የጋቦን እግር ኳስ ቅሌት፡ ለወሲባዊ ብዝበዛ የተጋለጡት ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች

ማሳሰቢያ፡ ይህ ዘገባ አንዳንድ አንባቢዎቸን ሊረብሹ የሚችሉ ይዘቶቸን አካቷል።

የጋቦን የታዳጊዎች እግር ኳስ ‘ከእኩይ ድርጊት’ ጋር ስሙ ተደጋግሞ ይነሳል። ዝነኛ ተጫዋች ለመሆኑ የጓጉ ታዳጊ እግር ኳሰኞች የወሲብ ጥቃት ሰለባ እንደሆኑ ሲነገር መስማት የተለመደ ነው።

የአገሪቱን እግር ኳስ የሚያስተዳድረው አካልም ታዳጊዎቹን ከዚህ ጥቃት ለመታደግ ‘እዚህ ግባ’ የሚባል ሥራ አልሰራም ሲሉ የሚወቅሱት ብዙዎች ናቸው።

‘ቢቢሲ አፍሪካ አይ’ የተሰኘው የምርመራ ፕሮግራም ከ30 በላይ እማኞችን አነጋግሮ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በሁሉም የጨዋታ ደረጃዎች ችግር እየፈጠረ ስለሚገኝ አንድ የ‘ብዝበዛ ኔትዎርክ’ መረጃ አግኝቷል።

በማዕከላዊ የአፍሪካ ክፍል የምትገኘው ጋቦን በእግር ኳስ አካባቢ ከሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶች ጋር ስሟ መያያዝ የጀመረው ከፈረንጆቹ 1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነው።

ስሙን መግለጽ ያለፈለገ አንድ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ፣ ታዳጊ ሳለ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ካምፕ ውስጥ የደረሰበትን ዛሬ የሆነ ያህል ያስታውሳል።

አንድ ዕለት፣ እሱ እና የእሱ ጓደኞች በውድቅ ሌሊት በቀያይ መብራቶች እና ሙሉ በሙሉ እርቃናቸውን ባሉ ወንዶች ወደ ተሞሉ ክፍሎች ይወሰዳሉ።

“ሰዎቹ እኔ እና ጓደኞቼን መነካኩት ጀመሩ። እያደረጉ የነበሩት ነገር አልገባኝም ነበር። መጸለይ ጀመርኩኝ፣ ወደ ውጪ መውጣት ፈልጌ ነበር ነገር ግን በሩ ተቆልፏል። ይዘው ወደ መሬት ጣሉኝ። ሁለት ጥበቃዎች ነበሩ። የተዘጋጁ ይመስሉ ነበር” ይላል።

ቀጥሏል “ጓደኛዬን መድፈር ሲጀምሩ ተመልክቻለሁ። ዐይኑን እያየሁት ነበር። እሱም እንደዚያው እኔን ያያል። አለቀስኩኝ ደጋግሜ ጮኩኝ። ያየሁትን ነገር የምናገር ከሆነ ለውድድር በድጋሚ እንደማልመረጥ እና ቤተሰቦቼ ሊገደሉ እንደሚችሉ ነገሩኝ” ይላል።

ይህ የያኔው ታዳጊ እግር ኳሰኛ ከዚያ ቀን ወዲህ የጋቦንን መለያ ለብሶ በእግር ኳስ ውድድሮች ላይ አልታየም።

ላለፉት በርካታ ዓመታት በጋቦን እግር ኳስ ውስጥ እየሆነ ያለውን ይህንን ድርጊት ባለሥልጣናት እንዲያውቁት ተደጋጋሚ ጥረት መደረጉን ቢቢሲ ሰምቷል።

በአውሮፓውያኑ 2019 የቀድሞ የጋቦን እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ፓርፊት ንዶንጋ ወደ አገሩ ተመልሶ ‘ጃርዲን ዲ ፉት ቦል አው ጋቦን’ የተሰኘ የስፖርት አካዳሚ አቋቁሟል።

ንዶንጋ በጋቦን የተከበረ ስም ያለው እግር ኳሰኛ ነው። በአውሮፓም ሜዳዎችም እግር ኳስን ተጫውቷል።

በጋቦን እግር ኳስ ውስጥ እየሆነ ያለውን ለባለሥልጣናት አሳውቋል።

በእኔ አቅም የሚቻለውን ሁሉንም ነገር ሞክሪያለሁ ሲል ለቢቢሲ የገለጸው የቀድሞ ተጫዋች የሊጉን ፕሬዝዳንት፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት እና የስፖርት ሚኒስትሩን ማነጋገሩን ይገልጻል።

