መምህሮቹ መታሰቢያ ለማቆም የሚጥሩለት ብዙ ያልተነገረለት ተመራማሪ ብሩህተስፋ

ለወትሮው ተማሪዎች ነበሩ ለመምህሮቻቸው ሽልማት የሚያበረክቱት፣ መታሰቢያ የሚያቆሙት።

አሁን ግን ለአንድ ብርቅዬ ተማሪያቸው መታሰቢያ ለማቆም መምህራን ከያሉበት ተሰባስበዋል።

ከተማሪያቸው ከተለዩ ዓመታት ቢነጉዱም አሁንም ግን በልባቸው ነው ያለው።

ለእርሱ አንድ ነገር ካላደረጉ ነፍሳቸው አላርፍ ብሏቸዋል።

ከቀለም ጋር ሲታገል ለነበረው፣ አገርም ሆነ ዓለም ከእሱ ብዙ ያተርፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ለነበረው ልጃቸው።

‘ለመማር’ ያህል ብቻ ላልተማረው፣ የአውሮፓ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮችን አጀብ ላሰኘው የቀለም ቀንድ - ዶክተር ኢንጂነር ብሩህተስፋ ኢብራሒም።

ለዚሁ ልጃቸው ሐውልት ለማቆምና በስሙ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት ለመገንባት ቤተሰቦቹ፣ መምህሮቹ እና ወዳጆቹ ሐምሌ 17/2014 ዓ.ም በተወለደባት አቀስታ ከተማ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ብሩህተስፋ ጨዋታውም ንግግሩም ከወረቀትና ብዕር ጋር ነበር።እንደ ሕጻን ብዙም ጨዋታ እና ቡረቃ አይስበውም፤ አያታልለውም ነበር።

እኩዮቹ ለሚፈነጥዙበት ጉዳይ “አይሞቀውም፤ አይበርደውም” የሚባል ዓይነት ባህሪ ነበረው።

ደግሞም እጅግ የተረጋጋ፣ ቁጥብ፣ ሰው አክባሪ።

ወላጆች “ልጅ ማለት እንደ እሱ!” እያሉ ልጆቻቸውን የሚያበረታቱበት፣ የሚገስጹበት፣ የሚያንጹበት ምሳሌ።

ብሩህተስፋ የፊደል ገበታ ቀርቦለት ያለማንም እገዛ ፊደላትን ገጣጥሞ መጻፍ የጀመረው የአራት ዓመት ህጻን ሳለ ነበር።

በዚህ የተደነቁት መምህራን ወላጆቹ እጁን ይዘው አንደኛ ክፍል ያስገቡት ዕድሜው ለትምህርት ሳይደርስ ነበር።

ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱንም ፉት ብሎ የጨረሰው በአራት ዓመታት ብቻ ነው።

ብሩህተስፋን አንደኛ መውጣት፣ ትምህርት ቤቱን ወክሎ መወዳደር፣ ዞኑን ወክሎ መወዳደር አይደክመውም ነበር። ሁሌም ተሸላሚ። ሁል ጊዜ አንደኛ።

“ይህ ልጅ የሚደርስበትን ማየት ነው። ለዓለም የሚተርፍ ልጅ ነው የሚሆነው” እያሉ ስለ ወደፊቱ መዳረሻው የተነበዩትም በርካቶች ነበሩ።

በእርግጥ ያሉትም አልቀረ።

የአገሪቷ የእውቀት ፍጆታ አልበቃው ብሎ ውቅያኖስ አቋረጠ።

እዚያ በነበረው የትምህርት ቆይታም የአውሮፓን ፕሮፌሰሮችና ተመራማሪዎች ጉድ አሰኝቶ እንደነበር አብረውት የተማሩት ይመሰክራሉ።

በኔዘርላንድስ ሁለተኛ ዲግሪውን ሲከታተል አንድ ዓመት የሚፈጀውን ትምህርት በወራት ውስጥ “አጠናቀሃል፤ ይበቃሃል” ተብሎ እንደነበረም አብሮት ትምህርት ሲከታተል የነበረው ጓደኛው ጌታቸው ተሾመ ያስታውሳል።

የሚያስደንቀው ግን ይህ አይደለም። “በቃህ” ሲባል የእርሱ መከፋት እንጂ።

ምክንያቱን በጠየቁት ጊዜም “እኔ አልጨረስኩም። መስራት የምፈልገው ነገር አለ” የሚል መልስ እንደሰጣቸው ጌታቸው አጋጣሚውን በአግራሞት ገልጾታል።

