ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቲክቶከሮች ለምን ያለቅሳሉ? ከምራቸው ነው? ለምንስ አሳዛኝ ይዘት የበለጠ ይመርጣሉ?
ሰዎች ማዘን አንሻም ቢሉም በበይነ መረብ ላይ የሚከታተሏቸው ይዘቶች ግን አሳዛኝ ናቸው።
መንግሥት ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት ወይም የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ለመፍጠር አሊያም ምርት እና አገልግሎትን ለመሸጥ በሚል ሰዎች ላይ ስሜት ለመፍጠር ይሞከራል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታይን ቁጥር ለመጨመርም ይህን መንገድ የሚከተሉ ብዙ ናቸው።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን በማስቆጣት የተሻለ ዕይታ ለማግኘት ይሞክራሉ።
አንድ ይዘት ሲለጠፍ ሰዎች ለይዘቱ ምላሽ እንዲሰጡ ስሜታቸውን መኮርኮር ያሻል። ይህም ቁጣን በመቀስቀስ የሚደረግ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጠራ ሬጅባይት (Ragebait) በሚል ስም ይጠራል።
ይህም ፖለቲካዊ መካረርን ከሚፈጥሩ ነገሮች መካከል ይጠቀሰል።
ሐዘኔታን በመቀስቀስ የሚደረግ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጠራ ደግሞ ሳድባይት (sadbait) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ራሳቸውን ሲያለቅሱ ይቀርጻሉ።
በአውሮፓውያኑ 2024 ቲክቶከሮች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ያገኙት በጣም የሚያሳዝን ሙዚቃ፣ ፊልም እና ዜና አልጋቸው ላይ ሆነው ሲመለከቱ የሚያሳይ ነው።
ሰዎች በባህሪያቸው ሐዘንን ማስወገድ ነው የሚፈልጉት። ግን ሳድባይት የተባለውን የሐዘን ይዘት የሚከታተሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
በፊንላንድ በታምፕሬ ዩኒቨርስቲ አጥኚዋ ሶማ ባሱ "ቁጣ፣ ሐዘን፣ መጸየፍ ወይም ሳቅን የመሰሉ ጠንካራ ስሜቶች ትኩረትን ይስባሉ" ትላለች።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካሉት በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ይዘቶች መካከል አንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ የእሱ ወይም የእሷ ጎልቶ እንዲታይ ጥረት ማድረግ ግዴታቸው ነው።
አንድ ይዘት ላይ ቆይታ እንዲያደርጉ ሰዎችን ከሚገፋፉ ነገሮች መካከል አንደኛው ስሜት እንደሆነ አጥኚ እና የምርመራ ጋዜጠኛዋ ሶማ ታስረዳለች።
አሳዛኝ ድመቶችን ከአሳዛኝ ሙዚቃ ጋር በማጣመር በቲክቶክ እና በኢንስታግራም ላይ መለጠፍ ሌላው መንገድ ነው።
ሳድባይት ሲሠራ ጥቅም ላይ የሚውለው ምሥል ወይም ቪድዮ የሰዎች ላይሆን ይችላል። በሰው ሠራሽ አስተውሎች የተዘጋጁ የተጎዱ ወታደሮች፣ የተራቡ ሕጻናት እና ሌሎችም ምሥሎች ተለቀው በርካታ ተመልካች አግኝተዋል።
በአሜሪካ አንድ በወጀብ የተጎዳን ሰው በማስመሰል በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተሠራ ምሥል ከፍተኛ ዕውቅና አግኝቶ ነበር።
ምሥሉ ሐሰተኛ ቢሆንም ሰዎች ግን ወደውታል።
ሐሰተኛ መረጃም ቢሆን የሴራ ትንተና እና ስሜትን የሚኮረኩር ነገር ተመልካች የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው።
