ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልብሷን በማውለቋ የታሰረችው ሴት እንድትፈታ ተጠየቀ
የኢራን ባለሥልጣናት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ልብሷን በማውለቋ ለእስር የተዳረገችውን ሴት እንዲፈቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጠየቁ። ተማሪዋ ልብሷን ያወለቀችው ሂጃብ መልበስ የሚያስገድደውን ሕግ በመቃወም ነው ብለዋል።
ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች ላይ በተዘዋወረ ቪዲዮ ተማሪዋ ልብሷን በማውለቅ በውስጥ ሱሪዋ እና በጡት መያዣ ብቻ በዩኒቨርስቲው ደረጃ ላይ ተቀምጣ ታይታለች።
በኋላም በቴህራን ኢስላሚክ አዛድ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ እና ምርምር ማዕከል ግቢ ውስጥ በእርጋታ ስትራመድ ታይታለች።
በሁለተኛው ቪዲዮ ደግሞ ግለሰቧ የውስጥ ሱሪዋን ስታወልቅ ይታያል። ብዙም ሳይቆይ ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች አስገድደው ወደ መኪና ሲያገቧት ታይተዋል።
አዛድ ዩኒቨርሲቲ ግለሰቧ “የአዕምሮ መታወክ” አጋጥሟት እና ወደ “ወደ አእምሮ ሆስፒታል” ተወስዳለች ብሏል።
በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ኢራናውያን ግን መግለጫውን ከመጠራጠር ባለፈ “የሴት፣ ሕይወት፣ ነፃነት” እንቅስቃሴ አካል አድርገው አቅርበውታል። በእንቅስቃሴው በርካታ ሴቶች ፀጉራቸውን እንዲሸፍኑ እና ረጅም ልብስ እንዲለብሱ የሚደነግገውን ሕግ በአደባባይ ሲጥሱ ታይተዋል።
ኩርዳዊቷ ማህሳ አሚኒ “በተገቢው መንገድ” ሂጃብ አልለበሰችም በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ በተቀሰቀሰ አገር አቀፍ ተቃውሞ ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
ራሱን “የኢራን የተማሪዎች ንቅናቄ ሚዲያ” ብሎ የሚገልጸው እና ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገው የአሚካቢር ጋዜጣ ቴሌግራም ቻናል ግለሰቧ የፀጉር መሸፈኛ ባለመልበሷ ከደኅንነቶች ጋር ወደ ግጭት እንዳመራች ዘግቧል። በፍጥጫ ወቅት ልብሷን ማውለቋንም አስታውቋል።
በቁጥጥር ስር ውላ ወደ መኪና ስትገባ ጭንቅላቷ ከመኪናው ጋር በመጋጨቱ ደም እንደፈሰሳት እና ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዷን አክሏል።
ግለሰቧ ወደ አዛድ ዩኒቨርሲቲ መማሪያ ክፍሎች ገብታ ተማሪዎችን መቅረፅ እንደጀመረች አንድ እማኝ ለቢቢሲ ፋርስ ተናግሯል። መምህሩ ድርጊቷን ሲቃወም እየጮኸች ሄዳለች ብሏል።
እንደ ዓይን ምስክሮች ከሆነ ግለሰቧ ተማሪዎቹን “ላድናችሁ ነው የመጣሁት” ብላቸዋለች።
“አስገዳጅ ሂጃብ መልበስ ላይ ተቃውሞዬን ስገልጽ የፀጥታ ኃይሎች ከያዙኝ በኋላ ቤተሰቦቼ የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለብኝ እንዲናገሩ ጫና ተደርጎባቸዋል” ስትል መቀመጫዋን ካናዳ ያደረገችው የሴቶች መብት ተሟጋቿ እና በ2018 ተቃውሞ ወቅት የፀጉር መሸፈኛ ሂጃቧን በማውለቋ የሦስት ዓመት እስራት የተፈረደባት አዛም ጃንግራቪ ትናግራለች።
“ቤተሰቦቼ አላደረጉትም። ብዙ ቤተሰቦች ግን የሚወዷቸውን ሰዎች ለመጠበቅ የተሻለው መንገድ እንደሆነ በማሰብ ጫና ውስጥ ገብተዋል። እስላማዊው ሪፐብሊክ የሴቶችን የአእምሮ ጤንነት ጥያቄ ውስጥ በመክተት ለማጥላላት የሚሞክረው በዚህ መንገድ ነው” ስትል አክላለች።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ኢራን “በኃይል የታሰረችው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በአስቸኳይ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መለቀቅ አለባት” ብሏል።
“እስክትፈታ ድረስም ባለሥልጣናት ከማሰቃየት እና ሌሎች እንግልት ሊከላከሏት ይገባል። ቤተሰቦቿ እና ጠበቃ ማግኘት ይገባታል። በእስር ወቅት በእሷ ላይ የተፈጸሙ የድብደባ እና የወሲባዊ ጥቃት ውንጀላዎች ገለልተኛ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል። ጥቃት አድራሾችም ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ሲልም አክሏል።
በኢራን የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ የሆኑት ማይ ሳቶ ቪዲዮውን በኤክስ ላይ ለጥፈው “የባለሥልጣናት ምላሽን ጨምሮ ይህንን ክስተት በቅርበት እከታተላለሁ” ሲሉ ጽፈዋል።
ኢራን ውስጥ በእስር ላይ የምትገኘው የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ናርጅስ መሐማዲ ጉዳዩ በጣም እንዳሳሰባት ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።
“ሴቶች ተቃውሞ ለማሰማት ዋጋ እንከፍላለን። እኛን በጉልበት ማንበርከክ ግን የማይታሰብ ነው።”
“በዩኒቨርሲቲው ተቃውሞዋን ያሰማችው ተማሪ ሰውነቷን የጭቆና እና የተቃውሞ ምልክት አድርጋዋለች። እንድትፈታ እና በሴቶች ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ እንዲያቆም ጥሪዬን አቀርባለሁ” ስትል አክላለች።