የአልበሽር ታማኞች ወደ ስልጣን መመለስ ስጋት የፈጠረባት ሱዳን

ህዝቡ በቃኝ ብሎ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽርን ከመንበራቸው ካስወገደ ሦስት ዓመታት ተቆጠሩ። ህዝቡ በአልበሽር ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (ኤንፒሲ) ፓርቲ ላይ ፊቱን ሲያዞር ስልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊው ሃይል ደግሞ ተጽዕኖ ፈጣሪ ቦታዎችን እያደላቸው ነው። ይህ ወደ ፖለቲካው ማዕከል የመመለሳቸው ጉዳት ስጋት ፈጥሯል።

የአልበሽርን አምባገነናዊ አገዛዝን በመቃወም በተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ ትልቅ ሚና ከተጫወቱት መካከል ጀነራል አብደል ፋታህ ቡርሃን ይጠቀሳሉ።

በኋላም ጀነራሉ የመሠረቱት ደካማ የሽግግር መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት ዕድሜው አጥሯል።

ወደ መንበሩ ከመጡት ብዙዎቹ ህዝባዊ ተቃውሞው በተቀጣጠለበት ወቅት በአልበሽር ስልጣን የተሰጣቸው ከፍተና አመራሮች ናቸው።

ጥብቅ የሸሪዓ ህግን የደነገገውን ኤንሲፒን የሚደግፉም ናቸው።

ሃምዛ ባሎል የፎርስስ ፎር ቼንጅ (ኤፍኤፍሲ) ከፍተኛ አባል ናቸው። ንቅናቄው እስከ መፈንቅለ መንግሥቱ ድረስ መንበሩን ከጄነራሎቹ ጋር ተጋርቶ ቆይቷል። ሠራዊቱ ኤንሲፒን በመከላከል ሽግግሩን እንዳከሰመው ባሎል ያምናሉ።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ከቀድሞው ሥርዓት መሪዎች ጋር “ከፍተኛ ትብብር ሲያደርጉ እንደነበር” ተናግረዋል።

"ከአብዮቱ ጀርባ ያሉ ኃይሎች መፈንቅለ መንግሥቱን ለመቀልበስ አንድ መሆን አለባቸው" ሲል ባሎል ለቢቢሲ ገልጸዋል።

መፈንቅለ መንግሥቱ ባለፈው ጥቅምት ነበር የተካሄደው። ከዚያ ወዲህ የሲቪል አገዛዝ ይመለስ በሚሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ከ100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ።

መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ ጄነራል ቡርሀን መመሪያዎችን አስተላልፈው ነበር። አንደኛው የቀድሞውን መንግስት የስልጣን ይዞታ ለማፍረስ እና ውሳኔዎቹን ለመሻር የተቋቋመው ኮሚቴ ሥራ ማቋረጥ ነው። ኮሚቴው ቀደም ብሎ ያስተላለፈውን ውሳኔም ሙሉ በሙሉ ሽረዋል።

ኮሚቴው በስመ ጥሩ የህግ ባለሙያ ዋጅዲ ሳሌህ ይመራል። ኮሚቴው በአልበሽር ዘመን የተንሰራፋውን ሙስና በማጋለጥ ረገድ ትልቅ ሚና ነበረው። ጠበቃው ጦሩ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በሙስና የተዘፈቁ ባለስልጣናትን እና ነጋዴዎችን ስም ይፋ አድርጓል። የመንግስት ሠራተኞችን ከሥራ አባሯል። ሃብት ማካበቱን አስታውቋል፣ የእስር ማዘዣ አውጥቷል፣ የባንክ ሂሳቦችንም አግዷል። መፈንቅለ መንግሥቱ በተካሄደበት ወቅት በኤንቺፒ አመራሮች እና በጦር ጄነራሎች መካከል ያለውን ግንኙነት እየመረመረ ነበር።

