ከጎዳና ላይ ኑሮ እና ልመና ወጥቶ ለሌሎች የሥራ ዕድል የፈጠረው ወጣት

ሰቦና ቡሎ በምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ ነው ተወልዶ ያደገው። ከቤተሰቡ ተለይቶ ጎዳና የወጣው ገና በስምንት ዓመቱ እንደነበር ያስታውሳል።

“ከሰባት ዓመቴ ጀምሬ ከቤተሰቤ እየጠፋሁ አንዴ ወደ ገጠር ሌላ ጊዜ ወደ ከተማ እየሄድኩ ነው ውጪ ማደር የጀመርኩት” ይላል ሁኔታውን ሲያስታውስ።

አባቱ ገና የሦስት ዓመት ሕጻን እያለ መሞቱን ቤተሰቦቹ ሲናገሩ ሰምቷል። በቤት ውስጥ የተለያየ ጫና ይደርስብኝ ነበር የሚለው ሰቦና፣ ከአምስት ወንድም እና እህቶቹ ተለይቶ በጨቅላ ዕድሜው ጎዳናን የሙጥኝ አለ።

ወደ ጎዳና እንደወጣ ያመራው ግን ወደ አሳሳ ከተማ ነው። አሳሳ የልጅ እግሮቹ እንደረገጡ ከብቶች ያላቸው ሰዎች ጋር በወር 35 ብር ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ።

የልጅ ጉልበቱ ግን ችሎ የተሰጠውን ሥራ መከወን አልሆነለትም። ከዚያ ወጥቶ ወደ ባሌ ደሎ መና፣ ገናሌ አመራ።

ሰቦና በደረሰበት ከተማ ሁሉ ሆቴል አልያም ጠጅ ቤት ተቀጥሮ ሳህን እያጠበ፣ ካልሆነም የዕለት ጉርሱን ብቻ እያገኘ ይኖር ነበር።

ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ሲሄድ በእግሩ ጭምር ይጓዝ እንደነበር የሚናገረው ሰቦና፣ “የሄድኩበትን እያንዳንዱን ከተማ ብቆጥር ብዙ ከተማ ላይ ያልተከፈለኝ ደሞዝ አለ” ይላል።

በወቅቱ ድህነትን እና ጥቃትን ሸሽቶ ከቤቱ የወጣው ሰቦና ልጅ ስለነበር ደሞዙን የሚከለክሉት እና የጉልበት ብዝበዛ የሚያደርሱበት በርካቶች እንደነበሩ ያስታውሳል።

“ጠዋት 10 እና 11 ሰዓት ከእንቅልፌ ተነስቼ እስከ ምሽቱ 11 ሰዓት ድረስ የምሰራበት ቦታ ነበር” የሚለው ሰቦና ሞያሌን፣ ቡሌ ሆራን፣ ዲላን፣ ሀዋሳን ረግጦ የመጨረሻ ማረፊያው ወደ ሆነችው አዳማ አቀና።

“ዛሬ ድረስ የሕይወት ገጠመኝ የሆነኝን ያገኘሁት አዳማ ነው”

አዳማ እንደ ደረሰ እጁን ዘርግቶ የተቀበለው የጎዳና ሕይወት መስቀል አደባባይ አካባቢ ጣለው።

መስቀል አደባባይ ፊት ለፊት የሚገኝ ምግብ ቤት ተቀምጦ ከምግብ ቤቱ የሚወጣውን ትራፊ መጠበቅ የዕለት ተዕለት ተግባሩ ሆነ።

የአዳማ ሆቴሎች ከተጠቃሚዎቻቸው የተረፈውን ሰብሰብው በሮቻቸው ላይ ተኮልኩለው ለሚጠብቋቸው የጎዳና ልጆች ይሰጧቸዋል።

እርሱም ከሌሎች መሰሎቹ ጋር ተሻምቶ ትራፊ መመገብ፣ ወለል ላይ መተኛት፣ አላፊ አግዳሚውን መለመን ጀመረ።

ማስቲሽ መሳብ፣ ሆድ ለመሙላት መለመን እንደ ቀላል የሚከወኑ የየዕለት ተግባራቱ ሆኑ።

ብላቴናው ሰቦና ጎዳና ወጥቶ ለአራት ዓመት ያህል የኖረባቸው የአዳማ ጎዳናዎች በርካታ ነገር አስተምረውታል።

በአዳማ ጎዳናዎች ላይ ሲኖር በከተማዋ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ መሹለክለክ ብሎም ማደር ቀላል ናቸው።

የደረሰባቸውን የኑሮ ሸክም ለመሸሽ፣ ያለባቸውን ረሃብ ለማስታገስ፣ ከለሊቱ ቅዝቃዜ ለማምለጥ ማስቲሽ የሚስቡ ታዳጊዎች ደንዝዘው መንቃት ሲያቅታቸው በስለት በመውጋት እንዲነቁ ማድረግ የጎዳና ሕይወት ካሳየው ሰቅጣጭ ገጠመኞቹ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ሰቦና በአዳማ ጎዳናዎች ላይ በቆየባቸው ዓመታት ከፍሳሽ ማስወገጃዎች ውስጥ ይልቅ በበረንዳዎች ላይ መተኛትን ይመርጥ እንደነበር ያስታውሳል።

