ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል የመሳሪያ ቁጥጥሯን በማላላት ዜጎቿ በቀላሉ እንዲታቀጡ ልትፈቅድ ነው
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ኢየሩሳሌም ውስጥ በፍልስጤማውያን የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ የእስራኤል የደኅንነት ምክር ቤት እስራኤላውያን መሳሪያ በቀላሉ መሳሪያ እንዲታጠቁ የሚያስችል ውሳኔን አሳለፈ።
ጥቃቶቹ የተፈጸሙት የእሳራኤል ሠራዊት ዌስት ባንክ ውስጥ ባካሄደው ዘመቻ ዘጠኝ ሰዎችን ከገደለ በኋላ ነው።
ውሳኔው በተጨማሪም የጥቃት ፈጻሚዎቹ ቤተሰቦች የመኖሪያ እና የማኅበራዊ ዋስትና መብቶቻቸው እንዲገፈፉ የሚያደርግ ነው።
የደኅንነት ምክር ቤቱ ውሳኔ ላይ የእስራኤል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ እሁድ ተወያይቶ የመጨረሻውን ሃሳብ ይሰጥበታል ተብሏል።
ባለፉት ሁለት ቀናት በፍልስጤማውያን ሁለት የተለያዩ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር “ጠንካራ” እና “ፈጣን” ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል።
ኔታኒያሁ “ሽብርተኝነትን ለመዋጋት” አዲስ እርምጃ እንደሚወስዱ የአገሪቱ የደኅንነት ምክር ቤት ከመሰብሰቡ አስቀድሞ በሰጡት አስተያየት ተናግረው ነበር።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በቁጥጥሩ ስር ባለችው ዌስት ባንክ የሚያሰማራውን የወታደሮቹን ቁጥር እንደሚጨምር ገልጿል።
በኢያሩሳሌም ሲልዋን እየተባለ በሚጠራው ሰፈር አንድ የ13 ዓመት ተዳጊ የእስራኤል ዜግነት ያላቸው አባት እና ልጅ ተኩሶ ማቁሰሉን ተከትሎ ነው ፕሬዝዳንቱ አስተያየት የሰጡት።
የ13 ዓመቱ ታዳጊ ወደ ጸሎት እየሄዱ የነበሩ አምስት ሰዎች ላይ የተኮሰ ሲሆን፣ ሁለቱን ለሕይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ እንደጎዳቸው የፖሊስ ቃል አቃባይ ገልጿል። ታዳጊው በሌላ መንገደኛ ተተኩሶበት የቆሰለ ሲሆን ሆስፒታል ገብቷል።
በሌላ በኩል ባለፈው ዓርብ በምሥራቃዊ እየሩሳሌም በአይሁድ ሰንበት የመጀመሪያ ዕለት በአይሁድ ምኩራብ ውስጥ ለጸሎት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ሌላ የተኩስ ጥቃት 7 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ቢያንስ ሦስት ሰዎች ቆስለዋል። ጥቃቱን የፈጸመው ታጣቂም በስፍራው ተገድሏል።
በምኩራቡ ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ከምሥቃዊ እየሩሳሌም የመጣ ፍልስጤማዊ እንደሆነ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከጥቃቱ ጋር በተገናኘ 42 ሰዎችን በእስራኤል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
የእስራኤል ፖሊስ ኮሚሽነር ኮቢ ሻብታይ በጥቃቱ ስፍራ ላይ ሆነው እንደተናገሩት “በቅርብ ዓመታት ካጋጠሙን አስከፊ ጥቃቶች መካከል አንዱ ነው” ብለዋል።
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች የተፈጸመውን ጥቃት ቢያደንቁም፣ ነገር ግን ከአባሎቻቸው አንዱ ስለመፈጸሙ ኃላፊነት አልወሰዱም። በዌስት ባክን እና በጋዛ ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንም ጥቃቱን ደግፈውታል።
ፕሬዝዳንት ኔታኔያሁ ዜጎች እንዲረጋጉ እና የፀጥታ ኃይሎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊቱ ደግሞ ተጨማሪ ወታደሮች እንደሚሰማሩ ገልጿል።
“በድጋሚ በራሳችሁ እጅ ሕግን ለማስከበር እንዳትሞክሩ አሳስባችኋለው” ያሉት ኔታኒያሁ ፕሬዝዳንት ባይደንን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎችን ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።
ባለፈው ማክሰኞ የእስራኤል ጦር አባላት ዘጠኝ የታጠቁና ሲቪል ሰዎች ፍልስጤማውያንን ከገደሉ በኋላ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል።
ይህንንም ተከትሎ ከጋዛ አካባቢ ወደ አስራኤል የሮኬት ጥቃት የተሰነዘረ ሲሆን፣ በምላሹም እስራኤል የአየር ጥቃት ፈጽማለች።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በእስራኤል እና በወረራ በተያዘው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ እየተባባሰ ያለው ሁኔታ በጣሙን እንዳሳሰባቸው በቃል አቀባያቸው በኩል ገልጸዋል።
እስራኤል በ1967 (እአአ) በተካሄደው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ወቅት ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠረች በኋላ ዋና ከተማዋ እንደሆነች ብትገልጽም፣ በአብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅናን አላገኘችም።