ኮሚቴው ነቃፊዎችም ነበሩት። አንዳንዶቹ በህገ ወጥ መንገድ ይንቀሳቀስ ነበር ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ኢ-ፍትሃዊ ቅጣትን እንዲተገበር መሳሪያ ሆኗል ሲሉ ይሞግታሉ።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ጦሩ ስልጣኑን ለማጠናከር ፊቱን ወደ ኤንሲፒ እና ደጋፊዎቹ አዞረ።

ከማዕከላዊ ባንክ፣ ከፍትህ፣ ከመንግስት ብሮድካስት እና ከመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተባረሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች በወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰዋል።

በአንድ ወቅት ኤንሲፒ መሪ እና አባላት የደቡብ ኮርዶፋን አስተዳዳሪ የነበሩት ጀነራል አህመድ ሙፍዳልን ጨምሮ ሌሎችም ቁልፍ ተሰጣቸው።

አሁን የጄኔራል ኢንተለጀንስ አገልግሎት (ጂአይኤስ) ሃላፊ ነው - ብሔራዊው የመረጃ እና የደህንነት አገልግሎት በአልበሽር የስልጣን ዘመን ይፈራ ነበር። ሙፍዳል ስሙን ቀይሮ ብሔራዊ የስለላ አገልግሎት (ጂአይኤስ) የተባለውን ተቋም ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

የኤንሲፒ ህይወት እየዘራ ስለመሆኑ ሌላ ማስረጃ እናቅርብ። የአባላቱ ንብረት የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የባንክ ሂሳቦች ታግደው ነበረ። አሁን የዋና ዋና አባላቱ ሂሳቦች እገዳው ተነስቶላቸዋል።

ከእነዚህ መካከል፡

· ኢብራሂም ጋንዶር፡ የቀድሞው የኤንሲፒ ኃላፊ እና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

· አናስ ኦማር፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተከሰሰው የቀድሞ የምስራቅ ዳርፉር ገዥ

· ሙሐመድ አሊ አል-ጂዙሊ፡ በአንድ ወቅት ታጣቂውን እስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ቡድን ይደግፉ የነበሩ የሃይማኖት መሪ

አልበሽር አሁንም እስር ቤት ናቸው። እአአ በ 2019 በሙስና ወንጀል ተከሰዋል። ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን በ1989 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስልጣን ባመጣቸው መፈንቅለ መንግስትጉዳይም ክስ ቀርቦባቸዋል። ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚደግፉኃይሎች ይበል የሚሉት ጉዳይ ነው። ችሎቱ መሰማት የጀመረው ጄነራል ቡርሀን መንበረ ስልጣኑን ከመቆጣጠራቸው በፊት ነው። .

በዳርፉር በተፈጠረው ግጭት ምክንያት አልበሽር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ይፈለጋሉ። ጦሩ ግን አሳልፎ እንደማይሰጥ አሳውቋል። አልበሽር ክሱን ያስተባብላሉ።

አንዳንድ ተንታኞች ከዚህም አለፍ ብለው ጦሩ አልበሽርን ከእስር ፈትቶ ሊሆን ይችላል ሲሉ ይገምታሉ። ለዚህ ደግሞ እአአ በ2013 የግብጽ ጦር ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክን ከመልቀቁ ጋር ለማመሳሰል ይሞክራሉ።

አሊ ካርቲ ከኤንሲፒ ጋር ስማቸው ጎልቶ ይነሳል። የሱዳን እስላማዊ ንቅናቄ ተጠባባቂ ዋና ጸሃፊ ናቸው። ይህ ሃገሪቱ ትልቁ የእስላማዊ ቡድኖች ጥምረት ነው። ከኤንሲፒ ማንሰራራት ጀርባ ያሉ ሰው እንደሆኑም ይታሰባል።

ካርቲ መቀመጫቸውን ቱርክ አድርገዋል። ከሦስት ዓመታት በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ ቴሌቭዥን ላይ ለቃለ መጠይቅ ተቀምጠዋል። ኤንሲፒን መከላከል ብቻ ሳይሆን እሳላማዊ ቡድኖች እንደገና መደራጀት እና በሚቀጥለው ምርጫ የመወዳደር መብት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ካርቲ በኮሚቴው ተጠያቂ ከተደረጉ የአልበሽር አስተዳደር አባላት አንዱ ናቸው።

