በሩሲያ ወረራ በተያዙ ግዛቶቿ የተደረገውን “የይስሙላ ምርጫ” ዩክሬን አወገዘች

ሩሲያ በይፋ ጠቅልዬ አስገብቻቸዋለሁ ባለቻቸው አራት ግዛቶች የተደረገውን ምርጫ ዩክሬን አወገዘች።

ሩሲያ በወረራ በያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ውስጥ እያደረገች ያለውን ምርጫ የአካባቢ ምርጫ ስትል ጠርታዋለች።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምርጫውን “የይስሙላ” ሲሉ ጠርተውታል።

ምርጫውም ምንም አይነት ህጋዊ ድጋፍ የሌለውም ሲሉም ሚኒስትሩ ተችተውታል።

የቀረቡት ሁሉም እጩዎች የሩሲያ ደጋፊ ወይም በሩሲያ የተመረጡ ገዥዎች የተካተቱበት እንደሆነም ተነግሯል።

በቅድመ ምርጫ ላይ የተሳተፉት በርካታ ነዋሪዎች የታጠቁ የሩሲያ ወታደሮች በተገኙበት ድምጽ እንዲሰጡም ተጠይቀዋል።

ምርጫውን በማደራጀት የተሳተፉ የዩክሬን ዜጎች ለወደፊቱም ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የዩክሬን ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

“ሩሲያ በህገ ወጥ መንገድ በጠቀለለቻቸው የዩክሬን ግዛቶች” እየተደረገ ያለው ምርጫ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ከሆነው የአውሮፓ ምክር ቤት ተቃውሞ ገጥሞታል።

ምክር ቤቱ “ዓለም አቀፍ ህግን የሚጥስ ነው” በማለትም ሩሲያ ይህንን ህግ ችላ በማለት መቀጠሏን ያሳየ ነው ሲልም ነው ወቀሳውን ያቀረበው።

እነዚህ አካባቢዎች የዩከሬን ሉዓላዊ ግዛቶች መሆናቸውን የጣሰ ከመሆን በተጨማሪ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ “የዲሞክራሲን ብዥታ የሚፈጥር ነው” ሲል ምክር ቤቱ በመግለጫው አትቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “ሩሲያ በወረራ በያዘቻቸው የዩክሬን ግዛት እየተደረገ ያለውን የይስሙላ ምርጫ ህገ ወጥ ነው” ሲሉም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ትችት በዝምታ ያልተመለከተችው ሩሲያ በበኩሏ፣ በዋሽንግተን በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ቅሬታዋን አቅርባለች።

እሁድ የሚጠናቀው ምርጫ ሩሲያ በይፋ ወደ ግዛቶቿ ጠቅልላ ባስገባቻቸው የዩክሬን አራት ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ይገኛል። እነዚህም ሉሃንስክ፣ ኬርሶን እና በከፊል በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባሉት ዛፖሪዢዢያ እንዲሁም ዶነትስክ ክልሎች ነው።

ባለፈው ዓመት በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ መጠቃለል ይሻሉ በሚል የጠቀለለቻቸው አራቱ ክልሎች 15 በመቶ ያህል የዩክሬንን ግዛት የሚሸፍኑ ናቸው።

ከነዚህ ግዛቶች በተጨማሪም ሩሲያ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በጠቀለቻቸት የክሪሚያ ግዛትም ምርጫ እየተካሄደ ይገኛል።