የህወሓትና በትግራይ ያሉ ተቃዋሚዎች ውዝግብ

በቅርቡ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በትግራይ ክልል ስለተካሄደው ጦርነት እና ስለ ክልሉ አስተዳደር ላይ በጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ በክልሉ ሁሉን አቀፍ የሽግግር አስተዳደር እንዲቋቋምም ጠይቀዋል።

በክልሉ ሥልጣን ላይ ህወሐት ለዘመናት የበላይ ሆኖ መቆየቱን የሚቃወሙት ሦስቱ ፓርቲዎች ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት)፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ (ውናት) እንዲሁም ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) ናቸው።

እነዚህ ፓርቲዎች ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ጦርነት ለማብቃት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ይካሄዳል በተባለው ድርድር ላይ ህወሓት ትግራይን ወክሎ የመደራደርም ሆነ ክልሉን በብቸኝነት የማስተዳደር ህጋዊምና ሞራላዊ መብት የለውም ይላሉ።

“ህወሓት በጉልበት ከሥልጣን ተወግዷል”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከማዕከላዊው መንግሥት ፖለቲካ የተገፋው ህወሓት፣ በፌደራል መንግሥቱ ተቀባይነት ያላገኘ ክልላዊ ምርጫዎች በማካሄድ ‘የሕዝብ ተቀባይነት’ አግኝቻለሁ በማለት ሥልጣኑን ለማጠናከር የሚያስችለው ሁኔታ ፈጥሮ ነበር።

ነገር ግን በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰን ጦርነት ተከትሎ ህወሓት ከክልላዊ ሥልጣኑ ተወግዶ በሕዝቡ ዘንድ ብዙም ተቀባይነት ያላገኘ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ መሪነት በትግራይ ለአጭር ጊዜ የቆየ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመስርቶ ነበር።

ጦርነቱን ተከትሎ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጅምላ ግድያ፣ ዘረፋ፣ ጾታዊ ጥቃት እና የመሠረተ ልማቶች ውድመት ደርሷል። የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎችም የመብት ተቋማት ለተፈጸሙት ጥፋቶች ህወሓትን ጨምሮ ሁሉንም ተጻራሪ ኃይሎች ተጠያቂ ያደርጋል።

የሳልሳይ ወያነ ትግራይ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ከበደ “በልጆቹና ባለቤቱ፣ በእናቱ እና በእህቶቹ ላይ ግፍና በደል የተፈጸመበት የትግራይ ሕዝብ የታገለው ለሉአላዊነቱ እና ለደኅንነቱ እንጂ ለህወሓት አልነበረም” ይላሉ።

“ህወሓት በሕግ ይሁን በሞራል ከሥልጣን በኃይል ተወግዷል። በዚህ መካከልም ሌላ አስተዳደር ተመስርቶ ነበር። ትግላችን የትግራይን መንግሥትነት መመለስ ነበር” ሲሉ ያስረዳሉ።

የባይቶና ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ክብሮም በርኸ ከመታሰራቸው ከቀናት በፊት ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ህወሓት ከፕሮፓጋንዳ በዘለለ ተገቢውን ወታደራዊ ዝግጅት ባለማድረጉ የትግራይ ሕዝብን ለአደጋ እንዲጋለጥ ስላደረገ ከሕዝቡ ጋር የነበረው ውል ፈርሷል” ይላሉ።

በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በክልሉ ውስጥ ለተፈጸተው ክፈተት ተጠያቂ የሚያደርጉት ህወሓትን ነው።

በትግራይ ሁሉን አሳታፊ አስተዳደርን የመመስረት ጉዳይ

በአዲስ መልክ የተደራጁት የትግራይ ኃይሎች ሰኔ 21/2013 ዓ.ም. ላይ መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የቀድሞ የክልሉ አስተዳደር ወደ ቦታው መመለሱን አስታውቀዋል።

ነገር ግን በትግራይ ሁሉን አሳታፊ አስተዳደር መመስረትን በተመለከተ ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበሩት የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአዲሱ መንግሥት ውስጥ ምንም ቦታና እውቅና አልተሰጣቸውም።

የሦስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊቀመንበሮችን ጨምሮ በርካታ አባሎቻቸው በትጥቅ ትግሉ የተሳተፉ ቢሆንም ህወሓት ግን ከበረሃ ተመልሶ ሥልጣኑን ብቻውን መቆጣጠር ነው የመረጠው ይላሉ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንዳንዶች የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሲጠይቁ ሌሎች ደግሞ ጥምር ክልላዊ ምክር ቤት እንዲቋቋም ጠይቀዋል። ሆኖም ከህወሓት ምንም አይነት አዎንታዊ ምላሽ አላገኙም።

ለአቶ ኃይሉ ከበደ በትግራይ ሁሉን አሳታፊ መንግሥት መመስረት ማለት በሕዝባዊ ተቋማቱ በኩል አዲስና አሳታፊ ሕዝባዊ አስተዳደርን ማወቀር ማለት ነው።

“ሕዝባዊ ትግል ነው ያካሄድነው፤ ስለሆነም ሕዝባዊ መንግሥት መመስረት አለበት የሚል እምነት ነበረን” ይላሉ።

አያይዘውም “እኛ የምንታገለው የትግራይ መንግሥትነት እንዲመለስ እንጂ ህወሓት እንዲመለስና ብቻውን ያለፉትን 30 ዓመታት እንዲደግም አይደለም” በማለት ያስረዳሉ።

የትግራይ ነፃነት አገርነት አላማው አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የትግራይ ነፃነት ፓርቲ (ውናት) ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ደጀን መዝገበ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ “ጥምር መንግሥት መሥርተን በጋራ ለመሥራት ተስፋ አድርገን ነበር” ብለዋል።

ህወሓትን “ህገወጥ” የሚሉት የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ አቋም በመያዝ ባወጡት የጋራ መግለጫ ህወሓትን ያካተተ ሕዝባዊ የሽግግር መንግሥት በክልሉ እንዲመሰረት ጠይቀዋል።

ነገር ግን በአሜሪካ የህወሓት ተወካይ የሆኑት አቶ ዮሐንስ አብረሃ “ከዚህ ቀደም ሕጋዊ ክልላዊ መንግሥት ወደ ቦታው ይመለስ ብለው ሲጠይቁ ቆይተው፣ ዛሬ ደግሞ ተመልሰው የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸው ልክ አይደለም” ብለዋል።

አክለውም “የትግራይ መንግሥትን ሕገወጥ ነው” በማለት መክሰሳቸው፣ ፓርቲዎቹን እሳቸው ‘የጠላት ኃይሎች’ ሲሉ ከሚገልጿቸው አካላት ነጥለው ለማየት እንደሚቸገሩ ገልፀዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ተቃዋሚዎችን “ቀበጦች” ሲሉ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ የወረፏቸው ሲሆን ለዚህ አባባላቸውም ከብዙዎች ዘንድ ጠንካራ ትችት ቀርቦባቸዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ሌሎች የህወሓት ‘ቀንደኛ’ ደጋፊዎች በበኩላቸው ተቃዋሚዎቹን ‘የዐቢይ ተላላኪዎች’ በማለት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል። ‘የሥልጣን ጥመኞች’ ሲሉም የሚከሷቸው አሉ።

ክብሮም በርኸ “ሥልጣን ፈላጊዎች ይሉናል። ሥልጣን ብንፈልግም ሃጢአት አይደለም። እኛ ፖለቲከኞች ነን፤ ምንም የሚያሳፍር ነገር የለውም። ሊያፍሩ የሚገባቸው እነዚያ በመጠቃቀምና በስብስብ ሥልጣን የተቆጣጠሩ ሰዎች ናቸው” ብሏል።

የድርድር እና የውክልና ጥያቄ ጉዳይ

ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲያበቃ በተለይም በአሜሪካ፣ በኬንያ እና በአፍሪካ ኅብረት የሚመሩ የድርድር ጥረቶች እየተሞከሩ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ተደራዳሪ ኮሚቴ መሰየሙን አስታውቀዋል። የህወሓት መሪዎችም በኬንያ መንግሥት ለሚመራ ውይይት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ተደራዳሪዎቻቸውን ግን እስካሁን ይፋ አላደረጉም።

ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነት ብዙዎች በሰላማዊ መንገድ ይፈታ ይሆን በሚል ተስፋ ቢያደርጉም ሌሎች ደግሞ “ጊዜ መግዣ ነው” የሚል ጥርጣሪ አላቸው።

በሰሜን አሜሪካ የህወሓት ተወካይ አቶ ዮሐንስ አብረሃ “በእኛ በኩል በውይይት መፍትሄ ሊመጣ ይችላል ብለን እናምናለን” በማለት ከሌላኛው ወገን በኩል ግን ጥርጣሬ እንዳላቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ኃይሉ ከበደ ግን “የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንዴ ፈርሷል። ለቀጣይ አቅጣጫም መነሻ ሊሆን አይችልም። የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ሊያስከብር አይችልም። በእሱ ተደራድረን የምናሳካው ጥቅምም የለም” ይላሉ።

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹም ከዚህ በመነሳት ነው ህወሓት የመደራደር ውክልና የለውም በማለት “የትግራይን ሕዝብ ለዚህ ውርደት አጋልጦ ትንሽ መፀፀት ያስፈልግ ነበር። እነዚህ ግን በድርቅና አድራጊ ፈጣሪ እኛ ነን እያሉ ነው” በማለት አቶ ኃይሉ ህወሓትን ይወቅሳሉ።

ዶ/ር ደጀን በበኩላቸው ይህንን ተቃዋሚዎች አለ የሚሉትን የሕግ ክፍተት በመጥቀስ “ህወሓት ብቻውን ለመደራደርም ሆነ ትግራይን ለመምራት ምንም አይነት የሕግ መሰረት የለውም” ሲሉ ይቃወማሉ።

ይህን ያሉበት ምክንያት ሲያስረዱም “በየትኛው ሕግ ነው ሠራዊት ሊገነባ እና ዲፕሎማሲን ማስቀጠል የሚችለው?” በማለት በሕገ መንግሥቱ መሰረት እነዚህ የፌደራል መንግሥት ተግባራት መሆናቸውን ያስታውሳሉ።

አክለውም “ከሕገ መንግሥቱ ውጪ የሆነ ኃላፊነት የያዘ መንግሥት አለ። ይህን መስራት የሚችል ኃላፊነት ያለው ፓርቲ የለም።። የወደፊት የትግራይ ዕጣ ለዘላለም ብቻውን እንዲወስን የተመረጠ ፓርቲ የለም። የህወሓት ስርወ መንግሥትንም ለመመስረት የመረጠ ሕዝብም የለም” ይላሉ።

“ህወሓት ለረጅም ጊዜ በሥልጣን ላይ ቆይቷል ለማለት ከሆነ ይገባኛል” በማለት የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ ነገር ግን ፓርቲው በሕግ አግባብ መመረጡን ይጠቅሳሉ።

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በመላ ትግራይ ተንቀሳቅሰው የህዝቡን ቀልብ መሳብ የሚችሉበትን ሁኔታ ፈጥረው፣ ሕዝቡ ህወሓትን በቃህ የሚለው ከሆነ የሕዝቡን ፍላጎት እንደሚያከብሩ አቶ ዮሐንስ ያስዳሉ።

ነገር ግን ፓርቲዎቹ ሕዝባዊ ስብሰባ እንኳን እንዳያካሂዱ መከልከላቸውን እና እንቅስቃሴያቸውም መገደቡን በማስመልከት ስለሚያርቡት አቤቱታ ከቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ዮሐንስ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሌላችው በመግለጽ “እንደዚያ የተደረገ ግን አይመስለኝም” ብለዋል።

የአዲሱ ውል ጥያቄ ምንድን ነው?

የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህወሓት ጋር በጋራ ለመሥራት ‘የፓርቲዎች የጋራ መድረክ’ ተቋቁሞ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በጋራ መወያየት ጀምረው እንደነበረ ያስታውሳሉ።

“የፓርቲዎች ፎረምን የልጆች መጫወቻ አድርገውታል” የሚሉት አቶ ኃይሉ ከበደ፣ ህወሓት ሲፈልግ ብቻ እንደሚሰበሰቡና ወታደራዊ ድሎች ሲገኙ ግን እንደሚረሱ ጠቅሰዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ግን የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ከስምንት ጊዜ በላይ ከዶ/ር ደብረፂዮን ጋር መወያየታቸውን በማኅበራዊ ሚድያ ጽሁፋቸው ላይ አስፍረው ነበር።

አቶ ኃይሉ ከበደ ግን “ከኅዳር ወር በኋላ ‘መከበብና መዘጋት’ ወደ ሚለው ግልፅ ወዳልሆነ ፖለቲካ ገባን። የትግራይ ሕዝብ እየጠፋና እየረገፈ ነው። በህወሓት ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ ሥራ መሥራት አልተቻለም። የትግራይ ሕዝብ ትግል ዲፕሎማሲያዊ አጋር አላገኘም” ይላል።

ተቃዋሚዎቹ ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ምክያት ሕገ መንግሥቱ በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ ፈርሷል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

የህወሓት ተወካይ አቶ ዮሐንስ ግን “ሕገ መንግሥቱ ፈርሷል ካልን እነሱስ በየትኛው አሰራር ነው ሕጋዊ ተቃዋሚ የሆኑት?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

“ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ነው ያጋጠመው” የሚለው ፖለቲከኛ ክብሮም በርኸ በበኩሉ አዲስ ውል ማሰር እንደሚያስፈልግ ያምናል።

"ለዓላማችን ስንል ሠራዊት ልንገነባና ዲፕሎማሲ መሥራት ስላለብን የሕግ ክፍተቱን ለመሙላት ፓርቲዎችና ሌሎች ግለሰቦች የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ ሊኖር ይገባል” ይላሉ ዶክተር ደጀን በበኩላቸው።

ህወሓት ምን ይላል?

በአሜሪካ የህወሓት ተወካይ የሆኑት አቶ ዮሐንስ አብርሃ “ሕገ መንግሥቱ ተሸራርፏል እንጂ ፈርሷል” ብለው እንደማያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ሕገ መንግሥቱ ፈርሷል ካልን ያለሱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለመንቀሳቀስ ይከብደናል” ሲሉም ይሞግታሉ።

“አሁን የሽግግር መንግሥት ቢቋቋም ተቃዋሚ ኃይሎቹ ከድርጊታቸው ይቆጠቡ ነበር?” የሚል ጥያቄ በማንሳትም የቀረበው ሐሳብ መፍትሔ እንደማያመጣ ይናገራሉ።

የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ እና ሌሎች የትግራይን ሕዝብ ዕጣ ፈንታን ሊወስኑ የሚችሉ ሁኔታዎች ሕገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ ሊፈቱ እንደሚችሉ ነው የሚያምኑት።

እሳቸው ይህን ቢሉም፣ ተቃዋሚዎቹ ግን በአንድ ድምፅ “ህወሓት በኢትዮጵያ ውስጥ መኖርን ነው የሚመርጠው። ከሕዝባችን የነፃነት ምኞት ጋር አልተስማማም” በማለት ይከሱታል።

‘ሕዝበ ውሳኔ’ የሚለው ቃልም ማደናገሪያና በተደጋጋሚ የትግራይን ህዝብ ጥቅም አሳልፎ የሰጠ መሆኑን ይገልፃሉ።።

ይህንን ክስ የማይቀበሉት አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው “የእኛ ምርጫ የሕዝባችን ውሳኔ ነው የሚሆነው። ሕዝባችን ምን እንደሚፈልግ ለመወቅም ለድርድር የማይቀርብ መድረክ እናዘጋጃለን” ብለዋል።

የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ዙሪያ በአሁኑ ወቅት የህወሓት አቋሙ ምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ዮሐንስ፣ ፓርቲው በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ ካካሄደ በኋላ ግልጽ እንደሚሆን ተናግረዋል።