በወቅቱ ልክ ከፈተና እንደወደቀ ተማሪ ነበር ማባበያ እና ማበረታቻ ያስፈለገው። “ከምንጠብቀው በላይ ሄደሃል። ይበቃሃል” ስለተባለ።

ብሩህተስፋ በርካታ የምርምር ሥራዎቹን ለዓለም አበርክቷል። በርካታ ሽልማቶችንም አግኝቷል።

የእውቀት ጥማቱን ሲያረካ ወደ አገሩ ተመልሶ በተለይ በአፍሪካ ደረጃ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ካምፓኒ የማቋቋም ህልም እንደያዘ ነበር ከዓመታት በፊት በድንገት ሕይወቱ ማለፉ የተሰማው።

ዶ/ር ኢንጂነር ብሩህተስፋ መጋቢት 14፣ 2007 ዓ.ም በተወለደ በ29 ዓመቱ በስዊድን፣ ስቶክሆልም ‘መዋኛ ገንዳ ውስጥ ሰጥሞ ሕይወቱ አልፏል’ የተባለው በድንገት ነበር።

ሞቱ በርካቶችን ያስደነገጠ ቢሆንም አሟሟቱ ግን አሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ታላቅ ወንድሙ ሚካኤል አሰፋ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የምርምር ሥራዎቹም በሰራባቸው ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ ምሥጢር ሆነው እንደሚገኙም ቤተሰቦቹ በቅሬታ ይገልጻሉ።

በዚህ ቁጭት ያደረባቸው ቤተሰቦቹ፣ መምህሮቹ እና ወዳጆቹ ታዲያ ለእርሱ መታሰቢያ ለማቆም ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ።

የብሩህተስፋ የትምህርት ጉዞ

ብሩህተስፋ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ወሎ ዞን፣ ለጋምቦ ወረዳ፣ አቀስታ ከተማ ነው።

ከመምህራን ወላጆቹ የተገኘው ብሩህተስፋ ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ ነበር።

የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በከፊል የተከታተለው በዚያው በተወለደባት ከተማ ነው።

የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ደግሞ ደሴ ከተማ በሚገኘው ወ/ሮ ስኂን ትምህርት ቤት አጠናቋል።

በጉብዝናው ተወዳዳሪ ያልነበረው ብሩህተስፋ፣ በወ/ሮ ስኂን የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቀንን በማስመልከት በፌደራል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በተዘጋጀው ውድድር በአማራ ክልል ካሉ ተማሪዎች ጋር ተወዳድሮ አሸንፏል።

በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናም ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች 'ኤ' በማምጣት፣ አራት ነጥብ ነበር ያስመዘገበው።

ይህንን ውጤቱን ይዞ በ1994 ዓ.ም ጅማ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ። በዚህ ጊዜ እናቱን በሞት አጣ።

ያደረበት ጥልቅ ሐዘን ሳይበግረው በሁሉም ዓመታት ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በኤሌክትሪካል ምህንድስና በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ተሸላሚ ሆኖ መመረቅ ችሏል። ያኔ ገና 21 ዓመቱ ነበር።

ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ የኤሌክትሪካል ምህንድስና ረዳት መምህር ሆኖ ተቀጠረ።

ለሰባት ወራት ከሠራ በኋላም የውጭ ትምህርት ዕድል አግኝቶ በኔዘርላንድስ ደልፍት ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ገባ።

እዚያም የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በቴሌኮሚዩኒኬሽን በማዕረግ በመመረቅ ነበር ያጠናቀቀው።

በወቅቱም ‘GNU' ራዲዮ ላይ የተመሰረተ ራዳርን በመጠቀም በቤት ውስጥ የሚካሄዱ የሰዎችን እንቅስቃሴ መገመት የሚያስችል የምርምር ሥራውን አበርክቷል።

ይህ የምርምር ሥራው በዓለም አቀፍ መድረኮችና በምርምር ህትመቶች ላይ ቀርቧል፤ ተሸልሟል።

ታዲያ በዚህ ጊዜ ነበር በትምህርት አቀባበሉ የተደነቁት የባሕር ማዶዎቹ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች ትምህርት በጀመረ በአስረኛ ወሩ “ይበቃሃል ተመረቅ” ያሉት።

ብሩህተስፋ ቴክኖሎጂ ላይ የመመራመር ጥማቱ በዚህ አልረካም።

በኖርዌጂያን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሦስተኛ ዲግሪውን በከፍተኛ ውጤት አጠናቋል።

