የዓለም ዋንጫ፡ የኢራን ተጫዋቾች ብሔራዊ መዝሙራቸውን ሳይዘምሩ ቀሩ

የኢራን ተጫዋቾች

የኢራን ተጫዋቾች በሃገራቸው ያለውን ጸረ መንግስት ተቃውሞ በሚደግፍ መልኩ በዓለም ዋንጫው ከእንግሊዝ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ብሔራዊ መዝሙራቸውን ሳይዘምሩ ቀርተዋል።

ብሔራዊ መዝሙሩ ሲጀምር አንዳንዶች ሲጮሁ ሌሎች ደግሞ “ሴት፣ ህይወት፣ ነጻነት” የሚል ጽሑፍ ከፍ አድርገው አሳይተዋል።

የኢራን ቴሌቪዥን ብሔራዊ መዝመሩ ሲጀምር ቀጥታ ስርጭቱን ገታ አድርጎ ቀደም ብሎ የተቀረጸ የስታዲየሙን ምስል አሰራጭቷል።

ባለፉት ወራት ቴህራን ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ አስተናግዳለች።

የጭንቅላት መሸፈኛ በትክክል አላደረግሽም በሚል በስነ ምግባር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ህይወቷ ያለፈው ማህሳ አሚኒ የተባለች የ22 ዓመት ኢራናዊት ጉዳይ አመጹን ማቀጣጠሉ ይታወሳል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይናገራሉ። 16 ሺህ 800 ሰዎች በጸጥታ ሃይሎች መታሰራቸውን ገልጸዋል።

ተቃውሞዎቹ በውጭ ጠላቶች የተቀናበሩ “አመጾች” ናቸው ሲሉ የኢራን መሪዎች ተናግረዋል።

ኢስላሚክ ሪፐብሊኳን በመተቸት የሚታወቀው የቀድሞ ተጫዋች ስም በማንሳት ደጋፊዎች በእረፍት ሰዓት “አሊ ካሪሚ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ብዙ የኢስላሚክ ሪፐብሊኩ ተቃዋሚዎች ተጫዋቾቹ በይፋ ተቃውሞውን ባለመደገፋቸው እና ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን በማግኘታቸው ሲተቿቸው ነበር።

ከጨዋታው በፊት አስተያየቱን የሰጠው ቡድኑ አምበል ኤህሳን ሃጅሳፊ ተጫዋቾቹ ህይወታቸውን ያጡትን “እንደሚደግፉ” ተናግሯል።

“በጨዋታው መርህ እና በዓለም ዋንጫው ህግጋት መሠረት ከሆነ” ተጫዋቾቹ “የመቃወም ነጻነት” አላቸው ሲሉ አሰልጣኝ ካርሎስ ኬሮዥም ገልጸዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን በመስከረም ወር ሲያከናውን ተጫዋቾች የቡድኑን አርማ ሸፍነዋል።

በእንግሊዝ 6 ለ 2 ከተሸነፉ በኋላ አሰልጣኝ ኬሮዥ ቡድኑ በሃገር ቤቱ አለመረጋጋት ጫና እንዳደረገበት ገልጸዋል።

“እግር ኳሳዊ ያልሆነ ሃሳብ በማምጣት ቡድኑን ለመበጥበጥ የሚመጡትን አናስተናግድም። ምክንያቱም እነዚህ እግር ኳስ ተጫዋቾች ናቸው” ብለዋል ፖርቹጋላዊው።

የኢራን ተጫዋቾች

“ልጆቹ ይጫወቱበት። ዓላማቸው ይህ ነው። እንደሌሎች ቡድኖች ሁሉ ሃገራቸውን እና ህዝባቸውን ለመወከል ይፈልጋሉ።ሁሉም ብሔራዊ ቡድኖች በየሃገሮቻቸው ችግር አላቸው” ብለዋል።

ቀድሞውየማንቸስተር ዩናይትድ ምክትል አሰልጣኝ አክለውም “ኃላፊነታቸው ያልሆንን ነገርመጥቶ በዚህ የዓለም ዋንጫ ወቅት መጠየቅ ተገቢ አይደለም። ለህዝቡ ደስታ እናክብር ለማስገኘት ነው ዓላማቸው።“

“እንደ ተጫዋች ራሳቸውን ለማሳየት በመፈለጋቸው ባለፉት ጥቂት ቀናት ምን ዓይነት ነገሮች እንዳሳለፉ ማሰብ ያቅታችኋል” ብለዋል።

ስለጉዳዩ አስተያየቱን የሰጠው ቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ጋሪ ሊንከር “በጣም ሃይለኛ እና ትልቅ መልዕክት ነው” ብሏል።

“እግር ኳስ ጉልበቱን ለመልካም ነገር ለማዋል እየሞከረ ነው” ሲል ገልጿል።