ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከደብረ ብርሃን ወደ ደሴ የሚወስደው ዋና መንገድ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱ ተገለጸ
ከደብረ ብርሃን ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ ከዛሬ ቅዳሜ፣ የካቲት 16/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱ ተገለጸ።
የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራው ጽሑፍ ከዛሬ ጀምሮ የትኛውም ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት ከደሴ - ሸዋሮቢት- ደብረ ብርሃን እንዲሁም ከደብረ ብርሃን - ሸዋሮቢት -ደሴ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለጊዜው እንዲቆም የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት መወሰኑን አስታውቋል።
ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የማቋረጥ እርምጃ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምሥራቅ 130 ኪሎ ሜትር ከምትርቀው የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው ከደብረ ብርሃን የሚጀመር ነው።
ኮማንድ ፖስቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈውም “ፅንፈኛ” ያላቸው ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል መሆኑን ገልጿል።
ሆኖም እየወሰድኩት ነው ያለው እርምጃ ለአጭር ጊዜ እንደሚቆይ ከመጠቆም በዘለለ ያስቀመጠው ቀነ ገደብም ሆነ፣መንገዱ መቼ ለአገልግሎት እንደሚከፈት ያለው ነገር የለም።
ከአዲስ አበባ ወደ ወደ የተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የሚወስደው ዋና መንገድ ከዚህ ቀደምም በተከሰቱ ጥቃቶች፣ ግጭቶች፣ እገታዎችና “ያለአግባብ” በጸጥታ ኃይሎች በሚደረጉ የኬላ ፍተሻዎች ምክንያት ሲዘጋና ሲከፈት ቆይቷል።
ይህም መንገደኞችን ለመጉላላት የዳረገ ሲሆን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩንም እንዳዳከመው ይነገራል።
የመንገዱ መዘጋት ከአዲስ አበባ ወደ ወልዲያ፣ ዋግ ኽምራ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚጓዙ መንገደኞችን የሚያስተጓጉል ሲሆን አገሪቷ ያጋጣማትን የኢኮኖሚ ቀውስም እንዳያባብስ ያሰጋል።
በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ባለፈው ዓመት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የክልሉ ከተሞችን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች እንዲሁም አብዛኞቹን የክልሉን ከተሞች እርስ በርስ የሚያስተሳስሩ መንገዶች ሰላም ርቋቸዋል።
በዚህም ምክንያት የከተሞች ነዋሪዎች ለሕክምና፣ ለሥራ ጉዳይ፣ ለዘመድ ጥየቃ አሊያም የውጭ አገር ጉዞ ለማድረግ ወደ ክልሉ ትላልቅ ከተሞች እንዲሁም ወደ መዲናዋ ለመግባት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የአየር ትራንስፖርትን አማራጭ ማድረጋቸው ተስተውሏል።
ይህንን ለማድረግ አቅማቸው ያልፈቀደላቸው ሰዎችም ከእንቅስቃሴያቸው ለመገታት አሊያም የደኅንነት ችግር ያለባቸውን መንገዶች በስጋት ለማቋረጥ ተገደዋል።
ወራት ያስቆጠረው በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት የተቀሰቀሰው መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በማፍረስ መልሶ ለማደራጀት እና ሌሎች ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ ነበር።
የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ እና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም፣ እስካሁን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች የሉም።
በክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ማኅበራዊ ገጽ ላይ በተጋራው የኮማንድ ፖስቱ ጽሑፍ ላይ “ አካባቢውን ከጽንፈኛ ኃይሉ በአጭር ቀናት ነጻ ለማድረግ” ሲል ባሳለፈው ውሳኔ ሕብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግለትም ጠይቋል።
ኮማንድ ፖስቱ “ፅንፈኛ” ሲል የገለጻቸው ኃይሎች እነማን እንደሆኑ በግልጽ አልጠቀሰም።
ሆኖም ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ ላይ በክልሉ ውስጥ በሚገኘው የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ውስጥ መንግሥት ሸኔ የሚላቸው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ ይነገራል።
ታጣቂዎቹ በተለያዩ ጊዜያት በጥቃት በወደመችው አጣዬ ከተማ እና በዙሪያ ባሉ ከተሞችና ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘርም ሲከሰሱ ቆይተዋል።
በሌላ በኩልም ባለፈው ዓመት መንግሥት የክልሉን ልዩ ኃይሎች ትጥቅ ለማስፈታት እና እንደገና ለማዋቀር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎችና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የፋኖ ታጣቂዎች በአካባቢው በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ይነገራል።
መንግሥት በታጣቂዎቹ ላይ በድሮንና በከባድ መሣሪያዎች የታገዘ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ነገር ግን በሚፈፅማቸው ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች፣ የጤና ባለሙያዎች እና ዓለም አቀፍ እና አገራዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እየገለጹ ይገኛሉ።
ከቀናት በፊት በዞኑ በሚገኝ ሞጃ እና ወደራ ወረዳ በአንድ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች እና የጤና ተቋም ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
አጠቃላይ የሟቾቹን ቁጥር “30 ይሆናሉ” ያሉ ምንጮች፤ በአያቱ እቅፍ ውስጥ ነበር የተባለው “ክርስትና የተነሳው ህጻን” ጉዳት ሳይደርስበት በሕይወት መትረፉንም ተናግረዋል።
ሰኞ የካቲት 11/2016 ዓ.ም በተፈፀመው በዚህ የድሮን ጥቃት ሕጻን ልጃቸውን ክርስትና አስነስተው በጭነት መኪና ተሳፍረው ሲጓዙ የነበሩ ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ከወረዳው ዋና ከተማ ሰላ ድንጋይ ወጣ ብላ ከምትገኝ ሳሲት ከተባለች አነስተኛ ከተማ ሲደርሱ የድሮን ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ቢቢሲ ከሟች ዘመዶች እና የሕክምና ምንጮች ሰምቷል።
ከረፋዱ 5፡00 እስከ 6፡00 ባለው ጊዜ እንደደረሰ የተነገረውን ይህንን ጥቃት የአካባቢው ነዋሪዎች “እልቂት” ሲሉ ነበር የገለጹት።
ካለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች የሚካሄደው ግጭት የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።
ከግጭቱም ጋር ተያይዞም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች አሳሳቢነቱ መቀጠሉን የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እየገለጹ ይገኛሉ።