በፍጥነት ወይስ ረጋ ብሎ መመገብ ነው ለጤናችን የሚጠቅመው?

ምንም እንኳን ጠደፍ ጠደፍ ብሎ መመገብ ቀላል ሊሆን ይችላል።

ምግብ አቅርበው ስልክዎን እየተመለከቱ፣ አልያም ቴሌቪዥን እያዩ መብላትም ለምደው ይሆናል።

ሳይንስ ግን ቀስ እያሉ፣ የሚጎርሱትን እያስተዋሉ እና እያጣጣሙ መመገብ በጤና ላይ የራሱ በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራል።

የምንመገበው ፍጥነት ከሆነ ከምግብ መፈጨት፣ በምንበላው ከመርካት እንዲሁም ክብደትን ከመቆጣጠር እና ከአጠቃላይ ጤና አንጻር ተጽዕኖ ያሳርፋል።

ለመሆኑ ስንመገብ ምን ማድረግ አለብን? በጥድፊያ መብላት በጤናችን ላይ ምን እግር የስከትላል?

የምግብ መፈጨት

በብራዚል ሳኦ ፓውሎ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ምግብ ትምህርት ያጠናችው ሊቪያ ሃሴጋዋ "ቀስ ብሎ ምግብን ማላመጥ፣ ማኘክ ምግቡ በአግባቡ እንዲልም በማድረግ የምግብ መፈጨትን ቀላል ያደርገዋል። ብዙ ጊዜ ታካሚዎቼን በቀላል ምሳሌ አስረዳቸዋለሁ። ጨጓራችን ጥርስ የለውም። ስለዚህ በአግባቡ ሳናላምጥ ስንውጥ የምግብ መፍጨት ሂደቱ እየቀነሰ እና አዝጋሚ ይሆናል" ብላለች።

አክላም "በተጨማሪ ማኘክ በአፋችን ውስጥ የምግብ መፈጨትን የሚያሳልጥ ምራቅ እንዲመረት ከማበረታታት ባሻገር፤ ንጥረ ምግቦች ከሰውነታችን ጋር እንዲዋሃዱ ይረዳል።"

ምግብ በአግባቡ ካልታኘከ፣ ጨጓራችን በሥራ ይወጠራል። ይህም ለሆድ መነፋት እና ለምግብ መፈጨት ችግር ይዳርጋል።

ሃሴጋዋ አክላ "ለዚህም ነው አንዳንድ ሰዎች ምግብ ከተመገቡ በኋላ ለሰዓታት የሆድ መነፋት እና ያለመፈጨት ስሜት የሚሰማቸው" ብላለች።

ምግብ ለምን ያህል ጊዜ መታኘክ አንዳለበት የሚታወቅ ቀመር የለም። ባለሙያዎች አፍ ላይ የደረሰ ምግብ ከመዋጡ በፊት በሚገባ መላም እና የጨጓራን ሥራ በሚያቀል መልኩ መድቀቅ አለበት ሲሉ ይመክራሉ።

"በተጨማሪም ትኩረትን በሚከፋፍሉ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ መመገብ፣ ቴሌቪዥን መመልከትም ሆነ ስልክ መጠቀም ወይም ሞቅ ያለ ጨዋታ ውስጥ ሆኖ ምግብን ማላመጥ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። ይህ በፍጥነት መመገብን እና በምንውጥበት ወቅት አየር አብሮ እንዲገባ ያደርጋል፤ ያ ደግሞ የሆድ መነፋትን ያስከትላል" ስትል ትናገራለች።

የጥጋብ ስሜት እና ክብደት መጨመር

ከምግብ በሚገባ መፍጨት ጋር በተያያዘ ከሚነሳው ተጽዕኖ በተጨማሪ የክብደት መጨመር ጉዳይ አብሮ ይነሳል።

በኒው ዮርክ በሚገኘው የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሳንደር ከርስተን "በፍጥነት መብላት በፍጥነት ኃይል መጠቀምን ያስከትላል፤ ይህም በደቂቃ ብዙ ካሎሪዎች እንድንጠቀም ያደርገናል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ ፈጣን የኃይል አጠቃቀም ከመጠን በላይ መብላትን ቀላል ያደርገዋል።"

ረጋ ብሎ መመገብ ምግብ በአፍ ውስጥ የሚቆይበትን ጊዜ የሚያራዝም ሲሆን፣ ቀደሞ የምግብ መፈጨት ስሜቶችን እና የሆርሞን መለቀቅን የሚቀሰቅሱ የስሜት ህዋሳትን ያሳድጋል" ስትል ትናገራለች።

