ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰሜን ለንደን ደርቢ፡ ቶተንሀም ወይስ አርሰናል? የሱተን ግምት ምን ይላል?
አርሰናል ከዴክለን ራይስ እና ማርቲን ኦዴጋርድ ውጭ ነው ቶተንሀም የሚጓዙት። ነገር ግን የሁለቱ ተጨዋቾች አለመኖር የሰሜን ለንደን ደርቢ ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዴት ያለ ነው?
“ራይስ የለም. . . ኦዴጋርድ የለም. . . ማሸነፍም የለም” ይላል የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን።
የሰሜን ለንደን ደርቢ እሑድ ከሰዓት 10፡00 ይደረጋል።
የዘንድሮውን ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች የሚገምተው ሱተን የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ትንበያ እንዲህ አስቀምጧል።
ቅዳሜ
ሳውዝአምፕተን ከማን. ዩናይትድ
ሳውዝአምፕተን ሶስት ጨዋታዎች አድርገው ሶስቱን ተሸንፈዋል። ከሻምፒዮንሺፕ አድጎ የመጣው ክለብ በፕሪሚዬር ሊጉ ሕይወት የከበደው ይመስላል። ከኋላ ኳስ መስርተው ለመጫወት የሚያደርጉት ሙከራም ትችት እየገጠመው ነው።
ባለፈው ሳምንት ከብሬንትፈርድ በነበራቸው ጨዋታ ስህተት በመሥራታቸው ጎል ሊቆጠርባቸው ችሏል።
ቅዳሜ ከማንቸስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት ፍልሚያም ቀላል አይሆንላቸውም። የኤሪክ ቴን ሀግ ቡድን የራሱ ችግር ቢኖርበትም ለዚህ ጨዋታ የሚሆን የጥራት ጥልቀት ግን አለው።
ግምት፡ 0 - 2
ውጤት፡ 0 - 3
ብራይተን ከኢፕስዊች
ሰዎች እኔ የኢፕስዊች ጠላት እንደሆንኩ ነው የሚያስቡት። ይህ ፍፁም ስኅተት ነው። አሰልጣኝ ኪየራን ማኬና እያደረገ ያለው ነገር መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።
ከዓለም አቀፍ ጨዋታዎች እረፍት በፊት ከፉልሀም ጋር ነጥብ መጋራት ችለዋል። አሁንም ቢሆን ከፕሪሚዬር ሊጉ ይወርዳሉ የሚለው ግምቴን አልተውም።
ኢፕስዊች ወደ ብራይተን ሜዳ ተጉዘው ምንም ነገር ይዘው ይመጣሉ ብዬ አልጠብቅም፤ ምክንያቱም ብራይተን ጥሩ ግስጋሴ ላይ ያለ ክለብ ነውና።
ግምት፡ 3 - 1
ውጤት፡ 0 - 0
ክሪስታል ፓላስ ከሌስተር
ክሪስታል ፓላስ በዘንድሮው የፕሪሚዬር ሊግ ውድድር አጀማመራቸው ቀዝቃዛ። የሚያበሳጭ ነው ብልም የሚያንሰው አይደለም። ነገር ግን የመጀመሪያ ድላቸውን ሩቅ ብዬ አላስብም።
ከሌስተር ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ የመጀመሪያ ድላቸውን ያጣጥማሉ ብዬ እገምታለሁ። ቀበሮዎቹ ሌስተሮች ወደፊት ከባድ ጊዜ ይጠብቃቸዋል የሚል ግምት አለኝ።
ግምት፡ 2 - 1
ውጤት፡ 2 - 2
ፉልሀም ከዌስት ሀም
ይህን ጨዋታ መገመት ቀላል አይደለም። እንዲህ ዓይነት ጨዋታዎች ናቸው በየሳምንቱ ግምቴ ስኅተት እንዲሆን የሚያደርጉት።
ፉልሀም መልካም አቋም ላይ ነው፤ ጨዋታውም ደስ ይላል። ዌስት ሀም በተመሳሳይ አቋሙ ጥሩ የሚባል ነው። መዶሻዎቹ ከሲቲ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ቢሸነፉም የጉዋርዲዮላን ቡድን መፈተን ችለዋል።
ሁለቱም ቡድኖች የጎል ዕድሎችን ይፈጥራሉ ብዬ እገምታለሁ። ነገር ግን ይህ ጨዋታ በመሸናነፍ ይጠናቀቃል ብዬ አላስብም።
ግምት፡ 1 - 1
ውጤት፡ 1 - 1
ሊቨርፑል ከኖቲንግሀም ፎረስት
የአርን ስሎት ሊቨርፑል እስካሁን ጎል አልተቆጠረባቸውም። ብዙ የጎል ሙከራም እየተደረገባቸው አይደለም። እንደዚህም ሆኖ ወደፊት ሲሄዱ ያስፈራሉ፤ ዩናይትድን በሜዳው መርታትም ችለዋል።
