ፈረንሳዊው የ“አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ጋዜጠኛ እና የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ታሰሩ

የ“አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ድረ ገጽ ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ “ከፋኖ እና ኦነግ ሸኔ ጋር በመተባባር ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት በመንቀሳቀስ” ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ጋዜጠኛው “በአስቸኳይ” እንዲፈታ መገናኛ ብዙኃኑ እና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄ ሲጠይቁ፣ ፖለቲከኛው አባል የሆኑበት ኦነግ ደግሞ ስለእስሩ ይመለከታቸዋል ለተባሉ ተቋማት ሁሉ ማሳወቁን ገልጿል።

ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን እና ፖለቲከኛው አቶ በቴ፤ “ሲቪል በለበሱ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት አባላት” በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 14/2016 ዓ.ም. እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የጋዜጠኛው ጠበቃ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የኦነግ የሕዝብ ግንኙት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ፣ አቶ በቴን ከስካይ ላይት ሆቴል በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋልን ቢያረጋግጡም፣ አብሯቸው ታስሯል ስለተባለው ጋዜጠኛ ግን እንደማያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ዘገባ ለሚያቀርበው “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ድረ ገጽ የሚሠራው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ከሁለት ሳምንት በፊት የካቲት 6 ቀን ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባን ለመዘገብ እና “የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮችን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ” እንደነበረ ጠበቃው ገልጸዋል።

አንቷን፤ የአፍሪካ ኅብረትን ስብሰባ ለመዘገብ የሚያስችለውን ፈቃድ ከኅብረቱ ማግኘቱን የሚናገሩት ጠበቃው፤ “[ጋዜጠኛው] የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮችን ኢንተርቪው ለማድረግ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ‘ኢንተርቪው ላደርግ ነው እውቅና ስጡኝ’ ብለው ጥያቄ አቅርበዋል። ይሄ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ያግኝ አያግኝ የታወቀ ነገር የለም” ብለዋል።

ጋዜጠኛው የሚሠራበት የፈረንሳዩ “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ድረ ገጽ የአንቷንን እስር አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ የካቲት 18/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን “የሚታወቅ” መሆኑን ገልጿል።

መገናኛ ብዙኃኑ “[አንቷን] በአገሪቱ ውስጥ ስለነበረው ሥራ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አሳውቋል፤ [ኢትዮጵያ ውስጥ] እንደ ጋዜጠኛ ለመሥራት የሚፈቅድለት ቪዛም ነበረው” ሲል ጋዜጠኛው ሕጋዊ አካሄዶቹን መከተሉን ጠቅሷል።

ጋዜጠኛ አንቷን፤ “ለጥያቄ ትፈለጋለህ” ተብሎ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንደተወሰደ፤ ኋላም ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መዘዋወሩን ጠበቃው ተናግረዋል።

ስለ ጋዜጠኛው እስር ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ፤ “በአገር አቀፍ ጉዳይ ላይ ምላሽ መስጠት ያለበት ፌደራል ፖሊስ ነው” በማለት ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቢቢሲ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ጋዜጠኛ አንቷን እና ፖለቲከኛው አቶ በቴ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ዕለት ረፋድ አራት ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳደር ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት አንድ ላይ መቅረባቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።

የኦነግ የሕዝብ ግንኙት ኃላፊው አቶ ለሚም፤ የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳዮች ኦፊሰር ቅዳሜ ዕለት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ይሁንና ከአቶ በቴ ጋር ዝርዝር ነገር ለመነጋገር ባለመቻላቸው በምን ጉዳይ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት እንደቀረቡ እንዳላወቁ ተናግረዋል።

በዕለቱ ጋዜጠኛ አንቷንን ወክለው በፍርድ ቤት የቀረቡት ጠበቃ እንደሚያስረዱት መርማሪ ፖሊስ፤ “ከፋኖ እና ከኦነግ ሸኔ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ ይዣቸዋለሁ” ሲል ለፍርድ ቤቱ መናገሩን ገልጸው፣ መርማሪ ፖሊስ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት መጠየቁንም ጠቅሰዋል።

ጠበቃው እንደሚያስረዱት ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት የጠየቀው፤ የጋዜጠኛውን ስልክ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ለማስመርመር፣ የጣት አሻራ ለመውሰድ እና “ሌሎች ተባባሪ አካላት ካሉ” በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚል ነው።

መርማሪ ፖሊስ ላቀረበው ጥርጣሬ ምላሽ የሰጡት ጠበቃው፤ “ግለሰቡ ጋዜጠኛ ናቸው፤ የጋዜጠኝነት ሥራ ከመሥራት ባሻገር ምንም አይነት ተሳትፎ የላቸውም። ወደዚህ አገር ሲገቡም ተገቢው ቪዛ፣ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ነው፣ ከአፍሪካ ኅብረትም ተገቢው የእውቅና ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፣ ቃለ መጠይቅ እንደሚያደርጉም ለመንግሥት አሳውቀዋል” የሚል መከራከሪያ ማቅረባቸውን አብራርተዋል።

ከፖለቲከኛው አቶ በቴ ጋር የነበራቸው ግንኙነትም “በቀን፣ የሕዝብ መገናኛ ቦታ ላይ” የተፈጸመ መሆኑን በመጥቀስም፤ “ምንም ሴራ ነበረ የሚያሰኝ ነገር አልነበረም” በማለት ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን ገልጸዋል። አብረው በችሎቱ የቀረቡት የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴም በፖሊስ የተገለጸው ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሌላቸው መናገራቸውን አስታውሰዋል።

ጠበቃው፤ የጋዜጠኛውን ስልክ ለመመርመር “የግለሰቦቹን በእስር ላይ መቆየት የሚጠይቅ እንዳልሆነ” እንዲሁም የጣት አሻራ ለመውሰድም “ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ መውሰድ ይቻል እንደነበር እና አሁንም ከ10 እና 15 ደቂቃ የበለጠ ጊዜ የሚወስድ እንዳልሆነ” ጠቅሰው የዋስትና መብት እንዲፈቀድ መከራከራቸውን አስረድተዋል።

የሁለቱንም ወገኖች መከራከሪያ ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም ከተጠየቀው 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ ስድስት ቀን መፍቀዱን ጠበቃው ገልጸዋል። የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚም ይህንኑ አረጋግጠዋል።

ወደ አዲስ አበባ የላከው ጋዜጠኛው የታሰረበት “አፍሪካ ኢንተለጀንስ”፤ በዛሬው መግለጫው የአንቷንን እስር “ምክንያት የለሽ” (unjustified) እና “በፕሬስ ነጻነት ላይ የተቃጣ ጥቃት” ሲል ገልጾታል። መገናኛ ብዙኃኑ እስሩን ያወገዘ ሲሆን፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛውን “በአስቸኳይ” እንዲፈቱም ጠይቋል።

በጉዳዩ ላይ ዛሬ መግለጫ ያወጣው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ሲፒጄም በተመሳሳይ ጋዜጠኛ አንቷን “በአስቸኳይ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ” እንዲለቀቅ ጥያቄ አቅርቧል።

አንቷን “ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ በአሳሳቢ ሁኔታ” ለእስር መዳረጉን የገለጸው ሲፒጄ፤ “የአንቷን ጋሊንዶ እስር፤ በሥራቸው ምክንያት የታሰሩ እና በአስቸኳይ መለቀቅ ያለባቸው ቢያንስ ስምንት ጋዜጠኞችን በሚገኙባት ኢትዮጵያ ላለው አስከፊ የፕሬስ ነጻነት ሌላ ምሳሌ ነው” ሲል እስሩን ተቃውሟል።