በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ ግድያ እንዲቆም እና ፈጻሚዎች ለሕግ እንዲቀርቡ አምነስቲ ጠየቀ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ ይፈጽማል ያለውን ግድያ እንዲያቆም እና በድርጊቱ የተሳተፉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

አምነስቲ ዛሬ ባወጣው አጭር ሪፖርት ላይ በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጸሙ ያላቸውን እና መረጃ ያሰባሰበባቸውን ግድያዎችን በመጥቀስ የደረሱ ጉዳቶችን አቅርቧል።

በተለይ በግጭቱ የመጀመሪያ ወራት በባሕር ዳር እና አካባቢዋ በመከላከያ ሠራዊት ከሕግ ውጪ ግድያዎች መፈጸማቸውን የጠቀሰው አምነስቲ፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች “ቤተሰቦች የሟቾችን አስከሬን በማንሳት እንዳይቀብሩ” እንደተከለከሉ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።

በሪፖርቱ ላይ የመከላከያ አባላት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ቀበሌ 08 በተባለው አካባቢ አቡነ ሃራ እና ልደታ በተባሉ ሰፈሮች በስድስት ሰዎች ላይ የፈጸሟቸውን ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎችን መዝግቧል። በተጨማሪም በጥምት ወር መጀመሪያ ላይ ሰባታሚት በተባለ ስፍራ ሌሎች ስድስት ሰዎችን መግደላቸውን አመልክቷል።

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው እና ወራትን ባስቆጠረው ግጭት ምክንያት ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን ያመለከተው አምነስቲ፣ አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት እንቅፋቶች እንዳሉም ጠቁሟል።

ግጭቱ በሰብአዊ መብቶች ላይ ያሳደረገውን ተጽእኖ ለመረዳት በመገናኛ ዘዴዎች መቋረጥ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመናገር እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ላይ ጫና በመፍጠር እና የበቀል እርምጃን መፍራት መረጃዎች በአዝጋሚ ሁኔታ እንዲወጡ እያደረገ ነው ብሏል።

አምነስቲ የአፍሪካ ቀንድ ተጠሪው ሱዑድ ኑር እንዳሉት የኢንተርኔት መቋረጥ ባለበት ሁኔታ ከርቀት ምርመራ ማካሄድ ከፍ ያለ ጥንቃቄን የሚሻ መሆኑን አመልክተው፣ ነገር ግን “በክልሉ እና በአገሪቱ ውስጥ ከሚካሄዱ ወታደራዊ ግጭቶች ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የመብት ጥሰቶችን መከታተላችንን እንቀጥላል” ብለዋል።

አምነስቲ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙት ግድያዎች የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ጥሰት እና ከባድ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸቀውን እንደሚያመለክቱ በመግለጽ፣ እነዚህም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል።

የመብት ተቆርቋሪው ድርጅት በኢትዮጵያ የእንዲህ ዓይነት ወንጀል ፈጻሚዎችን ተአማኒ በሆነ የፍትህ ሥርዓት ተጠያቂ ባለመሆናቸው ተደጋግመው እንዲፈጸሙ ምክንያት መሆኑን ጠቅሶ፣ “በመላው አገሪቱ የሚታየውን የፍትህ መጓደል እንዲያበቃ እና ተጠቃቂነት እንዲሰፍን” ጥሪ አቅርቧል።

አምነስቲ ባለፈው ዓመት ነሐሴ እና በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ባሕር ዳር ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች የተገደሉትን ሰዎች ቤተሰቦች እና የዐይን እማኞችን በማነጋገር ምስክርታቸውን በሪፖርቱ ውስጥ አካቷል።

በወታደሮች ግድያዎች ከተፈጸመ በኋላ ቤተሰቦች የሟቾችን አስከሬን እንዳያነሱ መከልከላቸውን እና ወታደሮቹ ከአካባቢው አስኪሄዱ ለረጅም ሰዓታት መጠበቅ እንደነበረባቸው እንዲሁም በተፈጠረባቸው ስጋት ሟቾችን በድብቅ ለመቅበር መገደዳቸውን ተናግረዋል ብሏል።