ተመልካቾች ብዙ ደቂቃ የሚያጠፉበት እና አስተያየት የሚሰጡበት ይዘት ደግሞ ወደ ሌሎች ብዙ ተመልካቾች እንዲደርስ ዕድልን ያገኛል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ገንዘብ የሚያገኙት ይዘታቸውን ከፍተኛ ቁጥር ወዳላቸው ሰዎች መድረሳቸውን መሠረት በማድረግ ነው።
ለዚህ ደግሞ ይዘታቸው ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች የመመልከት ዕድል እንዲያገኝ ስሜት መንካት ያለባቸው ሲሆን፣ የተሻለ ተመልካች ሲያገኙ ተከፋይነታቸውም ይጨምራል።
በዋሺንግተን ዩኒቨርስቲ አጥኚ የሆነችው ኒና ሉትዝ እንደምትለው፣ ሰዎች የሚያሳዝን ነገር በማየት የራሳቸውን ሐዘን ለማስታገስ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
"አንድ ዓይነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ይገናኛሉ" ትላለች።
ከሚያሳዝኑ ምሥሎች ወይም ይዘቶች ሥር 'ማውራት የሚፈልግ ሰው በቀጥታ መልዕክት መላክ ይችላል' ተብሎ ማሳሰቢያ ይቀመጣል።
ሰዎች ስለ ሐዘናቸው ከሌላ ሰው ጋር በማኅባራዊ ሚዲያ እንዲማከሩ በር የሚከፍት ነው።
ሐሰተኛ የሆኑ የተጎዱ ልጆች ወይም ወታደሮች ምሥል ሲለቀቅ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ስለ ወሲባዊ ጥቃት፣ ስለ ጽንስ ማቋረጥ፣ ስለ ቤተሰብ ሞት፣ ስለ ብቸኛነት፣ ስለ እምነት ወይም ሌላ ርዕሰ ጉዳይ የሚያዋራቸው ሰው እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ።
አጥኚዋ እንደምትለው፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ድጋፍ መጠየቅ የተለመደ ነው።
"ሰዎች የሚያዋሩት ሰው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያገኙባቸው እንደ ተምብለር ያሉ ድረ ገጾች አሉ" ትላለች።
ለምን ማልቀስ አስፈለገ?
አጥኚዋ ሶማ እንደምትለው ሐዘንን ለመሸጥ ብዙም አይከብድም።
ሕንድ ውስጥ በሠራችው ጥናት ለመረዳት እንደቻለችው የሚያለቅሱ ሰዎችን የሚያሳዩ ቪድዮዎች በቲክቶክ ተመልካቻቸው ብዙ ነው።
ሕንድ በ2020 ቲክቶክን ማገዷ ይታወሳል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች እንዴት ራሳቸውን ማስለቀስ እንደሚችሉ ሥልጠና የሚሰጡ ገጾችም አሉ።
ሐዘን ያዘለ ይዘት ሐሰተኛ ሲሆን የማስመሰል ባህሪ ቢኖረውም በማኅበረሰቡ ውስጥ በመደብ፣ በፆታ፣ በማንነት እና በጎሳ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያሳይም ነው ትላለች።
የማያውቁት ሰው ሐዘን ሲሰማው በማኅበራዊ ሚዲያ አይቶ ሐዘኑን መጋራት ድንበር ተሻጋሪ የስሜት ትስስርን ያሳያል።
በእውኑ ዓለም ለማሳየት እምብዛም ቀላል ያልሆኑ ስሜቶችን በማኅበራዊ ሚዲያ የማሳያ መድረክ መፍጠሪያ መንገድም ነው።
ሌላዋ አጥኚ ኒና እንደምትለው እያንዳንዱ ሰው በበይነ መረብ የሚጫወተው ሚና ተደማምሮ አጠቃላይ ውጤት ያመጣል።
"ብዙ ተመልካች ማግኘት ማለት ብዙ ገንዘብ ማግኘት ነው" ትላለች።
የሐዘን ይዘቶች የእውነትም ሆኑ የሐሰት ሰዎችን መሳብ የሚችሉበት መንገድ እንዳላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘቶች ለተመልካቶች የሚቀርቡበትን ሁኔታ የሚወስነው ቀመር (አልጎሪዝም) የሚሠራበትን መንገድ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ካወቁ በኋላ ያንን መንገድ ይከተላሉ።
ሁለቱም አጥኚዎች እንደሚሉት በዚህ መንገድ ስኬታማነታቸውን ያረጋግጣሉ። በምን መንገድ ይዘቱን ፈጠሩት የሚለው ሳይታይ ተመልካች ማግኘታቸው ብቻ በቂ መሆኑንም ያስረዳሉ።