ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ኢራን ለሩሲያ ስለምታደርገው የጦር ድጋፍ እየዋሸች ነው ሲሉ ከሰሱ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ኢራን፣ ሩስያ በዩክሬን ለምታደርገው ጦርነት እየሰጠችው ስላለው ድጋፍ “ዋሽታለች” እንዲሁም “የሽብር ተባባሪ” ሲሉ ከሰዋታል።
ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ለሩስያ ማቅረቧን ያመነች ሲሆን ይህ ግን ከወረራው በፊት ነበር ብላለች።
ምዕራባውያን ሩሲያ የኢራን "ካሚካዜ" ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በዩክሬን ቁልፍ የሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለመምታት እንደተጠቀመች ቢያምኑም ኢራን እና ሩሲያ ግን ይህንን አይቀበሉትም።
በኃይል የማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ሩሲያ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ በዩክሬን የኃይል አቅርቦት ተቋርጧል።
ምዕራባውያን ባለስልጣናት ኢራን ድሮኖችን ለሩሲያ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለሚዘውሩ ሰራተኞች ስልጠና ትሰጣለች ሲሉ ወቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም ኢራን ውንጀላውን ውድቅ ስታደርግ የቆየች ቢሆንም ነገር ግን ቅዳሜ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወደ ሞስኮ ተልከዋል ብለዋል ።
“ከዩክሬን ጦርነት ቀደም ብሎ ከብዙ ወራት በፊት የተወሰኑ ድሮኖችን ለሩሲያ ሰጥተናል” ሲሉ ሆሴን አሚር አብዶላሂን ቴህራን ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ሆኖም ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በቴሌግራም ቻናላቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢራን “በዚህ መግለጫዋም ቢሆን” ዋሽታለች ሲሉ ወቅሰዋል።
የ44 አመቱ ፕሬዚዳንት ዩክሬን በየቀኑ ወደ 10 የሚጠጉ የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እየመታች ነው ሲሉ የተናገሩ ሲሆን ኢራን በበኩሏ ለሩሲያ ያቀረበችው ድሮን ቁጥራቸው ጥቂት ብቻ እንደሆነ ተናግራለች።
ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ኢራን ለሩሲያ ከምታደርገው ድጋፍ እንድትታቀብም አስጠንቅቀዋል።
" ኢራናውያን አሰልጣኞች ለሩሲያ አሸባሪዎች ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንዴት እንደሚጠቀሙ እንዳሰለጠኑ በእርግጠኝነት እናውቃለን፣ ሆኖም ኢራን በአጠቃላይ ስለ ጉዳዩ ዝምታን መርጣለች” ብለዋል።
“ ኢራን ግልፅ በሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ መዋሸቷን ከቀጠለች ፣ በሩሲያ እና በኢራን መንግስታት መካከል ያለውን የሽብር ትብብር እና ሩሲያ ለእንደዚህ ዓይነቱ ትብብር ለኢራን የምትከፍለውን ምንድን ነው የሚለውን ዓለም ይመረምራል “ ብለዋል።
"በዘመናዊው ዓለም ውስጥ የትኛውም አሸባሪዎች ወይም ተባባሪዎቻቸው የማይቀጡበት ሁኔታ አይኖርም” ብለዋል።
አሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት እና እንግሊዝ ኢራን ለጦርነቱ የሚውል ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለሩሲያ በማቅረቧ ምክንያት ማዕቀብ ጥለዋል።