ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ውስጥ በሚካሄደው ተቃውሞ የሟቾች ቁጥር 76 መድረሱ ተነገረ
በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለች ሴት ሕይወት ማለፍን ተከትሎ ኢራን ውስጥ በተፈጠረ ረብሻ ቢያንስ 76 ተቃዋሚዎች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን አክቲቪስቶች ገለጹ።
መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው የኢራን ሰብአዊ መብቶች ድርጅት (አይኤችአር) ተቃዋሚዎችን ለማፈን ያልተመጣጠነ ኃይል እና ጥይቶችን ተጠቅመዋል ሲል ባለሥልጣናትን ከሷል።
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በርካታ የፀጥታ ኃይል አባላትን ጨምሮ የሟቾች ቁጥር 41 መድረሱን ገልጸዋል። ለችግሩም “ሁከት ፈጣሪዎች” ያሏቸውን ወቅሰዋል።
በተጨማሪም 20 ጋዜጠኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ታስረዋል።
የአይኤችአር ዳይሬክተር ማህሙድ አሚሪ-ሞጋዳም “በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሰው ስቃይ እና እንግልት ከባድ ነው። በተቃዋሚዎች ላይ ጥይት መጠቀም ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው። ዓለም የኢራንን ሕዝብ መሠረታዊ የመብት ጥያቄዎች መጠበቅ አለበት” ብለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤትም የኃይል እርምጃው በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጾ ባለሥልጣናት በሠላማዊ መንገድ የመቃወም መብትን እንዲያከብሩ አሳስቧል።
የማህሳ አሚኒ የቀብር ሥነ ሥርዓትን ተከትሎ የፀረ-መንግሥት ሰልፎቹ ከ80 በላይ በሚሆኑ የኢራን ከተሞች ተስፋፍቷል።
የ22 ዓመቷ ወጣት ዋና ከተማዋን ቴህራንን እየጎበኘች በነበረበት ወቅት ነው ሴቶች ፀጉራቸውን በሒጃብ እንዲሸፍኑ የሚደነግገውን ጥብቅ ሕግ በመተላለፍ በሥነ ምግባር ተቆጣጣሪ ፖሊሶች የተያዘችው።
“ለትምህርት” ወደ ማቆያ ጣቢያ ከተወሰደች በኋላ ተፈጸመባት በተባለ ድብደባ ለሦስት ቀናት ኮማ ውስጥ ቆይታ ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቷ አልፏል።
አሚኒ በድንገተኛ የልብ ድካም ሕይወቷ ማለፉን ፖሊስ ቢገልጽም ቤተሰቦቿ የፀጥታ ኃይሎች ድብደባ እንደፈጸሙባት በመግለጽ የፖሊስን ሪፖርት ውድቅ አድርገዋል።
በወጣቷ ሞት ምክንያት በፍጥነት የተቀሰቀሰው የሞራል ፖሊስ እና የሒጃብ ሕግ ተቃውሞ በኢራን ለዓመታት ካጋጠመው ከባዱ ፈተና ሆኗል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት ሴቶች ሒጃባቸውን ሲያቃጥሉ እና ፀጉራቸውን በአደባባይ ሲቆርጡ ታይተዋል “ሴቶች፣ ህይወት፣ ነፃነት” እና “ሞት ለአምባገነኑ” የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል።
ሰኞ ዕለት ቴህራን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች መደረጋቸው ታውቋል። ከ20 በሚበልጡ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች እና መምህራን የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል።
የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ የኢንተርኔት መቋረጥ የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ዘገባውን እንዳዘገየበት ጠቅሶ፣ በ14 ግዛቶች የ76 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጿል። ከእነዚህም መካከል ስድስት ሴቶች እና አራት ህጻናት ይገኙበታል።
ከሟቾች መካከል 35ቱ ከቴህራን በስተሰሜን በሚገኙት በማዛንድራን እና በጊላን ግዛቶች ነው። 24ቱ ኩርዶች በሚበዙባቸው ምዕራብ አዘርባጃን፣ ከርማንሻህ፣ ኩርዲስታን እና ኢላም ግዛቶች መሆናቸውንም አክሎ ገልጿል።
አይኤችአር እንዳስታወቀው ያገኛቸው ቪዲዮዎች እና የሞት ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት በተቃዋሚዎች ላይ ጥይቶች ከፀጥታ ኃይሎች እየተተኮሱ መሆኑን አረጋግጧል።
የኢራን ባለሥልጣናት ግን ይህንን ያስተባበሉ ሲሆን፣ ነገር ግን ከ1,200 በላይ ሰዎች መታሰራቸውንም አስታውቀዋል።
የኢራን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አክባር ሃሺሚ ራፍሳንጃኒ ሴት ልጅ ፋኤዝ ሃሺሚ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋሏን የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ሃሺሚ የኢራን መንግሥት በግልጽ በመተቸት ትታወቃለች።
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ ከ20 ያላነሱ ዘጋቢዎች እና ጦማሪያን እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሕግ ባለሙያዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተሟጋቾች እንዲፈቱ ጠይቋል።
“የኢራን የፀጥታ ኃይሎች ይህን ወሳኝ ታሪክ በሚናገሩት ጋዜጠኞች ላይ የሚወስዱትን የጭቆና እርምጃ በመተው እና ለሕዝቡ መረጃ ለመስጠት አስፈላጊ የሆነውን የኢንተርኔት አገልግሎት መመለስ አለባቸው” ሲል ሲፒጄ አሳስቧል።