“መንግሥት በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ካለው የትጥቅ ግጭት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ገለልተኛ ምርመራ በአስቸኳይ እንዲጀመር እና ድርጊቱን በመፈጸም በቂ ማስረጃ በተገኘባቸው ላይም ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ ሁኔታ በሕግ እንዲጠየቁ” ሲሉ የአምነስቲ የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ ጥሪ አቅርበዋል።

ምስክርነታቸውን ለአምነስቲ የሰጡት ግለሰቦች ግድያዎቹ በመከላከያ ሠራዊት አባላት መፈጸማቸውን እንዴት እንዳወቁ ተጠይቀው፣ አብዛኞቹ የሠራዊቱ አባላት ለወራት በባሕር ዳር ሲንቀሳቀሱ ስለነበር በደንብ ልብሳቸው እንደሚለይዋቸው ተናግረዋል። አንዳንዶች ደግሞ “የጦር መሳሪያ አምጡ፤ ፋኖን ትደግፋላችሁ?” በሚል የሟቾችን ቤተሰቦች መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከሚደረገው ግጭት ጋር በተያያዘ አምነስቲ የሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ ግድያዎች በርካታ መሆናቸውን እና በዚህ ሪፖርት ውስጥ የተወሰኑ ማሳያዎችን ብቻ እንዳቀረበ የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ተጠሪ ሱዑድ ኑር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እየተፈጸሙ ካሉ የመብት ጥሰቶች አኳያ በኢትዮጵያ ላይ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ ትኩረት ሊደረግባት ያገባል ያለው አምነስቲ፣ “የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ካውንስልን ጨምሮ የአገሪቱ አጋሮች በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ ለመከታተል በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምሩ” ጥሪ አቅርቧል።

በዚህ ሪፖርት የመጀመሪያ ግኝት ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት አምነስቲ ኢንትርናሽናል ቅጂውን ለፍትህ ሚኒስቴር እና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መላኩን ነገር ግን ምላሽ አለማግኘቱን አመልክቷል።

አምነስቲ በክልሉ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰቶችን የሚያመለክቱ በርካታ ክስተቶች አየደረሱት መሆኑን ለቢቢሲ ገልጾ፣ በአማራ ክልል ሆነ በመላው አገሪቱ ሌሎቹንም የመብት ጥሰቶችን በምርመራ ይፋ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ሱዑድ ኑር ተናግረዋል።

ድርጅቱ በቅርቡ በሰሜን ጎጃም መርዓዊ ውስጥ ስለተፈጸመው ከሕግ ውጪ ግድያን በተመለከተ ሪፖርቶች እንደደረሱትን እና በአገሪቱ ውስጥ ሌላ ግድያ መከሰቱን መስማታቸው እንዳሳሰባቸው የጠቀሱት ሱዑድ፣ ክስተቱን መከላታላቸውን መቀጠላቻውን ገልጸዋል።

ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው መርዓዊ ከተማ ጥር 20/2016 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት አባላት ቤት ለቤት አሰሳ በማካሄድ እና መንገድ ላይ ያገኟቸውን በርካታ ሰዎች መግደላቸውን ቤተሰቦች፣ የጤና ባለሙያዎች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ግን በሠራዊቱ ላይ ጥቃት ፈጽመው ወደ መኖሪያ አካባቢዎች ከገቡ የፋኖታጣቂዎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የተገደሉት ታጣቂዎች ናቸው ሲል በሠራዊቱ ላይ የቀረበውን ክስ አስተባብሏል።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ በኋላ የክልሉን ልዩ ኃይል ለመበተን እና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት በመንግሥት የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።

የክልሉ መስተዳደርም ሁኔታው ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለጽ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በመጠየቁ በክልሉ እና እንዳስፈላጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ወደ ክልሉ ተሰማርቶ ይገኛል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በተካሄዱ ወታደራዊ ግጭቶች በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ መደበኛ እንቅስቃሴዎች የተስተጓጎሉ መሆናቸውነ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በተጨማሪም በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል በሚካሄዱ ውጊያዎች እና በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውነ እና የንብረት ውድመት ማጋጠሙ እየተዘገበ ነው።