በሱቆች እና በፎቆች በረንዳዎች ላይ መተኛት ግን በባለቤቶቹ ወይንም በጥበቃ ሠራተኞች መባረር እና መደብደብ ያስከትላል።

“አዳማ ጎዳና ላይ እያለሁ ነው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሞቱት፤ ጥላሁን ገሠሠ ያረፈው፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈችበትን ግብ አስቆጥራ የከተማው ነዋሪ ሲደሰት ፊቴን በቀለም አዥጎርጉሬ የጨፈርኩት ጎዳና ላይ ሆኜ ነው” ይላል ጊዜውን ሲያስታውስ።

በአዳማ ጎዳናዎች ላይ ሲኖር የሚበላ ለማግኘት አንድ ቀን ወደ ቀበሌ 11 ሄዶ የገጠመው ግን ሕይወቱን ቀየረው።

ምግብ ለመለመን ወደ አንድ ቤት ደጃፍ ጎራ ብሎ የተረፈ ምግብ እንድትሰጠው የጠየቃት አንዲት ሴት “ሠርተህ አትበላም” ብላ እጣቢ እንደደፋችበት ያስታውሳል።

“የዚያን ቀን በጣም ከፍቶኝ አለቀስኩ። ከጎዳና ለመውጣት ለራሴ ቃል ገባሁ” በማለት ከዚያ በኋላ የሚሠራው ነገር መፈለግ ጀመረ።

በማግስቱ አዳማ ከተማ ጥቁር አባይ አካባቢ ወደሚገኝ መጋዘን በመሄድ ሸክም መሥራት ጀመረ።

በወዛደርነቱ ግን መሸከም የቻለው ሁለቴ ወይንም ሦስቴ ብቻ ነበር። ባዶ ሆዱን የነበረው ሰቦና ከዚያ በላይ መሸከም ስላልቻለ ራሱን ስቶ ወደቀ። ውሃ ተደፍቶበት ወተት ተግቶ ነቃ።

ሰቦና ለመሸከም አቅም ባይኖረውም ከመሥራት ግን ፊቱን አላዞረም። አንድ ሳምንት ሠርቶ ክፍያውን ከተቀበለ በኋላ ቀጥሎ ያመራው ግንባታ ወደ ሚካሄድባቸው ስፍራዎች ነበር።

በዚያም ግን ለሥራው የሚመጥን አቅም አላገኘም እና ተወው።

ከዚህ በኋላ አዳማን ለቅቆ ወደ ወደ ድሬዳዋ አመራ።

በቀን ሦስት የተለያየ ቦታ የሠራባት ድሬ ዳዋ

አዳማ የከባድ መኪና ሹፌሮች ጂቡቲን እና ሶማሊያን ሲያነሳሱ እሰማ ነበር የሚለው ሰቦና፣ ልቡ ሞቃዲሾን አርግዞ ድሬዳዋ ደረሰ።

ድሬዳዋ ታይዋን 07 ቀበሌ የደረሰው ጎረምሳው ሰቦና የገጠሙት አባት በከተማዋ ቆይቶ እንዲሠራ ምክንያት ሆኑት።

“ጋሼ እንግዳ በሕይወት ኖረው የደረስኩበትን ቢያዩ ደስ ይለኝ ነበር” የሚለው ሰቦና፣ በረንዳቸው ላይ ቁጭ ብሎ ሥራ እንደሚፈልግ ሲናገር በ25 ሊትር ጀሪካን ውሃ እየቀዳ እንዲያመላልስ ያደርጉት ጀመር።

የከተማዋ የውሃ እጥረት ለሰቦና ገበያ ሆነለት። “አንድ ጀሪከን ሃምሳ ሳንቲም እየተከፈለኝ ቀኑን ሙሉ እስከ 200 ጀሪካን ድረስ እቀዳ ነበር።”

የውሃ እጥረት በሚያስለቅሳት ድሬዳዋ ውሃ እየተሸከመ ለምግብ ቤቶች መሸጥ በቀላሉ ገቢ የሚያገኝበት ሥራ ሆነው።

በተለይ ይላል ሰቦና “ድሬዳዋ በልዩ ስሙ ታይዋን ተብሎ የሚጠራው ሰፈር ውሃ እየተሸከምኩ ለረዥም ጊዜ ሸጫለሁ።”

ሰቦና ከማለዳው አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ በጀሪካን ውሃ እየተሸከመ ለምግብ ቤቶች ሲሸጥ የትከሻ ውልቃት አጋጥሞት ነበር።

“ከኮኔል እስከ ታይዋን ሼክ አቢብ ድረስ ውሃ እየቀዳሁ ጎዳና ማደሬን ቀጠልኩ” የሚለው ሰቦና አብረውት ከሚያድሩ ሌሎች ልጆች ቀስ በቀስ ሀሺሽ መጠቀም ለመደ።

