ካልተሳካ ወታደራዊ እርምጃን ያስከትላል የተባለው የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር

የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት በአወዛጋቢው የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ አዲስ ስምምነት ላይ ለመድረስ በኦማን ዋና ከተማ ሙስካት ባለፈው ሳምንት በተዘዋዋሪ መንገድ ውይይት አድርገዋል።

የመጀመሪያው ዙር ውይይት አበረታች እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዙር ደግሞ ጣሊያን ሮም ላይ እንሚደረግ እየተጠበቀ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2018 ኢራን እና የዓለም ኃያላን መንግሥታት ከደረሱበት የቀድሞው የኒውክሌርየር ስምምነት አሜሪካንን አስወጥተው የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣላቸው ኢራንን አስቆጥቶ ቆይቷል።

አሁን መደረግ የጀመረው ድርድር ካልረሳከ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።

ኢራን ለምን ኒውክሌር እንዲኖራት አልተፈለገም?

ኢራን የምታካሂደው የኒውክሌር መርሃ ግብር ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚውል ነው በማለት የጦር ማሳሪያ ለማምረት እየሠራች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አስታውቃለች።

ነገር ግን ምዕራባውያን አገራት እንዲሁም የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ አካል የሆነው አይኤኢኤ በዚህ የኢራን ምላሽ እምነት የላቸውም።

በተለይ በ2002 ኢራን ምሥጢራዊ የኒውክሌር ግንባታ ተቋም እንዳላት በታወቀበት ወቅት ኢራን በእርግጥ ኒውክሌርን ለሰላማዊ ዓላማ ማዋሏ ላይ ጥርጣሬ ፈጥሯል።

ይህም ኢራን እና ሌሎች ከሞላ ጎደል ሁሉም የዓለም አገራት የፈረሙትን የኒውክሌር መስፋፋትን የመከላከል ስምምነት ስምምነት ያፈረሰ ነው ተብሏል።

ስምምነቱ አገራት ወታደራዊ ያልሆኑ የኒውክሌር ቴክኖሎጂዎችን፤ ለህክምና፣ ለግብርና እና ለኃይል ምንጭ እንዲጠቀሙ ይፈቅዳል።

የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር

አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2018 ከኢራን ጋር ከተደረሰው የኒውክሌርየር ስምምነት ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ፣ በኢራን ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦችን በመመለስ አፀፋዊ እርምጃ ስትወስድ ኢራንም ስምምነቱን የሚጥሱ ሥራዎችን አከናውናለች።

በዚህም ኢራን ለኒውክሌር ግንባታ ወሳኝ የሆነውን እና የተከለከለውን ዩራኒየም ለማበልጸግ በሺዎች የሚቆጠሩ የረቀቁ ማብላያዎችን ገንብታለች።

የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ወደ 90 በመቶ የተጣራ እና የበለፀገውን ዩራኒየም ይፈልጋሉ። በቀደመው ስምምነት መሠረት ኢራን እስከ 300 ኪሎ ግራም የሚደርስ በ3.67 በመቶ የበለጸገ ዩራኒየም እንዲኖራት ተፈቅዶለታል ነበር። ይህ መጠንም ለሲቪል እና ለምርምር ዓላማዎች ብቻ በቂ ሲሆን የኒውክሌር ቦምቦች ለመገንባት የሚያስችል አይደለም።

ባለፈው መጋቢት 2025 ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት ኢራን 275 ኪሎ ግራም ዩራኒየም እንዳላት ገልጿል ይህም ወደ 60 በመቶ በማጣራት አበልጽጋለች። ኢራን ዩራኒየምን የበለጠ ማበልጸጓ በንድፈ ሀሳብ ወደ ግማሽ ደርዘን የሚሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ለመሥራት በቂ ነው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢራን ይህንን ዩራኒየም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለአንድ ቦምብ በቂ የጦር መሳሪያ ደረጃ ልትቀይረው እንደምትችል ያምናሉ።

ሆኖም ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመሥራት ከአንድ ዓመት እስከ 18 ወር እንደሚፈጅባትም ተናግረው፤ አንዳንድ ባለሙያዎች መሣሪያው በስድስት ወር ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊገነባ ይችላል ይላሉ።

ትራምፕ ከኒውክሌር ስምምነቱ ለምን አወጡ?

የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በኢራን ላይ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን የጦር ማሳሪያ ለማምረት እየተጠቀመችበት ነው በሚል ጥርጣሬ ሰፊ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥለውባታል።

ማዕቀቡ ኢራን ነዳጅ ዘይቷን በዓለም ገበያ ላይ እንዳትሸጥ እና 100 ቢሊየን ዶላር በውጭ የሚገኝ የአገሪቱ ሀብት እንዳይንቀሳቀስ አግዷል። በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚዋ ውድቀት ውስጥ ገብቶ የመገበያያ ገንዘቧም በከፍተኛ ደረጃ ውድቀት ስለገጠመው በአገሪቱ የዋጋ ንረትን አስከተለ።

በአውሮፓውያኑ 2015 ኢራን እና ስድስት የዓለም ኃያላን አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንግደም ከዓመታት ድርድር በኋላ ከኢራን ጋር ስምምነት ለመድረስ ችለው ነበር።

በስምምነቱ ኢራን በኒውክሌር መርሃ ግብሯ እንድትሰራ የተፈቀደላትን ከመገደብ በተጨማሪ የዓለም አውቶሚክ ድርጅት ሁሉንም የኢራን የኒውክሌር ግንባታ ተቋማትን ለመጎብኘት እንዲችል እና የተጠረጠሩ ቦታዎችን እንዲፈትሽ ፈቅዳለች።

በምላሹም ኃያላኑ አገራት በኢራን ላይ ተጥሎ የነበረውን ከባዱን ማዕቀብ ለማንሳት ተስማምተዋል።

በኃያላኑ አገራት እና በኢራን መካከል የተደረሰው ይህ ስምምነት ተግባራዊ የመሆነው እስከ 15 ዓመታት ሲሆን ከዚያ በኋላ የሚያበቃ ይሆናል ተብሎ ነበር።

ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ ለመጀሪያ ጊዜ ሥልጣን ሲይዙ በ2018 የስምምነቱ ወሳኝ አካል የሆነችውን አሜሪካንን በማስወጣት ማዕቀቦችን በኢራን ላይ ጣሉ።

ትራምፕ ስምምነቱ ቋሚ ስላልሆነ እና የኢራንን የባሊስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራምን እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን የማይመለከት በመሆኑ "መጥፎ ስምምነት" ነው ብለዋል። በዚህም አዲስ ድርድር ተደርጎ በኢራን ላይ ሰፊ ግዴታን የሚጥል ስምምነት እንዲደረስ ለማስገደድ ማዕቀብ በድጋሚ ጥለዋል።

በዚህ የትራምፕ ውሳኔ ላይ ስምምነቱን የሚቃወሙት የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮች በተለይም እስራኤል ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

እስራኤል ኢራን በድብቅ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እያካሄደችው ነው በማለት፣ በስምምነቱ ከተነሳላት ማዕቀብ የምታገኘውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን ለማጠናከር እንደምትጠቀምበት አስጠንቅቃለች።

አሜሪካ እና እስራኤል የሚፈልጉት ምንድን ነው?

ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ድርድርን በተመለከተ የሰጡት መግለጫ ለእስራኤል እንግዳ ይመስላል። በዚህም ቀደም ካለው ስምምነት "የተሻለ" ስምምነት አደርጋለሁ እያሉ ሲናገሩ የነበረ ሲሆን፣ ኢራን ግን እንደገና ለመደራደር ፈቃደኛ ሳትሆን ቆይታ ነው አሁን ወደ ድርድር የተመለሰችው።

ከዚህ ቀደም ትራምፕ ኢራን ድርድር አድርጋ አዲስ ስምምነት ካልተደረሰ "ቦምብ ይጠብቃታል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ እንዳሉት ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ሙሉ በሙሉ መፍረስን እንደሚፈልጉ ገልጸው ይህም የሚመለከተው "የኒውክሌር ማበልጸጊያዋን፣ የጦር መሣሪያዋን እና ስትራቴጂካዊየ ሚሳኤል ፕሮግራሟ ነው" ብለዋል።

