ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የህንድ የመጀመሪያ መራጭ በ105 ዓመታቸው አረፉ
የህንድ የመጀመሪያ መራጭ በመባል የሚታወቁት ግለሰብ በ105 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
ህንድ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ መውጣቷን ተከትሎ የመጀመሪያውን ጠቅላላ ምርጫ ስታካሂድ ሽያም ሳራን ኔጊ የመጀመሪያው መራጭ እንደነበሩም ተነግሯል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ህንድ ባደረገቻቸው ምርጫዎች ሽያም ሳራን ድምጻቸውን ሰጥተዋል።
ትናንት ቅዳሜ ከመሞታቸው ከሶስት ቀናት በፊት በሂማካል ፕራዴሽ ግዛት በነበረው ምርጫም ላይ ድምጻቸውን በፖስታ ልከዋል።
ጡረተኛውም መምህር በበረዶ ውሽንፍር ምክንያት ምርጫው አምስት ወራት ቀደም እንዲል በሚኖሩበት ግዛት መወሰኑን ተከትሎም ነው በአውሮፓውያኑ 1951 የመረጡት።
በዚህም የምርጫ ውጤት የህንድ ብሔራዊ ኮንግረስ ከፍተኛ ድል የተቀዳጀ ሲሆን ጃዋሃርላል ኔህሩም በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ።
ይህም ምርጫ ከአውሮፓውያኑ 1848-1947 ለ100 ያህል የገዛው የብሪታንያ ቅኝ አገዛዝም ማክተሚያ ሆነ።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አገሪቱ በህዳር ወር ከምታካሂደው ምርጫ በፊት ኔጊ ድምጻቸውን በፖስታ ሲልኩም የህንድ ምርጫ ኮሚሽን ባለስልጣናት ቀይ ምንጣፍ ዘርግተውላቸዋል።
የህንድ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ኔጊ በጤና እክል ምክንያት በምርጫ ጣቢያ ላይ ያልተገኙት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ዘግበዋል።
በአውሮፓውያኑ 2014 ኔጊ መራጮችን ለማበረታታት በሚል የምርጫ ኮሚሽኑ አምባሳደር ሆነው የተሾሙ ሲሆን አገሪቱ ባደረገችው አጠቃላይ ምርጫ በርካቶች እንዲመርጡ በሚያበረታታ የጉግል ቪዲዮም ላይ ተሳትፈዋል።
ረቡዕ እለት የምርጫ ድምጻቸውን በፖስታ በላኩበት ወቅት ወጣቶች እንዲመርጡ ማበረታታቸውን የህንዱ ዘ ትሪቡት ጋዜጣ ዘግቧል።
“ወጣቶች በምርጫ መሳተፍ መብታችን ሳይሆን ኃላፊነታችንም መሆኑንም በማወቅ በዲሞክራሲያዊ ሒደቱ ለመሳተፍ ወደፊት መምጣት አለብን” ሲሉም ተደምጠዋል።
የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ቅዳሜ ዕለት በነበረ የምርጫ ዘመቻ ላይ ለኔጊ የነበራቸውን ክብር ገልጸዋል።
ኔጊ በካልፖ በሚገኘው መንደራቸው በሚደረገው የቀብር ስነ ስርዓት ባህሉ በሚፈቅደው መሰረት አስከሬናቸው በክብር እንደሚቃጠል መንግስት ተናግሯል።