በአዲስ አበባ እና በሌሎች የማዕከላዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የመሬት ንዝረት ተሰማ

እሑድ ምሽት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በሬክተር ስኬል 4.9 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ተሰምቷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ይህን አረጋግጧል።

የአሜሪካ መንግሥት ኦፊሴላዊ የመሬት መንቀጥቀጥ ድረ-ገፅ አሁናዊ መረጃ በሚያደርስበት ገፁ መተሀራ አካባቢ መካከለኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አስታውቋል።

ምሽት 2፡10 ገደማ በርካታ የአዲስ አበባ እና የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የመሬት ንዝረቱ እንደተሰማቸው በማኅበራዊ ሚድያዎች አጋርተዋል።

የአሜሪካው ድረ-ገፅ እንደገለፀው በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 2 ሰዓት ገደማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 10 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ነበረው።

ድረ-ገፁ አክሎ ከመተሀራ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የተከሰተው መንቀጥቀጥ ንዝረቱ ከ380 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ተሰምቷል፤ ፍጥነቱም 0.48 ሰከንድ ነው ብሏል።

የመሬት ንዝሩ በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ መንደሮች የተሰማ ሲሆን ሀያት፣ ሲኤምሲ፣ ቦሌ አራብሳ፣ የካ አባዶ እና ሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የመሬት ንዝረት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ፎቶዎች በርካታ ነዋሪዎች በድንጋጤ ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው መንገድ ላይ ሰብሰብ ብለው አስመልክተዋል።

ክራይሲስ24 የተባለው ድረ-ገፅ ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች መሰማቱን ፅፏል።

ይህን ተፈጥራዊን ክስተት የሚከታተሉ ድረ-ገፆች ከአዋሽ 23 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.9 ነው፤ ይህም መካከለኛ የሚባል ነው ሲሉ ዘግበዋል።

የአሜሪካው በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የሴስሞሎጂ ድረ-ገፅ በአውሮፓውያኑ መስከረም 30 በተመሳሳይ አካባቢ 4.5 ሬክተር ስኬል የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ መመዝገቡን አስፍሯል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጂኦፊዚክስ እና ስፔስ ሳይንስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ “የመሬት መንቀጥቀጡ ለነዋሪዎች አስጊ አይደለም” ሲሉ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ባለሙያው አክለው አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባ የተሰማው ንዝረቱ መሆኑን አስረድተዋል።

አክለው ከሰሞኑ በአፋር ክልል የመሬት መንቀጥቀጦች እንደነበሩ አረጋግጠዋል።

እሑድ ምሽት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ እስካሁን ምንም አልተሰማም።