በካርቱም በስተሰሜን በስማቸው የተመዘገቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቦታዎች ተወስደዋል።እሳቸው ግን ምንም አይነት ጥፋት አልፈጸምኩም ሲሉ አስተባብለዋል።

አሁን ደቡብ ሱዳን ለሚባለው እና በዋናነት ክርስቲያኖች ለሚኖሩበት ክልል ነጻነት ሲዋጋ ከነበረው ከሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ (ኤስፒኤልኤም) ጋር የተዋጋውን የሚሊሻ ቡድን በማቋቋም ይታወቃሉ።

በአልበሽር አስተዳደር ወቅት የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አሚን ሀሰን ኡመርም በቅርቡ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል። የእስላማዊ እንቅስቃሴው ሱዳንን ከማንኛውም ስጋት የሚከላከል 500 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉት ተናግረዋል።

ይህ ግን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። እስላማዊ ቡድኑ በእጁ ላይ 500 ሺህ ጦር ካለው በዳርፉር ግጭት ሰፊ ጭካኔ ፈጽሟል ተብሎ ከተከሰሰው የጃንጃዊድ ሚሊሻ የተውጣጣው የመከላከያ ሰራዊት (ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች (አርኤፍሲ)) በቁጥር ይበልጣሉ ማለት ነው።

የአርኤፍኤስ ተዋጊዎች ቁጥር ከ50 ሺህ እስከ 150 ሺhእ እንደሆነ ይገመታል።

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ጀነራል ቡርሃንን ጨምሮ በጦሩ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ቁልፍ ሰዎች የመፈንቅለ መንግሥቱ ምክትል መሪ የሆኑትን እና ተጽዕኗቸው እየጨመረ የመጣውን የአርኤስኤፍ አዛዥ ጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ተጽዕኖ ለመቋቋም ይህንን እየተጠቀሙበት ነው ብለው ያምናሉ።

ጦሩ በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ እንደሚደረግ እና ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንደሚያስረክብ ቃል ገብቷል።

አሜሪካ እና ሳውዲ አረቢያ ልዩነቶችን ለመፍታት በጄኔራሎቹ እና በኤፍኤፍሲ መካከል መደበኛ ያልሆነ ውይይት እያደረጉ ነው። ነገር ግን መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም ግንባር ቀደም ሆነው ከነበሩት የተውጣጡ የተቃውሞ ኮሚቴዎች በጦሩ ላይ ትልቅ ጥርጣሬ አላቸው። ተቃውሞውም እንደቀጠለ ነው።

ጀነራሎቹ ውይይቱን ዓላማቸው ህጋዊነት እንዲያገኝ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። ሌላው ፍርሃት አዲስ ስም ማውጣትን ጨምሮ አዲስ እስላማዊ ቡድኖች ያሉበትን የይስሙላ ምርጫ ይካዳል የሚል ነው።

"እነሱ (ኤንሲፒ) ከድርጅታዊ እና ከፋይናንስ የበላይነታቸው ጋር በምርጫ ከተካፈሉ ደስተኞች ይሆናሉ። ጭንቀቱ ይህ ነው" ሲሉ የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ጆናስ ሆርነር ተናግረዋል።

ለዚህም ነው ተቃዋሚ ኮሚቴዎቹ ጦሩ ወደ ሰፈሩ እንዲመለስ የሚፈልጉት። በተጨማሪም ሱዳንን ወደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚመራ አዲስ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ይፈልጋሉ።

ይህንን ዓላማቸውን ማሳካት ስለመቻላቸው ግልጽ አይደለም። ኤፍኤፍሲ ከጦሩ ጋር አዲስ የስልጣን ክፍፍል ውል እንዳይፈርም ጫና ሊያሳድሩ ግን ይችላሉ።