ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩክሬን ዋነኛ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች መውጫ አጥተዋል
የዩክሬን ቁልፍ ከተማ በሆነችው ሰቬሮዶኔትስክ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች አስፈላጊ አቅርቦቶች በሌሉበት ሁኔታ መውጫ ማጣታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠነቀቀ።
በርካታዎቹ በከተማዋ በሚገኘው አዞት የኬሚካል ፋብሪካ ስር ባሉ በረንዳዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ተነግሯል።
ከሰቬሮዶኔትስክ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚያገናኘው የመጨረሻ ድልድይ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በተካሄደው ጦርነት ወድሟል።
በዚህም 12 ሺህ የሚሆነው የከተማዋ ነዋሪ መውጫ ባጡበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል።
ለሳምንታት የበርካታ ከተሞች ማዕከል የሆነችውን ሰቬሮዶኔትስክን ከተማን ለመቆጣጠር የሩሲያ ከፍተኛ ወታደራዊ ግብ ሆኖ ቆይቷል።
“የውሃ እና የንፅህና እጦት ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል። ሰዎች ለረጅም ጊዜ ያለ ውሃ ሊኖሩ ስለማይችሉም ነው አስጨናቂ የሚሆነው” በማለት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ቃል አቀባይ ሳቪያኖ አብሬው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዩክሬን ምስራቃዊ ሉሃንስክ ክልል ውስጥ በምትገኘው ሴቬሮዶኔትስክ የምግብ እንዲሁም የጤና አቅርቦቶችም እያለቀ መሆኑን ቃለ አቀባዩ አክለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት በከተማዋ መውጫ ላጡት በሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች እርዳታ ለማድረስ ተስፋ ቢያደርግም ነገር ግን የጦርነቱ መቀጠል አደጋን ደቅኗል። ሴቶች፣ ህፃናት እና አረጋውያንን ጨምሮ በስፍራው ያሉ ዜጎችን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለመድረስ የረድዔት ድርጅቶች የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህንን ማስጠንቀቂያ ያሳለፈው ሩሲያ ቀደም ብሎ በአውሮፓ ትልቁ በሆነው የኬሚካል ፋብሪካ ውስጥ ተጠልልለው የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎችን ለማስወጣት የሰብዓዊነት ኮሪደር ለመክፈት የገባችውን ቃል ተከትሎ ነው።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ ሲቪል ዜጎችን በሩሲያ ቁጥጥር ስር ወዳለችውና በከተማይቱ ሰሜናዊ ክፍል ለማሻገር የታቀደው አስተማማኝ መንገድ ስለመከናወኑ ማረጋገጫ አልተገኘም።
በያዝነው ሳምንት ረቡዕ እለት የሩሲያ ደጋፊ የሆነው ተገንጣይ ቡድን ባለስልጣን በኬሚካል ፋብሪካው ውስጥ መውጫ አጥተው የሚገኙ ዜጎችን ለማስወጣት የሚደረገውን ሙከራ የዩክሬን ኃይሎች እያደናቀፉ ነው ሲሉ ከሰዋል።
በተጨማሪም የሩስያ መገናኛ ብዙሃን የዩክሬን ሃይሎች በፋብሪካው ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሲቪሎች ከታጣቂዎች ጋር ያሉ ሲሆን የአካባቢውን ነዋሪዎች እንደ ከለላ እየተጠቀሙባቸው ነው ሲሉ ከሰዋል።