ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ ወሰነ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ የብድር መጠንን መገደብን ጨምሮ የዋጋ ንረቱን ሊያረጋጉ የሚችሉ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑን አስታወቀ።
ለረጅም ጊዜ በአገሪቱ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረውን የዋጋ ንረትም በወሳኝ እና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ሊቀንሱ የሚችሉ በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ እና ተፈጻሚ እንዲሆኑ መወሰኑን የባንኩ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ዛሬ አርብ ነሐሴ 05/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ30 በመቶ በላይ በመሆን የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት መሠረታዊ ፈተና የሆነውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ማሻሻያዎች እንዲደረጉም ወስኗል።
በባለፉት ሁለት ዓመታት ኮቪድ፣ ግጭትን እና ድርቅ፣ የመንግሥት ገቢ ማነስ እና የወጪ ጫና መብዛት በመሳሰሉ ምክንያቶች የተነሳ የአገሪቱ የገንዘብ ችግሮች ሰፍተውና ጎልተው መታየታቸውን የብሔራዊ ባንኩ ገዢ ገልጸዋል።
በዚህም ምከንያት የመንግሥት የበጀት ጉድለት መጨመሩ እንዲሁም የውጭ ብድር እና እርዳታ ውስን ከመሆኑ ጋር ተያይዞም አብዛኛው የበጀት ጉድለት ከአገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮች በሚገኝ ብድር መሸፈን ግዴታ መሆኑም ተገልጿል።
አቶ ማሞ እንደተናገሩት መንግሥት ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማመጣጠን እና የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በ2016 ዓመት የበጀት ጉድለትን የሚገድብ መሠረታዊ አቋም ይዟል። ይህም ማለት የመንግሥት ወጪ እድገት እንዲገደብ፣ የበጀት ጉድለቱን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ እንዲቀንስ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህ እርምጃም መንግሥት ከአገር ውስጥ ባንኮች በተለይም ከማዕከላዊ ባንክ የሚወስደውን የብድር መጠን እንዲቀንስ እንደሚያደርገው ነው አቶ ማሞ ያስረዱት።
ባለፈው ዓመት የብድር እድገት ዋጋ የማረጋጋት ጥረት ውስንነት ታይቶበታል ያሉት አቶ ማሞ፣ በዚህም ምክንያት በዘንድሮው በጀት ዓመት ለመንግሥትም ሆነ ለግሉ ዘርፍ በሚሰጠው ብድር ላይ ገደብ ለማስቀመጥ ተወስኗል።
የዋጋ ንረትን ያረግባሉ የተባሉ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች
- ባንኩ የዋጋ ንረትን በ2016 በጀት ዓት ሰኔ መጨረሻ ላይ ከ20 በመቶ በታች የማውረድ፣ በ2017 ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ አጠቃላይ ግብ ይዞ እንደሚሠራም አቅዷል።
- በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የአገር ውስጥ ብድር እድገት በ14 በመቶ ጣሪያ ይገደባል። ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲያስተካክሉ ይደረጋል።
- በያዝነው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ የብድር መጠን በእጅጉ በመቀነስ ባለፈው ዓመት ከተሰጠው ብድር 1/3ኛ እንዳይበልጥ እና መሠረታዊ በሆነ መልኩ እንዲገደብ ይደረጋል።
- የገንዘብ ሚኒስቴር ቀጥታ ብድርን እንደ መጨረሻ አማራጭ የሚጠቀመው የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ በበቂ መጠን ለገበያ መቅረብ ሳይችል ሲቀር ብቻ እንዲሆን መግባባት ላይ መደረሱም ተገልጿል።
- ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ ብድር ላይ የሚከፍሉት የወለድ መጠን ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል።
- ቁልፍ በሆኑ የውጭ ንግድ ዘርፎች በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ላኪዎችን ለማበረታት የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ (forex surrender requirement) ከ70/30 ወደ 50/50 ቀመር እንዲሻሻል ይደረጋል።በዚህም መሰረት የሸቀጦች እና የአገልግሎት ላኪዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሬ ገቢ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ፣ 10 በመቶውን ለባንካቸው ያስተላልፋሉ። ቀሪውን በራሳቸው የባንክ ሂሳብ እንዲያስገቡ መፈቀዱም ተገልጿል።
የዋጋ ንረትን ለማርገብ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ ለምን አስፈለገ? የሚለውን አንስተው ያብራሩት አቶ ማሞ ምህረቱ የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመቀነስ፣ ቁጠባ እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታት እንዲሁም የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሆነም ገልጸዋል።
