመልከት ጠቃሚ እንዳልሆነ” ገልጸዋል
አል ጋሂስ እንደ አውሮፓውያኑ በ2045 የነዳጅ ኢንቨስትመንት ወደ 14 ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢንቨሰትመንት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
እሳቸው እንደሚሉት ከዛሬ ጋር ሲነጻጸር በ2045 የሃይል አቅርቦት ፍላጎት በ25 በመቶ ከፍ ይላል ያሉ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ሁሉም አይነት የሃይል አማራጭ ያስፈልጋል ብለዋል።
በአቡ ዳቢ ነገ ረቡዕ በነዳጅ ምርት ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ባለድርሻዎች የሚሳተፉበት ዓለምአቀፉ የነዳጅ ኤግዚቢሽን እና ጉባኤ ይከፈታል።