የብዝሃ ግብዓት እና ብዝሃ ውጽዓት (Multiple input and Multiple out put) ራዲዮ መስመሮችን ዱካ በመከታተል በምላሽ ላይ በመመራመር አዳዲስ ሳይንሳዊ ጽንሰ ሃሳቦችን በሦስተኛ ዲግሪው ምርምር ፈልስፏል።

ይህ የሞባይልና የራዲዮ ቴክኖሎጂ የምርምር ሃሳቡ ከዚህ በፊት ያልተሰራ በመሆኑም የኤክስኦን ሞባይልስ ምርጥ የፒኤችዲ ምርምር ሥራ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።

በርካታ የምርምር ሥራዎቹም በዓለም አቀፍ የሳይንስ ጋዜጦችና ድረ ገጾች ላይ ታትመዋል።

ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም እጁን ዘርግቶ የተቀበለው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ካምፓኒ ነበር ።

ወደ ስዊድን አቅንቶ የሞባይልና ኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ፣ ኤሪክሰን ውስጥ የምርምር ክፍል ልምድ ያለው ተመራማሪ በመሆን ተቀጠረ።

ሕይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስም ከአንድ ዓመት በላይ እዚያው ኤሪክሰን አገልግሏል።

ሕይወቱ ያለፈው ከኤሪክሰን ኩባንያ የሥራ መልቀቂያ ጠይቆ ለተሻለ ሥራ ወደ ኖርዌይ ለመሄድ ዕቃውን ሸክፎ በተሰናዳበት ወቅት ነበር።

“ሰኞ ዕለት የሥራ ባልደረቦቹ ሸኝተውት፣ በስቶክሆልም ያሉ ወዳጆቹና ጓደኞቹም ሸኝት አድርገውለት፣ረቡዕ ወደ ኖርዌይ ሊበር ማክሰኞ ዕለት ነው መዋኛ ገንዳ ውስጥ ሰጥሞ የመሞቱ መርዶ የተሰማው” ይላል ታላቅ ወንድሙ ሚካኤል ።

ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ፣ ከኩባንያው በለቀቀ ማግስት መዋኛ ገንዳ ውስጥ ሰጥሞ ሞተ የሚለው ዜና እስካሁን ድረስ አልተዋጠላቸውም።

ምክንያታቸውን ሲያስረዱም “ብሩህተስፋ አስተዋይ፣ ጠንቃቃ፣ የተረጋጋ እና የሚያደርገውን የሚያውቅ ነው” ይላሉ።

ከብሩህተስፋ የምርምርና የሕትመት ሥራዎች ጥቂቶቹ

ብሩህተስፋ ከአገር ውጭ፣ በፊሊፕስ ኩባንያ፣ በኤሪክሰን፣ እንዲሁም በኖርዌጂያን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተመራማሪነት እና በመምህርነት አገልግሏል። ብሩህተስፋ ከሠራቸው የምርምር ሥራዎች መካከል፡

  • ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሶፍትዌር ላይ የተመሰረተ ‘ኤኤም’ ራዲዮ መቀበያ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ምርምር
  • በGNU ራዲዮ ላይ የተመሰረተ ራዳርን በመጠቀም በቤት ውስጥ የሚካሄዱ የሰዎችን እንቅስቃሴ መገመት የሚያስችል የምርምር ሥራን አበርክቷል። በዚህ የምርምር ሥራ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመለየት፣ ለመጠቆም፣ ለመመደብ የሚያስችል በዶፕለር ራዳር ላይ የተመሰረቱ የሲግናል ፕሮሰሲንግ አልጎሪዝሞችን ዲዛይን አድርጓል።
  • የብዝሃ ግብዓት እና ብዝሃ ውጽዓት ( Multiple input and Multiple out put) ራዲዮ መስመሮችን ዱካ መከታተል፣ በርካታ አንቴናዎችን በመጠቀም ገመድ አልባ ኮሚዩኒኬሽንን የሚያሳልጥ ምርምር ሠርቷል።
  • ለቻናል ዛፒንግ ልኬታ የኢንተርኔት ፕሮቶኮል ቴሌቪዥን ፕሮቶታይፕ አበልጽጓል። ይህ የምርምር ሥራው የቴሌቪዥን ተመልካቾች ቻናል በሚቀያይሩበት ጊዜ የሚኖረውን መዘግየት እና የሚታየውን ጥቁር ገጽ ጠቃሚ መረጃዎችን ለማስተላለፍ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ያሳየ ነው።
  • በኢንተርኔት ፕሮቶኮል ቴሌቪዥን የልምድ ጥራት ማረጋገጫ ሞዴሎችን ቀርጿል።
  • ከዚህም ባሻገር በሲግናል ፕሮሰሲንግ፣ ራዳር እና በገመድ አልባ ግንኙነቶች አምስት የሕትመት ሥራዎች በዓለማችን ግዙፍ በሆነው የኤሌክትሪካል እና ኤሌክትሮኒክስ ተቋም [IEEE] ድረ ገጽ እና ጋዜጦች ላይ ከ10 በላይ የተመረመሩ የኮንፈረንስ ሕትመቶችን አቅርቧል።