ግን ጠብ ያለ ነገር አልነበረም።

ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ያደረገው ነገር ችላ ሲባል ፊቱን ወደ መገናኛ ብዙኃን አዙሯል።

ውጤት ግን ተመሳሳይ ነው “የምለውን መስማት የሚፈልግ የለም” ይላል።

ጉዳዩን የዩናይትድ ኪንግደሙ ጋርዲያን ሲዘግበው ግን አራት አሠልጣኞች ታሰሩ። ሦስቱ በእስር ቆይተዋል።

በጋቦን እግር ኳስ ውስጥ ከሚፈጸመው ወሲባዊ ጥቃት ጀርባ በተደጋጋሚ ስሙ የሚነሳው ፓትሪክ አሶሙኑ ኢይ ወይም በቅጽል ስሙ “ካፔሎ” ነው።

ካፔሎ ለአስርት ዓመታት የጋቦን ታዳጊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሆኖ ሠርቷል።

ይህ ማለት፣ ሰውዬው እሱ በሚመራው ብሔራዊ ቡድን የጋቦንን መለያ ለብሶ ወደ ሜዳ የሚገባውን የመወሰን ሥልጣን ያለው እሱ ጋር ነው።

“በመሠረቱ እሱ የአማልክትን ስፍራ ይዞ ነበር ምክንያቱም ሁሉም ያንቆለጳጵሰው ነበር። የማሠልጠኛ ቦታዎች እና አካዳሚዎችንም ጭምር” በማለት ፓርፊት ንዶንጋ ይናገራል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ታኅሣሥ ወር የፊፋ ገለልተኛ የሥነ ምግባር ኮሚቴ በካፔሎ ላይ የሚሰነዘሩ የወሲባዊ ብዝበዛ ክሶች ላይ የቅድመ ምርመራ ማካሄድ ጅምሮ ነበር። በምርመራው ውጤትም ከእግር ኳስ ጋር ከተያያዙ እንቅስቃሴዎች በሙሉ አግዶታል።

ይህንን ቅድመ ምርመራ አዲስ የተቋቋመው የፌጋፉት ወይም የጋቦን እግር ኳስ ፌዴሬሸን የሥነ ምግባር መርማሪ ቡድን በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2022 ወደ መደበኛ ምርመራ አሳድጎታል።

ሆኖም በዚህ ምርመራ ላይ፣ የዓለም አቀፉ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር የሕግ አማካሪው ሎይክ አልቬስ ስጋት አለው።

እሱ እንደሚለው ከሆነ ‘ፌጋፉት’ ይህንን ጉዳይ እንዲመረምረው ማድረግ በራሱ “በሁሉም ደረጃ የጥቅም ግጭት ያስነሳል” ይላል።

“የጉዳቱ ሰለባዎች የበደላቸው ተመሳሳይ ተቋም [ለምርመራ ሲመጣ] እንዴት ሊያምኑት ይችላሉ?” ሲል ይጠይቃል።

ካፔሎ የቀረቡበትን የመድፈር፣ ታዳጊዎችን ለወሲብ ጥቃት አሳልፎ የመስጠት እና የመበዝበዝ ክስን ያመነ ሲሆን፣ ፍርዱን በእስር ቤት ሆኖ እየተጠባበቀ ይገኛል።

የትኞቹ ባለሥልጣናት መቼ ስለጉዳዩ አወቁ? በሚለው ላይ ጥያቄ እየተነሳ ይገኛል።

ማንነቱን ለመደበቅ ስሙ የተቀየረው አሌክሰስ በጋቦን የታዳጊዎች እግር ኳስ ውስጥ አልፎ በአውሮፓ የመጫወት ዕድል አግኝቷል።

ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ መናገር የቻለበትን ምክንያት ሲያስረዳ አገር ውስጥ ስላልሆነ እንደሆነ ይገልጻል። ራሱን በግልጽ ቢያወጣ ሕይወቱን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ይናገራል።

“ካፔሎን አሰሩት ይህንን ካወቁ ስንት ጊዜ ሆነ? እስካሁን ያደረጉትም ነገር የለም። ነገሩን በዝቅተኛው ቦታ ላይ አቁመውታል። እስከ ላይ ድረስ የዘለቀ ነው። ግን ጉዳዩን ለመሸፈን ምንም ነገር ያደርጋሉ። ካፔሎ የመስዋዕት በግ ሆኗል። መታየት የነበረበት ግን ከላይ ያለው ነበር” ብሏል።