"አንጎል ለመጥገብ ምልክት የሚሰጡ ሆርሞኖችን ለመልቀቅ ጥቂት ደቂቃዎችን ይወስዳል። በፍጥነት የሚመገቡ ሰዎች ከሚያስፈልጋቸው በላይ ብዙ ምግብ ይበላሉ። ምክንያቱም ሰውነታቸው ጠግበዋል ብሎ ለመጠቆም በቂ ጊዜ የለውም።"

ውጤቱም ከልክ በላይ ካሎሪ እንድንወስድ የሚያደርግ ሲሆን፣ በዚህም በሰውነት ውስጥ ስብ እንዲከማች ያደርጋል።

በረዥም ጊዜ ያለው የጤና አደጋ

በፍጥነት መብላት እንደ አሲድ መረጨት እና የጨጓራ ሕመም ያሉ ከምግብ መፈጨት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ችግሮችን ያባብሳል።

በተጨማሪም ለአሲድ መረጨት (reflux) የተጋለጡ ሰዎች በፍጥነት በሚመገቡበት ወቅት ሕመማቸው እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል።

"ሌላው ወሳኝ ነገር በአንጀት ውስጥ በሚገኙ ባክቴርያዎች ላይ ያለው ተጽእኖ ነው። ምግብ ወደ አንጀት ውስጥ በአግባቡ ተፈጭቶ ሳይደርስ ሲቀር የአንጀት ባክቴሪያን ሚዛንን ሊያበላሽ ይችላል። ይህም አጠቃላይ የምግብ ልመት ሥርዓቱን ይጎዳል" ብለዋል ሃሴጋዋ።

አክለውም ይህ ልማድ እየቀጠለ ከሄደ፣ በተለይም ከሌሎች ጤናማ ያልሆኑ ባህሪዎች ጋር ተዳምሮ ወደ ከልክ በላይ ውፍረት ሊያመራ ይችላል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ከምግብ ልመት ጋር ተያይዘው ለሚመጡ የጤና እክሎች ተጋላጭነትን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል።

ከእነዚህም መካከል ዓይነት 2 የስኳር በሽታ፣ ጉበት በስብ የመሸፈን፣ የልብ ሕመም፣ የደም ግፊት እና አልፎ ተርፎም እንደ ኮሎሬክታል፣ የጡት እና የጣፊያ ካንሰር ያጋልጣል።

ረጋ ብሎ ለመመገብ የሚረዱ ነጥቦች

የተሻለ የአመጋገብ ልምዶችን ለማዳበር ለሚፈልጉ፣ ሃሴጋዋ የምትሰጠው የመጀመሪያ ጠቃሚ ምክር በእያንዳንዱ ጉርሻ መካከል እጅን በፍጥነት ወደ ምግብ ከመሰንዘር መቆጠብን ነው።

"ሹካን ወይም ማንኪያን ሁልጊዜ ይዞ አለመቆየት፣ ምክንያቱም ያንን ማድረግ ሳናውቀው ቶሎ ቶሎ እንድንበላ ያደርጋል" ብለዋል።

"የምንመገብባቸውን ሹካ እና ማንኪያዎችን ወይንም እጃችንን ማሳረፍ በድጋሚ ወደ ማዕዱ እጃችንን የምንሰነዝርበትን ፍጥነት ይቀንሰዋል። ስለዚህ ይህ የመጀመሪያው ነጥብ ነው፣ አንዴ ጎርሶ ቀጣዩን ጉርሻ ከማዘጋጀት በፊት እያላመጡ መቆየት የሚለው ነው።"

ሃሴጋዋ በአፍህ ውስጥ ምግብ እስኪልም ድረስ ማላመጥ ቀጥለው የሚመክሩት ነጥብ ነው።

"አፋችን ውስጥ ያለው ምግብ በሚገባ መታኘኩን የልመቱ ደረጃ ይነግረናል። ያ ደግሞ የምንወጥበትን ጊዜ ያዘገይልናል።"

በምንመገብበት ጊዜ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማስወገድም የግድ ነው።

ቴሌቪዥን እየተመለከቱ መመገብ ወይም ስልክ እየነካኩ ማዕድ ላይ መቅረብ በምን ያህል ፍጥነት አንደተመገብን እና ምን ያህል እንደበላን ለማወቅ ያዳግታል።

"እየተመገቡ ብዙ ላለማውራት ይሞክሩ። ወሬዎቹ ትኩረትን ሊከፋፍሉ እና ሳያውቁት የሚበሉበትን ፍጥነት ሊጨምሩ ይችላሉ። ስለዚህ ጨዋታውን በመቀነስ የሚበሉትን በሚገባ እያስተዋሉ መቆየት ይመከራል" ሲሉ ሃሴጋዋ ይናገራሉ።