ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ ላይ የሶማሊያ ሴቶች በወንዶች መወከላቸው ቁጣን ቀሰቀሰ
የሶማሊያ ወንድ ተወካዮች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት በተዘጋጀ የሴቶች ጉዳይ ጉባኤ ላይ መሳተፋቸው በሶማሊያውያን ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ።
የሶማሊያው የቤተሰብ ሚኒስትር ጄኔራል ባሺር ሞሐመድ ጃማ እና አንድ ሌላ ወንድ ልዑክ በሴቶች ጉዳይ ላይ በሚመክረው ጉባኤ ሲሳተፉ የሚያሳይ ፎቶ በኤክስ ገጻቸው ላይ ማጋራታቸውን ተከትሎ ነው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቁጣው የተቀሰቀሰው።
“በጉባኤው ላይ የሶማሊያ ሴቶችን ወንድ ልዑካን ከፊት ሆነው ወክለዋቸው ማየት የአገሪቱ መንግሥት ለሴቶች ጉዳይ ግድ እንደሌለው የሚያሳይ ነው” በማለት ታዋቂዋ ሶማሊያዊት ደራሲ እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ፋቲያ አብሴ ለቢቢሲ ተናግራለች።
አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን በልዑኩ ውስጥ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም እንዳሉበት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አራት አባላት ባሉት በልዑክ ውስጥ ከሁለቱ ወንዶች በተጨማሪ ሁለት ሴቶች መካተታቸውን ገልጸዋል።
በኒው ዮርክ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ሁለት ሴቶች ሶማሊያን ወክለው መሳተፋቸውን፣ ነገር ግን ሚኒስትሩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ፎቶ ውስጥ አለመካተታቸውን ተናግረዋል።
በጉባኤው ላይ ከ57 አገራት 197 ልዑካን ለተሳታፊነት የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 21ዱ ወንዶች መሆናቸው ተነግሯል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተካሄደው ስብሰባ ተሳታፊዎች ፎቶግራፍ ይፋ ከሆነ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሶማሊያውያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።
በርካቶች የታዩት ልዑካን ወንድ መሆን የሶማሊያ መንግሥት ለአገሪቱ ሴቶች ተገቢውን ትኩረት አይሰጥም ሲሉ ተችተዋል።
በጉባኤው ላይ የተነሱ እና በኤክስ ላይ ከተጋሩ በርካታ ፎቶዎች መካከል የሶማሊያው ሚኒስትር ጄኔራል ጃማ ከአማካሪያቸው የቀድሞው የምክር ቤት አባል አብዱላሂ ጎዳህ ባሬ ጋር እንዲሁም ሌላ ፎቶ ደግሞ በስብሰባው ቦታ የሚኒስትሩ ረዳት ነው ከተባለ ሰው ጋር ታይተዋል።
“በስብሰባው ላይ ሚኒስትሩ ብቸኛው ወንድ ተሳታፊ አልነበሩም፣ የቻይናን እና የጃፓንን የመሰሉ አገራት ወንድ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በርካታ ወንዶች ነበሩ” ሲሉ በሶማሊያ የቤተሰብ እና ሰብዓዊ ልማት ሚኒስቴር ውስጥ ባለሥልጣን የሆኑት ሞሐመድ ባሺር አለቃቸውን ተከላክለዋል።
ባለሥልጣኑ ጨምረውም በጉባኤው ላይ የተሳተፉት ሁለቱ ሴት ልዑካን ታዋቂዋ ወታደራዊ መኮንን ኢማን ኤልማን እና በሚኒስቴሩ ሠራተኛ የሆኑት ሳዲያ ሞሐመድ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ በሶማሊያ መንግሥት ላይ የተቀሰቀሰው ቁጣ እና ትችት ባለፈው ዓመት ሐምሌ መንግሥት የሴቶች እና ሰብዓዊ መብቶች ሚኒስቴርን ስያሜ ወደ የቤተሰብ እና ሰብዓዊ ልማት ሚኒስቴር የቀየረበትን ውሳኔ ተቃውሞ በድጋሚ ቀስቅሶበታል።
የሚኒስቴሩ ስም ሲቀየር ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን የሆኑት እና የአገሪቱን የስለላ ተቋም እንዲሁም የእስር ቤቶች አስተዳደርን የሚመሩት ጄኔራል ጃማ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
ለዓመታት በዘለቀ የእስር በርስ ጦርነት ውስጥ የቆዩት እና በቅርቡ ደግሞ በእስላማዊ ታጣቂዎች ጫና ውስጥ ያሉት ሶማሊያውያን ሴቶች በአገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ወሳኝ ሚና እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል።
በተጨማሪም በርካታ ሶማሊያውያን ሴቶች ወደ አመራርነት በመምጣት ሰፊ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ቢሆንም ግን አስካሁን ፖለቲካዊ ተጽእኖ ባለው የሥልጣን ቦታ ላይ ያሉ ሶማሊያውያን ሴቶች ቁጥር ብዙ አይደለም።
የሴቶችን ጉዳይ የሚመለከተው ሚኒስቴር በወንድ መያዙን ብዙዎች ቢቃወሙትም አንዳንዶች ግን ልምድ ያለው ወንድ ሚኒስትር ቦታውን ቢይዝ ችግር የለውም በሚል ይከራከራሉ።
ነገር ግን በዘርፉ ጠንካራ የሴቶች ድምጽ እንዲኖር የሚደረገው ጥሪ እየጠነከረ ሲሆን፣ የሚኒስቴሩ ባለሥልጣን ባሺርም ተቋማቸው ሴቶች በሚኒስቴሩ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።