ጁሊያን ብለን የምንጠራው ሌላኛው እግር ኳሰኛ ደግሞ ራሱም በ14 ዓመቱ ብዝበዛ እንደደረሰበት ይናገራል።

ተጫዋቹ ለጋቦን እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለበርካታ ዓመታት ተጫውቷል። የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ተጫዋቾች ቁጥርን ለማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነ ያምናል።

“ምን ያህል አሠልጣኞች ወንድ ተጫዋቾችን እንደሚበዘብዙ ባለወቅም፣ ለጊዜው ካፔሎን ብቻ እንመልከት። በጣም ታዋቂ ነው፣ ይህንን ድርጊት ላለፉት 25 ወይም 30 ዓመታት ፈጽሟል። በየዓመቱ ቢያንስ 50 ወንዶችን የማግኘት ዕድል ነበረው። ይህ ካልሆነ ግን ከዚህም ከፍ ያለ ቁጥር ነው ማለት ነው” ይላል።

“ምን ያህሎች የዚህ ድርጊት አካል እንደሆኑ እናስበው። እያወራን ያለነው በሺዎች ስለሚቆጠሩ ወንዶች ነው” ሲልም አክሏል።

የፌግፉት ወይም የጋቦን እግር ኳስ ፌዴሬሸን ኃላፊ ፒሬሩ አሊያን ሟንጓንጊ ከሥልጣን እንዲለቁ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም በሥልጣናቸው ቆይተው በአውሮፓውያኑ 2022 ዳግም ተመርጠዋል።

የዓለም አቀፉ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር የሕግ አማካሪው ሎይክ አልቬስ ሰውዬው ከሥልጣናቸው መታገድ እንዳለባቸው ያምናል።

“እየቀረበበት ያለው የወቀሳና ክስ ክብደት ወዲያውኑ ከሥልጣኑ እንዲታገድ የሚያደርግ ነው። ከምርጫው በፊት ጊዜያዊ ዕግድ መጣል ነበረበት” ይላል።

ሟንጓንጊ የፌግፉት ኃላፊ እንደመሆናቸው በሚመሩት መስክ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ባለማወቃቸው ለያዙት ሥልጣን ብቁ ያልሆኑ ያደርጋቸዋል። አሊያም ብዝበዛውን ለመሸፋፈን በመሞከር ጥፋተኛ ይሆናሉ።

ሰውዬው ዳግም ከተመረጡ ከሦሰት ሳምንት በኋላ የታሰሩ ሲሆን “ታዳጊዎች ላይ የሚፈጸም የወሲባዊ ጥቃት ወንጀሎችን ሪፖርት ባለማድረግ” ተከሰዋል።

'ካፔሎ' ላይ እንደሆነው ግን ፊፋ ሰውዬው ላይ ዕግድ አላስተላለፈም። በዚህም ሳቢያ እስር ቤት ሆነው የፌግፉትን ሥራዎች መምራት ቀጥለው ነበር።

የፊፋ የሕጻናት ደኅንነት ፖሊስ “አባሉ የሆነ ግለሰብ በሌላ አካል ምርመራ የሚደረግበት ከሆነ ከኃላፊነቱ ይታገዳል” ይላል።

የጋቦን የቀድሞ ተጫዋች እና እንደ አውሮፓውኑ በ2014 የጋቦን እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበርን ለመጀመሪያ ጊዜ ያቋቋመው ሬሚ ኤባንጋ እንደ ፓርፊት ንዶንጋ ሁሉ ስለጉዳዩ በግልጽ ከሚያወሩ ጥቂት ዕውቅ እግር ኳሰኞች አንዱ ነው።

በእርግጥ እሱ ብዝበዛ አልደረሰበትም። ሆኖም የዚህ ሰለባ የሆኑ በርካታ ጓደኞች አሉት።

“የአገር ውስጥ የፍትሕ ሥርዓቱ የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት አስሯል። ፊፋ ደግሞ ምንም አላደረግም ነበር። 'ካፔሎ' ላይ እንዳደረጉት እሱ ላይ ለምን አላገዱትም?” ሲል ይጠይቃል።

አክሎም “እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ፌዴሬሽኑን መምራቱን ቀጥሎ ነበር። ይህ ነገር ሌላ ቦታ የተፈጸመ አይመስለኝም” ብሏል።