ኢራን በአሁኑ ድርድር የሚደረሰው ስምምነት የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመገደብ እንጂ ለማፍረስ እንዳመይሆን እና የማዕቀብ እፎይታ ለማግኘት እንሚሆን ተስፋ አድርጋለች።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ "ዓላማችን ከእኩል አቋም ላይ ተነስተን ፍትሃዊ እና አክብሮት የተሞላበት ስምምነት ላይ መድረስ ነው" ብለዋል።

ትራምፕ ከኢራን ጋር "የቀጥታ ድርድር እንደሚደረግ" ቢናገሩም፣ አራግቺ ባለፈው ሳምንት በኦማን የተደረገው ድርድር ቀጥተኛ ያልሆነ መሆኑን አመልክተው፣ በእሳቸው እና በአሜሪካው ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ መካከል አጭር ንግግር ብቻ እንደነበር ገልጸዋል።

አራግቺ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰው፣ ነገር ግን ትራምፕ በመጀመሪያ ምንም አይነት "ወታደራዊ አማራጭ" እንደማይኖር መስማማት አለባቸው ብለዋል።

ከትራምፕ ከኢራን ጋር ድርድር እንደሚደረግ ካሳወቁ በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዳሉት ተቀባይነት ያለው ብቸኛው ስምምነት ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለማስወገድ መስማማቷን ያካትታል። ይህም ማለት "በአሜሪካ የበላይ ተቆጣጣሪነት እና ፈጻሚነት ወደ ኢራን ገብተን፣ የኒውክሌር ተቋሞቿን እናፈነዳለን፣ ሁሉንም መሳሪያዎች እናፈርሳለን" ብለዋል።

የእስራኤል ትልቁ ስጋት ትራምፕ ኢራን ሙሉ ለሙሉ እጅ ሳትሰጥ ከስምምነት በመድረስ አስታራቂ ስምምነት ላይ በመድረስ ዲፕሎማሲያዊ ድል ሊያውጁ ይችላሉ የሚል ነው ።

የኒውክሌር መስፋፋትን የሚከለክለውን ስምምነት ያልፈረመችው እስራኤል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳላት ይታሰባል፤ ነገር ግን ይህንን የሚያስተባብልም ሆነ የሚያረጋግጥ መረጃ የለም። የእስራኤልን ህልውና የማትቀበል ኒውክሌር የታጠቀች ኢራን ትልቅ ስጋት እንደሚፈጥርባት ታምናለች።

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራንን ሊያጠቁ ይችላሉ?

አሜሪካ እና እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር መሠረተ ልማትን በቦምብ የማውደም ወታደራዊ አቅም አላቸው፣ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ውስብስብ እና አደገኛ እንዲሁም ውጤቱ እርግጠኛ የማይሆንበት ነው።

የኢራን ቁልፍ የኒውክሌር ተቋማት የተገነቡት ቦታዎች ከመሬት በታች የተቀበሩ ናቸው፤ ይህም ማለት እነዚህን ተቋማት ለማጥቃት ከመሬት በታች ሰርስው መግባት የሚችሉ በጣም ኃይለኛ ቦምቦችን መጠቀም ይጠይቃሉ። እንዲህ ያሉት ቦምቦች አሜሪካ ያላት ሲሆን በእስራኤል በኩል ግን የሚታወቅ ነገር የለም።

ጥቃት ቢሰነዘርባት ኢራን እራሷን መከላከሏ አይቀሬ ነው። ይህም በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ ንብረቶችን ልታጠቃ እና ሚሳኤሎችን በእስራኤል ላይ መተኮስን የሚጨምር ይሆናል።

ለእንዲህ ዓይነቱ ወታደራዊ ዘመቻም አሜሪካ በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ያሏትን የጦር ሠፈሮቿን እንዲሁም አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦቿን መጠቀሟ አይቀርም።

ነገር ግን በአካባቢው ትልቁን የአሜሪካ አየር ኃይልን የምታስተናግደው ኳታርን ጨምሮ ሌሎችም አገራት ከኢራን ሊሰነዘር የሚችል የአጸፋ ጥቃትን በመስጋት አሜሪካ ግዛታቸውን ተጠቅማ ኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንድትፈጽም ላይስማሙ ይችሉ።