ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ 'አቀነባባሪ' የፍርድ ሂደት በጊዜያዊነት ቆመ
የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ በዋነኝነት አቀነባብረዋል የሚባሉት ፌሊሴ ካቡጋ በሄግ እየተካሄደ ያለው የፍርድ ሂደት በጊዜያዊነት ቆመ።
የ90 ዓመቱ ካቡጋ በሄግ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት እየተዳኘ ይገኛል።
ጠበቆቻቸው የመርሳት ህመም ስላለበት ፍርድ ለመቅረብ ብቁ አይደለም ማለታቸውንም ተከትሎ ነው በጊዜያዊነት የቆመው።
ካቡጋ ከ26 ዓመታት ዓደን በኋላ ነው ከሶስት ዓመታት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለው።
የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጤንነቱ እስኪገመገም የፍርድ ሂደቱ በጊዜያዊነት እንዲቆም ተስማምቷል።
ፈሊሴ ካቡጋ የኢንተርሃምዌይ ሚሊሻዎች የመንፈስ አባት ይሉታል።
ያኔ የተገደሉት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሃቢያሪማና የቅርብ ወዳጅም ነበር። ቤተሰብም ነበር፤ በጋብቻም ተሳስሯል።
በዚያ ዘመን እጅግ የናጠጠው የሩዋንዳ ዜጋም ፈሊሴ ካቡጋ ነበር።
ሻይ ቅጠል ንግድ የእርሱን ያህል የነገደ አፍሪካዊ አልነበረም።ከፍተኛ ሃብትም አካብቷል።
ካቡጋ በጣም አስፈሪ፣ በጣም ጨካኝ፣ በጣም ጉልበተኛ እንደነበር ይነገራል።
የሁቱ ጨፍጫፊዎችን አስታጥቆ ያደራጀ፣ ለቱትሲዎች መጨፍጨፊያ ይሆን ዘንድ ካራ ከነመሞረጃው ወደ አገር ቤት በገፍ ያስገባው እርሱ ነበር ይባላል።
የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ይነዛ የነበረው አርቲኤልኤም (RTLM) ራዲዮ ጣቢያ ባለቤትም ነበር።
ፈሊሴ ካቡጋ በዘር ማጥፋት ወንጀል ከሚፈለጉት ሰዎች ቁጥር አንዱ ብቻም ሳይሆን አየሁት ለሚል 5 ሚሊዮን የሚያሸልም ውድ ወንጀለኛ ነበር።
ካቡጋ በሃሰተኛ ማንነት በፓሪስ ውስጥ በሚገኝ አፓርታማ ውስጥ ይኖር እንደነበር የደረሱበት የፈረንሳይ መርማሪዎች ናቸው።
28 የተለያዩ ማንነቶችና ስሞች ነበሩት።
በሁለት አህጉሮች ውስጥ ሲሽሎኮሎክ ቆይቷል።
በአፍሪካና በአውሮፓ ምናልባትም እጅግ ቁልፍ ከሚባሉ ሹሞች ጋር ተመሳጥሯል።
ማንነቱና 'የት'ነቱ ሳይደረስበት እንዲቆይ ሀብቱን አፍስሷል።
ከዘር ጭፍጨፋው የተረፉ ሩዋንዳውያን ካቡጋ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ሊሞት ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል። የፍርድ ሂደቱ ዓመታትም እንደሚወስድ ይጠበቃል።