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2022 ፊፍ 'ካፔሎ' እና ሁለት ሌሎች አሠልጣኞችን እንዲሁም የእግር ኳስ ሊጉ ኃላፊን አግዷል። ሆኖም የፌዴሬሽኑ ኃላፊ አልታገዱም።

በሌላ በኩል የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንዴሬሽን ወይም ካፍ ሟንጓንጊ ጥፋተኝነታቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ ንጹህ እንደሆኑ ይቆጠራሉ ብሎ የነበረ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2022 ለጋቦን ስፖርት ሚኒስትር ፍራንክ ናጉማ በጻፉት ደብዳቤ ኃላፊው ለምን እንደታሰሩ ጠይቆ ነበር።

ከወር በኋላ ደግሞ የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ሞስቴፔ የፌዴሬሽኑን ኃላፊ እስር ቤት ድረስ ሄደው ጠይቀዋቸዋል።

ስድስት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ ሰውዬው የተለቀቁ ሲሆን፣ ይህ ከሆነ ከሦስት ሳምንት በኋላ ደግሞ በ2022 የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ላይ ከካፍ ፕሬዝዳንት ጋር ተቃቅፈው ታይተዋል።

ኢባንጋት፣ ሰውዬው በኳታሩ የዓለም ዋንጫ መጋበዛቸው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አካል በጋቦን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደስተኛ እንደሆነ ሊያመለክት ይችላል ብሏል።

“ያ ግብዣ 'ጥሩ ሥራ ነው የሠራኸው' የሚል አያስመስልም? ይህ የሆነው ወሲባዊ ብዝበዛ ላይ እርምጃ ላልወሰደ አካል ነው” ሲል ይናገራል።

ከዚህም አልፎ፣ ከሦስት ወር በፊት ሟንጓንጊ በካፍ ትልቁ ሥልጣንን በያዘው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው ተመርጠዋል።

ባለፈው ሳምንት በካይሮ በተካሄደው እና ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅ አገር ይፋ በሆበት መድረክ ላይም ታይተዋል።

በጋቦን ያለው የወሲባዊ ብዝብዛ ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከወጣ ሁለት ዓመታት ቢጠጋም ዋና ዋና የፌዴሬሽኑ ሰዎች አሁንም በሥልጣን ላይ ናቸው።

ዕውቁ ጋቦናዊ ተጫዋች ኤባንጋ “ሥርዓቱ እንዲህ እንዲቀጥሉ እንደሚያደርጋቸው አምናለሁ፤ ምክንያቱም ምንም የተለወጠ ነገር የለም” ብሏል።

በርካታ ታዳጊዎች አሁንም አደጋ ላይ ናቸው ብለው የሚሰጉ ብዙዎች እንደሆኑ ሀሳባቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ሰዎች ይናገራሉ።

“ብዝበዛው አሁንም እንደቀጠለ አምናለሁ” ይላል ጁሊያን።

ቢቢሲ በዘገባው የጋቦንን እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ካፍን እንዲሁም ፊፋን በዘገባው አካቷል።

ሁሉም ጠንከር ባሉ ቃላት የሕጻናትን ወሲባዊ ብዝበዛ አውግዘዋል።

የጋቦንን እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና መሪው ሟንጓንጊ የቀረበባቸውን ክስ በሙሉ አስተባብለዋል። ከወሲባዊ ብዝበዛዎች ጋር በተገናኘ ያሉ ጉዳዮች ላይ ተገቢው እርምጃ ተወስዷል ሲሉም አክለዋል።

ፊፋ እና ካፍም የቀረበባቸውን ክስ በሙሉ ውድቅ አድርገዋል። ፊፋ በ2022 የጀመረው ምርመራ አሁንም እንደቀጠለ ጨምረው ገልጸዋል።

ሁለቱም አካላት ምርመራው በፊፋ የምርመራ የሥነ ምግባር መመሪያ እና በሌሎች ሕጎች መሠረት እየተከናወነ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የካፍ ፕሬዝዳንት ሞቴስፔ የጋቦን ጉብኝት ተቋሙ የወሲባዊ ብዝበዛ ለመከላከል ያለውን የማያወላዳ አቋም ለማንጸባረቅ እና ምርመራውን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነውም ብሏል።

ቢቢሲ በአገሪቱ ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ከሥልጣን የወረዱትን የቀድሞው የጋቦን ስፖርት ሚኒስትርን ያነጋገረ ሲሆን፣ “ወሲባዊ ብዝበዛን በተመለከተ ከማንም መረጃ አልደረሰኝም” ሲሉ ራሳቸውን ነጻ አድርገዋል።