“ጥቁር በመሆኔ የቆዳ ካንሰር አይዘኝም የሚል እምነት ነበረኝ”

ኢሰር ኔኔር

የፎቶው ባለመብት, Isser Nener

ኢሰር ኔኔር በ20ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ላይ እያለች የቆዳ ካንሰር እንዳለባት ታወቀ።

በአንድ ወቅት በእግሯ ጀርባ ላይ አነስ ያለ ነገር በቅሎ ያየችው ከጓደኛዋ ጋር እየተዝናናች ነበር። ጓደኛዋም ዶክተር እንድታይ መከራት።

“እናም ወዲያው ዶክተሮች ጋር ሄጄ አስወገዱት” ትላለች ኢሰር።

ሆኖም ከሳምንት በኋላ የቆዳ ካንሰር እንደሆነ ተነገራት። ይህ መጥፎ ዜና ሲነገራት በጣም ደንግጣና ተበሳጭታ እንደነበር ታስታውሳለች።

ለኢሰር በጣም ያስደነቃት ነገር ቢኖር በጥቁር ቆዳ ውስጥ ያለው ሜላኒን የተባለው ንጥረ ነገር ከፍተኛ መጠን ባለው ፀሐይ ሊጎዳ አይችልም የሚለውን የተለመደ አባባል ከማመኗ ጋር ተያይዞ ነው ።

ጠየም ያለ ወይም ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ሰው የቆዳ ካንሰር በጭራሽ ሊይዘው እንደማይችል እና ከፀሐይ ብርሃን መጠበቅ እንደማያስፈልግ ነበር የምታምነው።

“እናም ሰን ስክሪን (የፀሐይ መከላከያ) መቀባት አያስፈልግም ብዬ አስብ ነበር። ነገር ግን አሁን የተረዳሁት ነገር ማንኛውም አይነት ቀለም ያለው ቆዳ ቢሆን ያው ቆዳ ነው። እናም በካንሰር መያዝ ማንኛውንም ሰው እንደሚያጋጥመው ነው” ትላለች ኢሰር።

[ሜላኒን በሰውነት ውስጥ የፀጉር፣ የዐይን እና የቆዳ ቀለም የሚያመርት ንጥረ ነገር ነው። ከፍተኛ ሜላኒን የሚመነጭ ከሆነ የዐይን፣ የፀጉር እና የቆዳ ቀለም ይጠቁራል]

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአምስት ዓመት በኋላም የቆዳ ካንሰሩ ተመልሶ የመጣ ሲሆን “እንደ ዕድል ሆኖ ቀደም ብዬ ሳይብስ ደረስኩበት፤ እናም ምንም አይነት ጨረር ህክምና (ኬሞ ቴራፒ) ሂደት ውስጥ አላላፍኩም። ከሊምፍ ኖዶች ውስጥ አንዱን ማስወገድ ነበረባቸው።”

[ሊምፍ ማለት በተፈጥሮ ሰውነት ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ፈሳሽ ሲሆን ተግባሩም በሰውነት ውስጥ በመዘዋወር ቆሻሻን የሚያጣራ ነው። ይህንንም ነጥረ ፈሳሽ በሰውነት ውስጥ እንዲዘዋወር የሚረዱት ማጣሪያ ወንፊት ያላቸው ሊምፍ ኖዶች (Lymph node) ይባላሉ።]

አሁን ኢሰር፣ ከ10 ዓመታት በኋላ ከካንሰር ነጻ ሆናለች።

ኢሰር በልጅነቷ የፀሐይ መከላከያ ተጠቅማ አታውቅም። ካደገችም በኋላም በዚሁ ልምዷ ነው የቀጠለችው።

በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ኪንግደም ካለው የካንሰር ምርምር ተቋም ጋር በመተባበር ሌሎች ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሰሩ ለማስጠንቀቅ እየሰራች ነው።

ተቋሙ ባደረገው ምርምር መሰረት ሜላኖማ የተሰኘው የቆዳ ካንሰር በእስያውያን እና በጥቁር ሕዝቦች፣ ከነጭ ሰዎች ባነሰ መልኩ እንደሚከሰት አስታውቋል።

ነገር ግን የብሪቲሽ የቆዳ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ኦፌሊያ ዳዚ እንደሚሉት ይህ ካንሰር በጥቁሮች ላይ ሲከሰት “በጣም አስከፊ ደረጃ ላይ የሚደርስና የሚታወቀውም ከባሰ በኋላ ነው” ይላሉ።

ለዚህም እንደ ማሳያነት የሚጠቅሱት ስመ ጥር የሬጌ ሙዚቀኛውን ቦብ ማርሌን ነው። የተወሰነ የሰውነቱ ክፍል የቆዳ ቀለም መቀየሩን ካየ በኋላ መጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰ ሜላኖማ ካንሰር መሆኑ ታወቀ። ሕይወቱም ያለፈው በዚህ ካንሰር ህመም ነበር።

“ቆዳችንን ልናይና ልንመረምር ይገባል። ቆዳችንን ስናይ ሙሉ በሙሉ የሰውነታችን ክፍል መሆን አለበት“ በማለት ያስረዳሉ።

“ነገር ግን በተለይ ጠየም ያለ ወይም ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ግለሰቦች ሰዎች መረገጫቸውን፣ እግራቸውን፣ እጅን፣ መዳፍን እና ጥፍርን መመልከትን መርሳት የለባቸውም” በማለትም ምክራቸውን ይለግሳሉ።

