ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"...ከገመትነው በላይ ውጤት መጥቷል" ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
የትምህርት ሚኒስትሩ ፐሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በባለፈው ዓመት የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ከተገመተው በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የ12ተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ውጤትን አስመክልተው እሁድ መስከረም 4/2018 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ2017 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
"በተወሰነ ደረጃ ከገመትነው በላይ ውጤት እየመጣ፤ የትምህርት ጥራት እየጨመረ፤ ከኩረጃ ነፃ ሆነው የሚያልፉ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ፤ ይህ ደግሞ ዩኒቨርስቲዎቻችን ውስጥ የሚገቡ ተማሪዎቻችን ጥራት እየጨመረ. . . እንደሆነ የሚያሳይ ነው" ሲሉ ገልፀዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ሥርዓቱ ላይ ማሻሻያ ያደረገው ከአራት ዓመት በፊት በ2013 ዓ.ም. ነበር ።
አገሪቱ መድረስ ከምትፈልግበት ደረጃ ለመድረስ "መሠረታዊ የሆነ የትምህርት ዘርፍ ለውጥ" ማድረግ ቁልፍ ሆኖ መገኘቱን በመግለጫቸው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የ12ተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ውጤትም በዚህ ዓውድ ውስጥ መታየት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
በአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ መሠረት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት የሚችሉ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ናቸው።
በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ተኛ ክፍኛ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 585 ሺህ 882 ተማሪዎች ውስጥ 8.4 በመቶ ብቻ አልፈዋል።
በ2016 ትምህርት ዘመን 5.4 በመቶ ተማሪዎች ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት አስመዝግበዋል።
ሚኒስትሩ የፈተና ሥርዓቱ ላይ ማሻሻያ ከተደረገበት ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው ምጣኔ ጋር አወዳድረው ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ ጨምሯል ብለዋል።
"ከሞላ የጎደል" ማጭበርበር እና መኮረጅ ጠፍቷል በተባለበት በ2017 የትምህርት ዘመን 585 ሺህ 882 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 47.4 በመቶ ሴቶች፤ 52.6 በመቶዎቹ ደግሞ ወንዶች ናቸው።
የ2017 ዓ.ም. አማካኝ ውጤት 31.67 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የታየው የሁለት በመቶ ገደማ ብልጫ "የተፈታኙ ችሎታ እና ዕውቀት ከፍ እያለ" መሄዱን አመላካች ነው ብለዋል።
አዳሪ ትምህርት ቤቶች "እንደሚጠበቀው" ትልቁን ውጤት ማስመዝገባቸውን የጠቀሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ የተማሪዎች አማካኝ ውጤት 71 በመቶ መሆኑን ገልፀዋል።
ዝቅተኛው ውጤት ያስመዘገቡት ደግሞ 'የማታ ትምህርት ቤት' ተማሪዎች ሲሆኑ፣ 25.9 በመቶ አምጥተዋል።
መደበኛ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች 30.6 በመቶ፤ የግል ትምህርት ቤቶች 51 በመቶ አማካኝ ውጤት ተመዝግቧል።
በትምህርት ዓይነቶች ከፍለው የገለፁት ሚኒስትሩ ኬሚስትሪ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት የትምህርት ዓይነት ሲሆን፤ 'አፕቲትዩድ' ደግሞ ዝቅተኛው ውጤት የተመዘገበበት ሆኗል።
ተማሪዎችን በማሳለፍ ምጣኔ አዲስ አበባ (28.9 በመቶ)፣ ሐረሪ ክልል (21.8) እና አማራ ክልል (12.1) ከክልሎች በቅደም ተከተል ደረጃ ይዘዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ "ትልቅ ለውጥ" ሲሉ የገለፁት ሌላው ጉዳይ በ2017 የትምህርት ዘመን የተፈታኞች ቁጥር ቢቀንስ ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር ግን መጨመር ነው።
