ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“የኤርትራ ወታደሮችን ከትግራይ እንዲወጡ መጠየቅ የሚችለው የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ነው” የኤርትራ አምባሳደር
የኤርትራን ሠራዊት ከትግራይ እንዲወጣ መጠየቅ የሚችለው ሌላ ማንም ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ነው ሲሉ በሩሲያ የኤርትራ አምባሳደር ተናገሩ።
አምባሳደር ጴጥሮስ ፀጋይ ይህንን ያሉት ከሩሲያ መንግሥት የዜና ተቋም ከሆነው አርአይኤ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ሲሆን፣ አሜሪካ የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከትግራይ እንዲወጡ መጠየቋን በመቃወም ይህንን ማለት የሚችለው የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ሠራዊት ጎን በመሰለፍ በውጊያዎች መሳተፋቸውና በተለያዩ የመብት ጥሰቶች ሲከሰሱ ቆይተዋል።
በዚህም ሳቢያ አሜሪካ፣ የተለያዩ ምዕራባውያን አገራት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ ክልል ውስጥ እነድታስወጣ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
እንዲሁም ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በተደረሰው ስምምነት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ እና የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ መስማማታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ስላለው ሁኔታ በዜና ተቋሙ የተጠየቁት በሩሲያ የኤርትራ አምባሳደር ጰጥሮስ ፀጋይ “በአሁኑ ወቅት አማጺያኑ ተዳክመው ምንም ማድረግ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ቢገኙም፣ ፖለቲካዊ ድጋፍ ግን አላቸው” ብለዋል።
በተካሄደው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት የበላይነት ማግኘቱን የጠቀሱት አምባሳደሩ “የኢትዮጵያ ድል የእኛም ድል ነው” በማለት በጦርነቱ ሂደት ተይዞባቸው የነበሩ ግዛቶችን ማስመለሳቸውን ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር በትግራይ ውስጥ የተሰማሩትን የኤርትራ ወታደሮችን በተመለከተ ከአሜሪካ እና ከተለያዩ ወገኖች እንዲወጡ የሚቀርበውን ጥያቄ ያጣጣሉት አምባሳደሩ ግዛቱ የኢትዮጵያ ስለሆነ ጥያቄው መምጣት ያለበት ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ነው ብለዋል።
“ወታደሮቻችን እዚያ ካሉ፣ ለቀው እንዲወጡ መጠየቅ ያለባቸው አሜሪካኖች ሳይሆኑ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጋር ግንኙነት ስላለን ኢትዮጵያ ናት ያንን ማድረግ የምትችለው።”
አምባሳደሩ በተጨማሪም አሜሪካ ለትግራይ አማጺያን ድጋፍ እንደምትሰጥ በመግለጽ በአካባቢው እያሳደረችው ያለው ተጽእኖ ጦርነቱ መልሶ እንዲያገረሽ ሊያደርግ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
በህወሓት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በድንበር ይገባኛል ምክንያት በአስር ሺዎች ያለቁበት ጦርነት ያደረጉት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለ20 ዓመታት በፍጥጫ ውስጥ መቆየታቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በወሰዱት ወሳኝ እርምጃ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በአጭር ጊዜ ተሻሽሎ በትግራይ ውስጥ በተደረገው ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት የፌደራል መንግሥቱን በመደገፍ ተሰልፎ ቆይቷል።
የሁለት ዓመቱን የእርስ በርስ ጦርነት ያስቆመው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል እንደሚወጣ የተነገረ ሲሆን፣ ከሳምንት በፊትም ወታደሮቹ ከአንዳንድ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች መስማቱን መዘገቡ ይታወሳል።
ነገር ግን ባለፈው ሳምንት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች አሁንም የኤርትራ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኤርትራ ወታደሮች እና የፌደራል መንግሥቱ ያልሆኑ ኃይሎች መውጣት ከህወሓት ኃይሎች ትጥቅ መፍታት ጋር ጎን ለጎን እንደሚከናወን የተገለጸ ቢሆንም ስለተግባራዊነቱ የተባለ ነገር የለም።