በስዊድን አገር የሞባይልና ኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያው ኤሪክሰን፣ በ13 ወራት ውስጥ፣ ስድስት ለብቻው፣ አራት ከሌሎች ጋር በመሆን 10 የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ መብቶች ማግኘቱን እና ጥቂቶቹ በሂደት ላይ እንደነበሩ ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ ተናግረዋል።

በርካታ የቴክኖሎጂ ምርምር ሥራዎችን ያበረከተው ብሩህተስፋ፣ በባሕርዳር የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ ፣ የኢንጂነሪንግ እና የሒሳብ ማበልጸጊያ ማዕከል ውስጥ በምሳሌነት ፎቶግራፋቸው ከእነ ታሪካቸው ተሰንዶ ከተቀመጡት አልበርት አንስታይን እና ኢንጂነር ቅጣው እጅጉን ጨምሮ ሌሎች የዓለም ሳይንቲስቶች ተርታ ምስሉ ከነግብሩ በጉልህ ተሰቅሏል።

በኔዘርላንድስ አብሮት ትምህርቱን ሲከታተል የነበረው ጓደኛው ጌታቸው፣ብሩህተስፋ በጉብዝናውና በባህሪው እጅግ የሚያስደንቀው ተማሪ እንደነበር ይናገራል።

"ብሩህተስፋ መውሰድ የነበረበትን ኮርስ በአጭር ጊዜ ካጠናቀቀ በኋላ ከሌሎች ተማሪዎች ቀድሞ ባቀረበው የምርምር ሥራው ከፍተኛ ውጤት ነበር ያገኘው" ይላል።

የምርምር ሥራው የራዲዮ ሞገድ ተጠቅሞ የሰዎችን እንቅስቃሴ መለየት የሚያስችል ነበር።

አሁን ዓለም ላይ ባለው ቴክኖሎጂ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለማወቅ አገልግሎት ላይ የሚውለው ካሜራ ነው።

ይህ ደግሞ ከግለሰቦች መብት ጋር ተያይዞ ትችት ይቀርብበታል።

ብሩህተስፋ በዚህ የምርምር ሥራው ያለመው ይህንን ችግር ለመፍታት ነበር። ያለ ካሜራ ራዲዮ ሞገድን (ራዳርን) በመጠቀም የሰዎችን እንቅስቃሴ መለየት የሚያስችል ምርምር ነበር የሠራው።

ይህ የፈጠራ ሥራው ታዋቂው የሳይንስ መጽሔት ኤ ትሪፕል ጆርናል ላይ ታትሟል።

“ብዙ ጊዜ ብሩህተስፋ በሚያገኘው ውጤት አይረካም” የሚለው ጌታቸው፣ ሌላው ሰው አርኪ ነው ብሎ የሚያስበው ለእርሱ አያስደስተውም።ምን አልባት ካለው አቅም አንጻር እያነሰው ይሆናል” ይላል።

ጌታቸው፣ ብሩህተስፋ ኤሪክሰን እያለ በርካታ የምርምር ሥራዎች እንደሠራ ጠቅሶ፣ “ምን አልባት አንድ ቀን ካምፓኒው የምርምር ሥራዎቹን ለዓለም ያሳውቅለት ይሆናል፣ አሊያም እዚያው ምሥጢር አድርጎ ያስቀራቸው ይሆናል” ሲልም አክሏል።

“ፈተና የምናርመው በእርሱ የፈተና ወረቀት ነበር”

ማተቤ አዲስ ብሩህተስፋን ከ7ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ፕሮዳክቲቭ ቴክኖሎጂ እና የሒሳብ ትምህርት አስተምረውታል።