ባለፈው ዓመት (በ2016 የትምህርት ዘመን) 36 ሺህ 409 ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት ያመጡ ሲሆን፤ በ2017 የትምህርት ዘመን ደግሞ 48 ሺ 929 ተማሪዎች አልፏል።
ይህም ማለት በዚህ ዓመት ወደ ዩኒቨርስቲ ያለፉ ተማሪዎች ካለፈው የትምህርት ዘመን ጋር ሲነፃፀር የ34.4 በመቶ ዕድገት አላቸው።
"ሁሉም ክልሎች ካለፈው የተሻለ ውጤት አምጥተዋል። አንዳንዶቹ ትልቅ፤ አንዳንዶቹ መጠነኛ" ውጤት አምጥተዋል ሲሉም አብራርተዋል።
ለአብነትም ትልቅ ለውጥ ታየበት ያሉትን የጋምቤላ ክልልን ያነሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ክልሉ ባለፈው ዓመት 1.7 በመቶ ተማሪዎቹን ብቻ ያሳለፈ ሲሆን፣ በ2017 የትምህርት ዘመን ግን 4.5 በመቶ ተማሪዎችን አሳልፏል ብለዋል።
ኦሮሚያ ክልል ደግሞ 11 ሺህ 611 ተማሪዎችን በማሳለፍ ከ2016 ዓ.ም. ካሳለፋቸው ተማሪዎች በ3500 ተጨማሪ ተማሪዎች ማሳለፉን በበጎ ጎን አንስተዋል።
23 በመቶ ተማሪዎች በኦንላይን የተፈተኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 21.7 በመቶዎቹ ማለፋቸው ከወረቀት ፈተና በተሻለ የኦንላይን ፈተና አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለው እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
ከ600 ነጥብ 591 ከፍተኛው ውጤት ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል አዳሪ ትምህርት ቤት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ማስመዝገቡን ገልፀዋል።
በተፈጥሮ ሳይንስ በሴት የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 579 ከአዲስ አበባ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ ውጤት የመጣው (በወንድ) 562፤ በሴት ደግሞ 548 መሆኑን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ ከ500 ላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር "ከፍተኛ ለውጥ" መታየቱን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ቁጥሩ በእጥፍ ማደጉን አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ ክልል እና አማራ ክልል በርካታ ተማሪዎች ከ500 ነጥብ በላይ ያስመዘገቡባቸው ክልሎች በመሆን ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
አዳሪ ትምህርት ቤት (ቦርዲንግ ትምህርት ቤት) 87.1 በመቶ ተማሪዎችን ሲያሳልፉ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች 86.6 በመቶ፣ የግል ትምህርት ቤቶች 51.6 በመቶ፣ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ደግሞ 5.6 በመቶ ተማሪዎቻቸውን አሳልፈዋል።
አንድም ተማሪ ያላሳለፉት ትምህርት ቤቶች በ2016 ትምህርት ዘመን 1363 የነበሩ ሲሆን በ2017 እነዚህ ትምህርት ቤቶች 1249 ናቸው።
ይህም ማለት ባለፈው ዓመት ምንም ተማሪ ያላሳለፉ 114 ትምህርት ቤቶች በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪ አሳልፈዋል።
ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች 50 መሆናቸውንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስታውቃል።
"የተሻለ ውጤት" ለመመዝገቡ ተቋማቸው ባደረገው የመጀመሪያ ዙር ግምገማ የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቅሱም "የወላጆች እና የተማሪዎች ብርታት እና ጥረት" ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል።
"ከፈተናዎች ጋር ተያይዞ የገጠመን ችግር እንደ ማኅበረሰብ አጠቃላይ የሞራል ክስረታችን አንዱ መለኪያ ነው። ሁሉን ነገር በአቋራጭ ማግኘት ይቻላል ተብሎ የሚታመንበት፤ ሁሉን ነገር በስርቆት በማጭበርበር ማግኘት ይቻላል ተብሎ የሚታመንበት የሞራል መሠረት ላይ የቆመ አገር ምንም ነገር ቢያደርግ የሚፈልገው ዕድገት ሊያገኝ አይችልም" ሲሉ የፈተና ሥርዓቱን ለምን ጠበቅ ማድረግ እንዳስፈለገም ገልፀዋል።