የዋጋ ንረት ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ ከባድ እና ለረጅም ጊዜ ከዘለቁ የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎች አንዱ ሲሆን፣ በመላው ሕብረተሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ሸክም ሆኖ ቆይቷል።
ባለፉት አስር ዓመታት የዋጋ ንረት በአማካይ በየዓመቱ 16 በመቶ ጭማሪ እያሳየ እንደነበር የገለጹት የብሔራዊ ባንኩ ገዢ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ከ30 በመቶ በላይ ሆኖ ቆይቷል።
በሰኔ ወር የተመዘገበው የዋጋ ንረት 29.3 ዓመታዊ እድገት ያሳየ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ30 በመቶ በላይ ሆኖ ከቆየው የዋጋ ንረት በተለይም አምና በተመሳሳይ ወቅት በከፍተኛነቱ የተመዘገበው የ34 በመቶ እድገት አንጻር መጠነኛ መሻሻል አሳይቷል ተብሏል።
በተጨማሪም ምግብ ነክ የዋጋ ንረት ባለፈው ዓመት ከነበረበት 38 በመቶ በዘንድሮው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ወደ 28 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
ይህ መሻሻል አበረታች እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ማሞ፣ የዋጋ ንረት ጊዜ የማይሰጠው እና ተጨማሪ ሥራን የሚጠይቅ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
“ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከማክሮ ኢኮኖሚም ሆነ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ቋሚ ገቢ ባላቸው እና በድሃው ሕብረተሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከሚያሳድረው አሉታዊ ተፅእኖ አንጻር በርካታ የከፉ ጉዳቶች አሉት” ብለዋል።
የዋጋ ንረት ለረጅም ጊዜ በቆየ ቁጥር አሁን በኢትዮጵያ እንዳለው ስር የሰደደ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስጋት እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ተከሰተው የዋጋ ንረት መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው?
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ሆነ በሌሎች አካላት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ዋነኞቹ ምክንያቶች የአቅርቦት ውስንነት፣ የማምረቻ ወጪ መናር እና ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች በተለይም የገንዘብ እና የፊሲካል ፖሊሲዎች አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው አቶ ማሞ የተናገሩት።
ለምሳሌም ያህል በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ጦርነቶች ግብርና እና የግብር ነክ ምርቶችን ሥርጭትን አስተጓጉለዋል።
በተጨማሪም በዓለም ገበያ የሸቀጦች በተለይም የነዳጅ፣ የማዳበሪያ እና የትራንስፖርት ዋጋ መናርንም ጠቅሰዋል።
በአውሮፓውያኑ ከ2020 አጋማሽ እስከ 2022 አጋማሽ ድረስ ብቻ የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ 40 በመቶ፣ የማዳበሪያ ዋጋ 200 በመቶ እንዲሁም የትራንስፖርት ዋጋ በ300 በመቶ ጭማሪ በማሳየቱ የኢትዮጵያ የዋጋ ንረትን ካባባሱ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀስ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
እንዲሁም ኮቪድ፣ ግጭት እና ድርቅ የመሳሰሉ ውስጣዊ ችግሮችን ለመቋቋም የተወሰዱ ከወትሮው ላላ ያሉ የገንዘብ እና ፊሲካል ፖሊሲዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ለተከሰተው የዋጋ ንረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
ለዋጋ ንረት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ከመኖራቸው አንጻር የኢትዮጵያን የዋጋ ንረት ለመፍታት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዋጋን ለማረጋጋት መወሰድ የሚገባቸው ከገንዘብ ማሻሻያ በተጨማሪ ሌሎች እርምጃዎችንም አቶ ማሞ ምህረቱ ጠቅሰዋል።
ከጠቀሷቸው የአቅርቦት እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ውስጥ፡
- የአቅርቦት ማሻሻያ እርምጃዎች መውሰድ፦ በሸማቾች የዋጋ ኢንዴክስ የ54 በመቶ ድርሻ ያለውን ምግብ ነክ የዋጋ ንረት ለመቀነስ የግብርና ምርቶችን ትርጉም ባለው መልኩ ማሳደግ እና ምርታማነትን መጨመር ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል። በዚህም ረገድ የሚታረሰውን መሬት ስፋት መጨመር፣ የመስኖ እርሻን ለመጨመር ኩታ ገጠም እርሻን እና የከተማ ግብርናን ማጎልበት እና ማበረታትን እንደ ምሳሌ ከተጠቀሷቸው መካከል ናቸው።
- ሁነኛ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ፡ የትራንስፖርት አውታሮችን፣ የሎጂስቲክ ሥርዓቶችን የንግድ ተወዳዳሪነትን በሚያግዙ መልኩ ለማሻሸል መዋቅራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ለዋጋው መረጋጋት አስተዋጽኦ እንዳለው አቶ ማሞ አስረድተዋል። እንደ ምሳሌ ያነሱት ይህ ማሻሻያ የአቅርቦት ሰንሰለትን ለማሳለጥ እና ተወዳዳሪ የምርት ገበያ ለመፍጠር የሚያግዙ እና በሂደትም የዋጋ ጫናን ለማርገብ እንደሚያግዙ በማስረዳት ነው።