ሞባይልና ኮምፒዩተር ባልነበረበት ዘመን ትልቅ የቴክኖሎጂ ፍላጎት እንደነበረው የቀድሞው መምህሩ ማተቤ ያስታውሳሉ።

በዚህም ትልቅ ተመራማሪ ሊሆን እንደሚችል ይገምቱ ነበር።

“ብሩህተስፋ አይሳሳትም” የሚሉት ማተቤ፣ ፈተና የሚያርሙት በእርሱ የፈተና ወረቀት እንደነበር ያወሳሉ።

“የረጋ ስሜት አለው። አይቆጣም፣ አይረብሽም፣ አስተማሪ አይንቅም። በተማርኩባቸውም ሆነ ባስተማርኩባቸው ትምህርት ቤቶች የእርሱን ዓይነት ተማሪ አላጋጠመኝም” ይላሉ።

ብሩህተስፋ በጥያቄ ይፈትናቸው እንደነበር የሚናገሩት ማተቤ፣ እርሱን ለማስረዳት “የማስተምረውን ትምህርት በድጋሜ ለማጥናት እገደድ ነበር” ብለዋል።

ማተቤ የብሩህተስፋን ሕልፈተ ሕይወት የሰሙት በማኅበራዊ ሚዲያ ነበር።

“ከረበሹኝ መርዶዎች የከፋው የእርሱ ሕልፈት ነበር” ብለዋል።

ከተበረከቱለት ሽልማቶች ጥቂቶቹ

  • ኖርዌጂያን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ምርምር ጥናት አሸናፊ ሆኖ የኤክሶን ሞባይል ሽልማትን በመውሰድ የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪውን አግኝቷል። ያኔ ገና 27 ዓመቱ ነበር።
  • የሴንሰር መሣሪያዎች ኮንፈረንስ ምርጥ የምርምር ሥራ ሕትመት ሽልማትን ወስዷል።
  • የአምስተኛው አይካስ ኮንፈረንስ ምርጥ የምርምር ሥራ ተሸላሚ መሆን ችሏል።
  • በሰሜን አሜሪካ የኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ድርጅት የሆነው ኢዊ [EWI] የትምህርት ዕድል ተሸልሟል።
  • በኔዘርላንድስ ትዩ ደልፍት ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቃን የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚም ነበር።
  • በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ትምህርት የመጀመሪያ ድግሪ ምሩቃን በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳሊያውን የግሉ አድርጓል።

የመታሰቢያ ሐውልትና የሕዝብ ቤተ መጻሐፍት

ቤተሰቦቹ፣ መምህሮቹና ወዳጆቹ እስካሁን ለእርሱ አንዳች መታሰቢያ ባለመቀመጡ ይቆጫሉ።

በተለያየ ጊዜ ቤተሰቦቹ እና ጂማ ዩኒቨርሲቲ አብረውት የተማሩ ጓደኞቹ ፋውንዴሽን በማቋቋም ለእርሱ መታሰቢያ ለማቆም ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ ነገር ግን እንደታሰበው አልሄደላቸውም።

አሁን ግን ከያሉበት የተሰባሰቡት መምህሮቹ እና ወዳጆቹ ለዓለም የተረፈው ጉብዝናው ቢያንስ በተማረበት አካባቢ ለሚገኙ ትውልዶች ምሳሌ ይሆን ዘንድ መታሰቢያ ለማቆም ደፋ ቀና እያሉ ነው።

በዶ/ር ኢንጂነር ብሩህተስፋ ስም የመታሰቢያ ሐውልትና የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት ለማሰራት የአቀስታ ከተማ አስተዳዳር በሰጣቸው ቦታ ላይ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ለማሰሪያውም ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ እየሰሩ እንደሆነ ከፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት መምህር ማተቤ አዲስ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ ብሩህተስፋ ከቤቱ ተነስቶ ወደ ትምህርት ቤት ይጓዝበት የነበረውን አውራ ጎዳና በስሙ ሰይሞለታል።

የፕሮጀክቱ ዓላማም “ሌሎች ብሩህተስፋዎች እንዲፈጠሩ፣ ጥሩ ሥራ የሰሩ ሰዎች ታሪክ መነገር እንዳለበት፣ ለሌሎች ምሳሌ መሆን እንዳለበት። መማሪያ እንዲሆን ነው” ብለዋል ማተቤ።

“የዚህ ልጅ ታሪክ ሲዳፈን መምህራን ተቀምጠው ማየት አለባቸው ብዬ አላምንም” የሚሉት አስተማሪው፣ ይህንን ባያደርጉ አደራ እንደበሉ እንደሚቆጥሩትም ተናግረዋል።