ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዲስ የብሔራዊ ባንክ ገዢ እና ሚኒስትሮችን ሾሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይናገር ደሴን (ዶ/ር) አንስተው አቶ ማሞ ምህረቱን የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አድርገው መሾማቸውን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በተሸኙት ሚኒስትሮች ቦታም አዳዲስ ሚኒስትሮችን መሾማቸውን ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ምክንያታቸው ባልተገለጸ ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባልነት የተሰናበቱትን አራት ሚኒስትሮችን ከሚተኩት ባለሥልጣናት በተጨማሪም ለብሔራዊ ባንክ አዲስ አስተዳዳሪ ተሹሞለታል።

ነገር ግን እንደቀደሙት ሁሉ የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይነገር ደሴ (ዶ/ር) በፈቃዳቸው ቦታቸውን ይልቀቁ፣ ከባንኩ ገዢነት በመንግሥት ይነሱ ወይም ወደ ሌላ ኃላፊነት ይሾሙ የተባለ ነገር የለም።

አዲስ የብሔራዊ ባንክ ገዢ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾመው አገሪቱ ብር የመግዛት አቅም በተለያዩ ምክንያቶች ክፉኛ እየተፈተነበት ባለበት፣ በብር እና በዶላር መካከል ያለው የምንዛሪ መጠን እየሰፋ በመጣበት ወቅት ነው።

ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው ተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከወራት በኋላ በ2011 ዓ.ም ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የብሔራዊ ባንክ ገዢ የሾሙት አገሪቱ ከከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ጋር እየታገለችበት ባለችበት ጊዜ ነው። ዓመታዊው የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ20 በመቶ በላይ ሲሆን ባለፈው ዓመት ደግሞ ከ33 በመቶ በላይ ነበረ።

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማን ናቸው?

ከጥር 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው የተሾሙት አቶ ማሞ ምህረቱ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ በ100 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ግዙፎቹን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ኢትዮቴሌኮምን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በማካተት በተለያዩ የኢነቨስትመንት ዝርፎች ላይ የተሰማራ ነው።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመንግሥት ሀብትን የማስተዳደር እና የውጭ መዋዕለ ነዋይን የመሳብ ሥራን የሚያከናውን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራ ተቋም ነው።

አቶ ማሞ ቀደም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት አማካሪ እና የንግድ ጉዳዮች ተደራዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ ከዚያ በፊት ደግሞ በዓለም ባንክ ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት ሰርተዋል።

አቶ ማሞ ምህረቱ በትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሕግ ዲግሪ፣ ከኔዘርላንድስ አምስተርዳም ዩኒቨርስቲ በዓለም አቀፍ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማ እንዲሁም በሕዝብ አስተዳደር ከሃርቫርድ የሥነ መንግሥት ትምህርት ቤት የሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።

ሌሎች ሹመቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ አርብ ጥር 12/2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረጉት የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሹመት ሚኒስትሮች እና በተለያዩ ዘርፎች አማካሪዎቻቸውን አሳውቀዋል።

ቀደም ሲል በወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ተይዞ የነበረውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትርነት ቦታን ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ በአቶ ታከለ ኡማ ቦታ የማዕድን ሚኒስትር እንዲሆኑ አቶ ሀብታሙ ተገኝ እንዲሁም በአቶ ኡመር ሁሴን ተይዞ የነበረውን የግብርና ሚኒስትርነት ዶ/ር ግርማ አመንቴ እንዲሆኑ በመሾም የተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቀው መጠየቃቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም አቶ ማሞ ምህረቱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ፣ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር እና አቶ መለሰ አለሙ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ የዘርፍ አስተባባሪ ሆነው ተሹመዋል

እንዲሁም ወ/ሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር መሆናቸው ተገልጿል።