በተለይም በመረገጫቸው ላይ ኪንታሮት አለብን ብለው ያመኑ ታካሚዎች በኋላ ላይ በቆዳ ካንሰር መጠቃቸው ታውቋል ይላሉ።

ጥቁር የቆዳ ቀለም በፀሐይ ጨረር ምንም አይሆንም የሚለውን አባባል በመጥቀስ ዶክተር ዳዚ እንደሚናገሩት፣ ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ምናልባትም የመጣው ጥቁር ሰዎች ከሌሎች የቆዳ ቀለም ካላቸው ሰዎች በበለጠ መልኩ ሜላኒን ስላላቸው ነው።

የባህር ዳርቻ ላይ የተቀመጠ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“በማኅበረሰቡ ውስጥ ‘ጥቁር ምንም አይሆንም’ ወይም ሰዎች ‘የመጣሁት ከሞቃታማ አገር ነው’፣ ‘በፀሐይ ሙቀት ምንም አልሆንም’ የሚሉ አሉ። በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲህ አይነት አባባሎች የመጡት ከፍተኛ ሜላኒን አለን ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው” ሲሉ ዶክተር ዳዚ አክለው ተናግረዋል።

ከፍተኛ ሜላኒን የቆዳ ቀለምን ቢያጠቁርም ሌሎች ባህርያትም አሉት። ሜላኒን “በውልደት የሚገኝ የተፈጥሮ የፀሐይ መከላከያ ነው” የሚሉት ዶክተሯ “በቆዳ ሕዋሳት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከአልትራቫዮሌት ጉዳት እና በዲኤንኤ ላይ በአልትራ ቫዮሌት ምክንያት የሚመጡ ለውጦችን ይከላከላል።”

“ሜላኒን በእውነቱ ከዚያ ቢጠብቅም መቶ በመቶ ከፀሐይ ብርሃን አይጠብቅም” የሚሉት ዶክተር ዳዚ፣ ሰዎች ሊያስቡበት የሚገባው የቆዳ ካንሰር ብቻ እንዳልሆነም ያስጠነቅቃሉ።

“ጥቁር ቆዳ ባላቸው ሰዎች ላይ በዋነኛነት የማየው ከፍተኛ የሆነ ሃይፐርፒግመንቴሽን ነው። የፀሐይ አልትራቫዮሌት ጨረር ሃይፐርፒግመንቴሽንን ከፍ ያደርገዋል።”

ሃይፐርፒግመንቴሽን ማለት የቆዳችን የተወሰነው ክፍል ተለይቶ በጣም የጠቆረ ሲሆን ነው። ይህም ከፍተኛ በሆነ ሜላኒን ንጥረ ነገር በሰውነት ስለሚመረት የሚከሰት ነው።

ስለዚህ በከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን ላይ ስንሆን ምን ማድረግ አለብን?

የዶክተር ዳዚ ምክር “የብሪቲሽ የቆዳ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ሦስት አቅጣጫ ያለው ራሳችንን የመጠበቅ ዕቅድን አስቀምጧል። እነዚህም ጥላ፣ ልብስ እና የፀሐይ መከላከያ” ናቸው።

ቆዳችንን ኮፍያን ጨምሮ በአለባበስ እንዲሁም የፀሐይ መነፅር በማድረግ ከፀሐይ ብርሃን ከአልትራቫዮሌት ጨረር መጠበቅ ይቻላል።

“የፀሐይ ጨረሮች በጣም ኃይለኛ በሆኑበት ከጠዋቱ 5 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ጥላ መጠቀምም ይመከራል። ሰን ስክሪን ( የጸሐይ መከላከያ ሲመርጡ) ኤስፒኤፍ 30 የተሰኘውን ክሬም ወይም ከዚያ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው እና ጥሩ የአልትራቫዮሌት መከላከያ መጠቀም አለብን።

ነገር ግን “ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኤስፒኤፍ የተሰኘው ሰንስክሪን ክሬም የተሻለ ነው።”

“የፀሐይ መከላከያው ውሃ የማያሳልፈው መሆኑን እርግጠኛ ይሁኑ። ኤስፒኤፍ ክሬም በየሁለት ሰዓቱ ይቀቡ፤ ይህም በጣም ጠቃሚ ነው።”

ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ

  • መሸፈን፣
  • ቢያንስ ኤስፒኤፍ 30 ወይም ቁጥሩ ከፍ ያለ የፀሐይ መከላከያ ክሬም ይቀቡ፣
  • ሰን ስክሪን (የፀሐይ መከላከያ) ሲመርጡ አልትራ ቫዮሌትን መቋቋም የሚችልና ውሃ የማያሳልፍ መሆኑን እርግጠኛ ይሁኑ።
  • ሰን ስክሪን (የፀሐይ መከላከያ) በየሁለት ሰዓቱ ይቀቡ፣
  • ከፀሐይ ይጠለሉ ወይም ጥላ ይያዙ፣
  • የሚያሳስብ ነገር ካዩ ሐኪምዎን ያማክሩ።