በእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትሩን መባረር ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የመከላከያ ሚኒስትሩን ማባረራቸውን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ።

የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ዮአቭ ጋላንት ከስልጣን የተነሱት በአገሪቷ ያለውን የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል የወጣ አወዛጋቢ እቅድን ከተቃወሙ በኋላ ነው።

የሕግ ማሻሻያው መንግሥት ዳኞችን የሚሰይመውን ኮሚቴ ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠር የሚያስችሉ እቅዶችን የሚያካትት ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ ፍርድ ቤቶች ለሥልጣን ብቁ አይደሉም የተባሉን መሪ ለማንሳት ሥራቸውን ፈታኝ የሚያደርግ ነው።

በመሆኑም ማሻሻያው በሙስና ወንጀል ተከሰው በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ ያለው የቤንያሚን ኔታንያሁ ፍላጎት እንደሆነ የሚያምኑትን አስቆጥቷል።

ኔታንያሁ ግን የሕግ ማሻሻያው ፍርድ ቤቶች ከአቅማቸው በላይ በሥራ እንዳይጨናነቁ ለማድረግ ያለመ እና በቅርብ በተካሄደው ምርጫ በሕዝብ ድምጽ የተሰጠበት ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ሰኞ ዕለት ጠዋት የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ መንግሥት የሕግ ማሻሻያዎቹን እንዲያግድ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ “ለእስራኤል ሕዝብ አንድነት እና ኃላፊነት ሲሉ የሕግ ማሻሻል ሒደቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ፕሬዚደንቱ በዚሁ ጽሑፋቸው “የእስራኤል ሕዝብ ዓይን እርስዎ ላይ ነው” ሲሉም አክለዋል።

አሜሪካ በበኩሏ በእስራኤል ያለው ሁኔታ እጅጉን እንዳሳሰባት ገልጻ፣መስማማት ላይ እንዲደረስ ጠይቃለች።

ተቃዋሚዎቹ የእስራኤልን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ፣ ብረቶችን እያጋጩ በእየሩሳሌም በሚገኘው የኔታንያሁ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ ከዚያም እስራኤል ምክር ቤት-ክኔሴት ለመድረስ የፖሊስ ኃይሎችን ጥሰው አልፈዋል።

አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ለቢቢሲ ስትናገር “ኔታንያሁ እንደ ዲሞክራሲያዊ አገር ያለንን መስመር እያለፉ ነው” ብላለች።

“ያለንን የመጨረሻውን ዲሞክራሲ እየተከላከልን ነው። በዚህ ሁኔታ መተኛት አልችልም። ይህንን እብደት እስከምናስቆም ድረስ ምንም መስራት አልችልም” ስትልም ጨምራ ተናግራለች።

በቴል አቪቭ የሚገኝ አውራ ጎዳናም የአገሪቷን ሰንደቅ ዓላማ በሚያውለበልቡ ተቃዋሚዎች ከሁለት ሰዓታት በላይ ለሆነ ጊዜ ተዘግቶ ቆይቷል።

የጸጥታ ኃይሎችም ተቃዋሚዎቹን ለመበተን ውሃ ተጠቅመዋል።

የቀድሞ ወታደር የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትር ጋላንት፣ አዲስ በወጣው የሕግ ማሻሻያ ደስተኛ አይደሉም።

ጋላንት ሕጉን በመቃወም ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ንግግር የእስራኤል የመከላከያ ኃይሎች በሕጉ የተቆጡ እና የተበሳጩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጋላንት በቴሌቪዥን ቀርበው ይህንን ሲናገሩ ከአገር ውጭ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፣ ከዚህ በኋላ "እንደ መከላከያ ሚኒስትር በእርሳቸው ላይ እምነት አይኖረኝም" ብለዋል።

ሁለቱ ፖለቲከኞች የሊኩድ ፓርቲ አባላት ሲሆኑ የመከላከያ ሚኒስትሩ በአቋማቸው የተወሰኑ የፓርቲ አባላትን ድጋፍ ማግኘት ችለዋል።ሌሎች የቀኝ አክራሪዎች ደግሞ ሚኒስትሩ እንዲባረሩ ጠይቀዋል።

መከላከያ ሚኒስትሩ፣ ከሥልጣናቸው ከተባረሩ በኋላ በትዊተር ገጻቸው “የእስራኤል ደኅንነት የሕይወቴ ተልዕኮ የነበረ እና ሁልጊዜም የሚሆን ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል።

የእስራኤል ተቃዋሚ መሪ ያሪ ላፒድ በበኩላቸው የጋላንት መባረር ለመንግሥት “አዲስ ዝቅጠት ነው” ሲሉ ኮንነውታል።

“ኔታንያሁ ጋላንትን ማባረር ይችላል፤ ነገር ግን እውነታውን መካድ አሊያም የጥምረቱን እብደት ለመቃወም የሚታገሉትን የእስራኤልን ሕዝብ ማባረር አይችሉም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ሕግ በዚህ ሳምንት መጨረሻ በምክር ቤት ድምጽ እንዲሰጥበት ይፈልጋሉ።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ “በቅርቡ ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር እንደተነጋገሩት ዲሞክራሲያዊ እሴቶች የአሜሪካ እና የእስራኤል ግንኙነት መለያዎች ናቸው። አሁንም መቀጠል አለባቸው” ሲሉ በእስራኤል ባለው ሁኔታ አሜሪካ ስጋት እንደፈጠረባት ተናግረዋል።

በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት “መሠረታዊ ለውጦች” በሰፊ ሕዝብ ድጋፍ ላይ መመሥረት አለባቸው ሲሉም ቃል አቀባይዋ አክለዋል።

የእስራኤል መሪዎች በሚቻለው ፍጥነት መግባባት ላይ እንዲደርሱም አሳስበዋል።