የኖቲንግሀሙ አጥቂ ክሪስ ዉድ ጎል እያስቆጠረ ቢሆንም አንፊልድ ላይ ይሳካለታል የሚል ግምት የለኝም። የኖቲንግሀም ዕቅድ መከላከል ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ብገምትም አይሳካላቸውም። ሞሐመድ ሳላህ ያስቆጥራል፤ አርን ስሎትም ያሸንፋሉ።
ግምት፡ 2 - 0
ውጤት፡ 0 - 1
ማን. ሲቲ ከብሬንትፈርድ
ብሬንትፈርድ ማንቸስተር ሲቲን ግራ ከሚያጋቡ ቡድኖች መካከል ነው። በ2022-23 የውድድር ዘመን ብሬንትፈርድ በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ ሲቲን መርታቱ አይዘነጋም።
ነገር ግን ዘንድሮ ይህ ይደገማል የሚል ግምት የለኝም። የሚያስቆመው ያልተገኘው ኧርሊንግ ሀላንድ እና ሲቲ ይህን ጨዋታ ያሸንፋሉ ብዬ እገምታለሁ።
ግምት፡ 3 - 1
ውጤት፡ 2 - 1
አስተን ቪላ ከኤቨርተን
የኤቨርተኑ አሰልጣኝ ሾን ዳይሽ ቡድናቸው 2 ለምንም ከመመራት ተነስቶ በቦርንመዝ 3-2 መሸነፉ ብዙ ትችት እንዲያስተናግዱ አድርገቸዋል። ዳይሽ ውጤት ይፈልጋል። ነገር ግን እንዳመታደል ሆኖ ቪላ ፓርክ ሄዶ ይህን ማሳካት ይችላል አልልም።
ኤቨርተን ባለፈው የውድድር ዘመን በቪላ ሜዳ 4 ለምንም ነው የተረመረሙት። ምንም እንኳ ውጤት ለማግኘት ይፋለማሉ ብዬ ባስብም የሚሳካላቸው ግን አይመስለኝም።
ግምት፡ 2 - 0
ውጤት፡ 3 - 2
ቦርንመዝ ከቼልሲ
ቦርንመዝ በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስካሁን ሽንፈት አላስተናገዱም። ኤቨርተን ሄደው ወሳኝ እና አስገራሚ ድል ይዘው መጥተዋል።
ስለቼልሲ ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም። ኮል ፓልመር ለዚህ ጨዋታ ይድረስ አይድረስም የሚታወቅ ነገር የለም። በዚህ ምክንያት ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል የሚል ግምት ነው የማስቀምጠው።
ቼልሲ፡ 1 - 1
ውጤት፡ 0 - 1
እሑድ
ቶተንሀም ከአርሰናል
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ኮንትራታቸውን አራዝመዋል። ነገር ግን ወደ ሰሜን ለንደን ደርቢ የሚጓዙት ወሳኝ የሚባሉ ሁለት ተጫዋቾቻቸውን ትተው ነው።
ማርቲን ኦዴጋርድ በጉዳት ዴክለን ራይስ ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም። ምንም እንኳ እንደ ጆርጊንሆ እና ቶማስ ፓርቴ ያሉ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች መሐል ሜዳውን ሊቆጣጠሩ ቢችሉም ራይስ እና ኦዴጋርድ አለመኖራቸው ጉዳት ነው።
መድፈኞቹ በዚህ ጨዋታ የጎል ዕድል እንደሚፈጥሩና ሊያስቆጥሩም እንደሚችሉ እገምታለሁ። ነገር ግን ግምቴ ለስፐርስ ያደላ ነው።
የአንጅ ፖስቴኮግሉ ቡድን በያዝነው የውድድር ዘመን የጎል ዕድል እየፈጠረ ነው። በዚህኛው የሰሜን ለንደን ደርቢ ቶተንሀም ሆትስፐርስ እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።
ግምት፡ 3 - 2
ዎልቭስ ከኒውካስል
ምንም እንኳ ኒውካስል ዘንድሮ ሽንፈት ባይቀምስም አጨዋወታቸው ብዙም የልብ ልብ የሚሰጥ አይደለም።
ዎልቭስ ደግሞ ድል አልቀናቸውም። ብዙ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ከመረብ የማገናኘት ችግር አለባቸው። ይህ ጨዋታ ለኒውካስል ወይስ ለዎልቭስ የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው።
ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ነው የኔ ግምት።
ግምት፡ 1 - 1