በዚህ መካከል ወደ ድሬዳዋ የሆቴል ሥራ ለመጀመር ከባሕር ማዶ የመጡ ሰዎች የሰቦናን ትጋት ሲያዩ አብሯቸው እንዲሠራ ጠየቁት።

ሰቦና ከጎዳና ተነስቶ እነርሱ ባዘጋጁት ቤት እንዲኖር ቢደረግም፣ ካለበት ሱስ ለመላቀቅ ግን ፈተና ሆነበት።

ማስቲሽ መሳብ፣ ሀሺሽ ማጨስ በቀላሉ አራግፎ የሚጥለው ነገር አልሆነም።

ምግብ ቤቱ ተደራጅቶ እስኪከፈት አራት ወር የፈጀ ቢሆንም፣ እነርሱ ባዘጋጁለት ቤት እየኖረ፣ ደሞዝ እየተከፈለው ቆየ።

ምግብ ቤቱ ተከፍቶ ቀይ ባሕር ሬስቶራንት ተብሎ ሥራ ሲጀምር ሰቦና አስተናጋጅነት መሥራት ጀመረ።

ሥራውን ሲለምድ እና ገቢ ማግኘት ሲጀመር ካስጠጉት አሠሪዎቹ ወጥቶ የራሱን ቤት ተከራየ።

በሂደትም ከእነርሱ ጋር ወጥቶ ሌላ ቦታ ተቀጠረ።

ከዚህ በኋላ “በአንድ ጊዜ ሦስት የተለያዩ ስፍራዎች የሠራሁበት ጊዜ አለ” የሚለው ሰቦና፣ ማለዳ አንድ ካፌ በባሬስታነት፣ ከሰዓት በኋላ ሌላ ሻይ ቤት አስተናጋጅነት፣ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ደግሞ ቢፍቱ የጫት ማኅበር ውስጥ ጫት ወደ ውጭ የሚልኩ ጋር ተቀጥሮ ይሠራ እንደነበር ይናገራል።

“ሁሌ እንደዚያ የምሠራው ያቺ የተደፋችብኝን እጣቢ እያስታወስኩ ነበር። ይህ እስከ ዛሬ ድረስ ይሰማኛል።”

ድሬዳዋ ለታታሪው ሰቦና ምቹ ብትሆንም፣ የቀይ ባሕር ሆቴል ባለቤቶች አዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ለከፈቱት ምግብ ቤት ወሰዱት።

ከአሰሪዎቹ በስተቀር ማንንም የማያውቀው ሰቦና ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በምግብ ቤቱ ሲሠራ ቢቆይም ንግዱ በመክሰሩ ምክንያት ምግብ ቤቱ ተዘጋ።

ድሬዳዋ የራሱን ቤት ተከራይቶ እየሠራ ይኖር የነበረው ወጣት ያለ ረዳት እና ያለ ሥራ ቀረ።

አዲስ አበባ ከመጣ ያወቃቸው ግለሰቦች ጋር እያደረ፣ ባዶ ሆዱን ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ሲንከላወስ ያየችው አንዲት ሴት እርሷ ጋር እየበላ ወደፊት ሲያገኝ እንዲከፍላት በቀን አንዴ ይመገብ ጀመረ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላም በአካባቢው ሲኖር የሚያውቀው ግለሰብ አንድ ሺህ ብር ሲሰጠው ከሰው አጥር ስር ሆኖ ጫት እና ቡና አፍልቶ መሸጥን፣ እዚያው ደግሞ ድለላ መሥራት መጀመሩን እና ገቢው እያደገ እንደመጣ ይናገራል።

በዚህ ሥራ ላይ እያለ ከተዋወቃት ሴት ጓደኛው ጋር በመሆን ከጎን ቀላል ምግቦችን እየሠሩ መሸጥ ጀመሩ።

በዚህ ወቅት ነው ገንዘብ መቆጠብ እንዲሁም እቁብ ገብቶ ገንዘብ ማሰባሰብ የጀመረው።

በዚህ መካከል ሰቦና ሕንጻ አከራይቶ በድለላ ጥሩ ገቢ ሲያገኝ፣ “ሥራዬን እያስፋፋሁ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ጁስ ቤት ከፈትኩ” ይላል።

ሰቦና ሁለተኛውን የጭማቂ ቤት በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ከፍቷል።

ሁለቱ ጭማቂ ቤቶች ለ15 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል የሚለው ሰቦና፣ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ዶሮ ማርባት እና መሬት ተከራይቶ ስንዴ መዝራት እንዲሁም የድንች እርሻ ላይም ተሰማርቷል።

ራሱን በገቢ ያጠነከረው ሰቦና ቀጣይ ህልሙ የጎዳና ልጆችን መርዳት ሲሆን፣ ሕጻናቱን ከጎዳና ላይ ካነሳ በኋላ የተለያዩ የሙያ ሥልጠና አግኝተው ራሳቸውን የሚደግፉበትን ነገር ማመቻቸት ነው።