የሶማሌ ክልል በሶማሊላንድ ግጭት ውስጥ እየተሳተፈ ነው መባሉን አስተባበለ

የሶማሌ ክልል ሁለት መቶ ዜጎች በተቀጠፉበት ነጻ አገርነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ ግጭት የክልሉን ወታደሮች በመላክ ድጋፍ እየሰጠ ነው መባሉን አስተባበለ።

የሶማሊላንድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በላስ አኖድ ግጭት እየተዋጋቸው ያሉ የጎሳ ታጣቂዎችን የሶማሌ ክልል ጦር ልኮ ድጋፍ እየሰጠ ነው ማለቱን ተከትሎ ነው ክልሉ ክሱን እንደማይቀበለው መግለጫ ያወጣው።

“የሶማሌ ክልል ጦር በላስ አኖድ ግጭት ውስጥ እንደሌለ ለሶማሊላንድ አስተዳደር ነግረናቸዋል” በማለት የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሐሙስ ጥር 30/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ነጻ አገርነቷን ባወጀችው በሶማሊላንድ መንግሥት እና በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ስር መተዳደር እንፈልጋለን በሚሉ የጎሳ አመራሮች ከአንድ ወር በፊት በተነሳው ግጭት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ ዶሎ ግዛት ገብተዋል።

ሶማሊላንድ፣ የሶማሌ ክልል እና ፑንትላንድ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር ጦራቸውን ግጭት ወደተነሳበት ላስ አኖድ ልከዋል ስትል ከሳለች።

የሶማሊላንድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 30/2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ አንድ ግዛት የሆነው የሶማሌ ክልል ግጭቱን ከማቀጣጠል እንዲቆጠብ እና ጦሩንም እንዲያስወጣ ጠይቋል።

“የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኃይሎችን ጨምሮ ሌሎች ኃይሎች ከላስ አኖድ እንዲወጡ እናሳስባለን” በማለትም የሶማሊላንድ መንግሥት በመግለጫው ጠይቋል።

የሶማሌ ክልል ከሶማሊላንድ አስተዳደር ለሚቀርቡ ተከታታይ ውንጀላዎች ምላሽ ላለመስጠት ሞክሯል ያለው ክልሉ ክሱን “ግዴለሽ” በማለት አውግዟል።

ሶማሊላንድ “በሌሉ ጠላቶችን ላይ ጣቷን በመቀሰር እየደረሰባት ያለውን የፖለቲካ ጫና አቅጣጫ ለማስቀየር እየሞከረች ነው” ብሏል።

በተጨማሪም የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ወንድማማች በሆነው የሶማሊላንድ እና የክልሉ ሕዝቦች መካከል ጥላቻ ሊፈጥሩ ከሚችሉ አስተያየቶች እና ድርጊቶች እንዲቆጠቡም ክልሉ አሳስቧል።

ይህ መግለጫ የወጣው የሶማሌ ክልል በሶማሊላንድ ያለውን ግጭት ለመፍታት በግንባር ቀደምትነት የአሸማጋይነት ሚና እየተወጣ ባለበት ጊዜ መሆኑም ተዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት የክልሉ አሸማጋዮች በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት መተዳደር እንፈልጋለን የሚሉት የሱል፣ ሳናግና ካይን የጎሳ መሪዎችን ለየብቻቻቸው ማናገራቸውም ተገልጿል።

ከተቀረው የሶማሊያ ክፍል በተለየ በተረጋጋ ሁኔታ በሰላም ውስጥ የቆየችውን የሶማሊላንድን ሰላም ያደፈረሰው ግጭት የተቀሰቀሰው በአወዛጋቢዋ ግዛት ላስ አኖድ ውስጥ ነው።

ግዛቲቱ ዋነኛ የንግድ መስመር ስትሆን ሶማሊላንድ እና ቀሪው አጎራባች በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ስር ያለችው ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደሯ ፑንትላንድ በይገባኛል ሲወዛገቡባት ቆይተዋል።

ከወራት በፊት ደግሞ በላስኖድ ከተማ ለተፈጸሙ ተከታታይ ግድያዎች የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ምንም አይነት የተጠያቂነት እርምጃ ባለመስፈናቸውም ሕዝቡን እንዲሁም የጎሳ መሪዎችን አስቆጥቷል።

በተለይም ታኃሣሥ ወር ላይ አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ መገዳላቸውን ተከትሎ የሶማሊላንድ መንግሥት ደኅንነት ማስጠበቅ አልቻለም በሚል ተቃዋሚዎች የሶማሊያን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለቡ።

የሶማሊላንድ የፀጥታ ኃይሎችም ለተነሳባቸው ተቃውሞ በሰጡት ምላሽ 20 ሰዎች መግደላቸው ተዘግቧል።

ጥር ወር ላይም በአካባቢው በአብዛኛው ነዋሪ የሆኑት የዱልብሃንቴ ጎሳ ሚሊሻ መታጠቃቸው ተሰምቷል።

የጎሳው መሪ ጋራድ ጃማ ጋራድ አሊ የሶማሊላንድ ምሥራቃዊ ክፍል የሆኑት ሱል ሳናግ እና ካይን ክልሎች ተወካዮች ጋር በላስ አኖድ ስብሰባ ጠሩ።

የሶማሊላንድ ግዛት 20 በመቶ የሚሆነውን የሚወክለው ይህ ጥምረት ሶማሊያን ለመቀላቀል እና በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት መመራት እንፈልጋለን የሚል መግለጫም አወጡ።

የጎሳዎቹ መሪዎች መግለጫ በሶማሊላንድ ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን የአገሪቱ ባለሥልጣናትም ከተማዋ በከባድ መሳሪያዎች እንድትከበብ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተነግሯል።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግጭቱን ከጽንፈኛ ቡድኖች ጋር የተባበሩ ፀረ ሰላም ሚሊሻዎችን ተጠያቂ አድርጓል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድን ጨምሮ በርካታ አገራት በሁለቱ ኃይሎች መካከል ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የተበባሩት መንግሥታትም በላስ አኖድ የተፈጠረው ግጭት ረግቦ እልባት እንዲያገኝ እና ዜጎችም ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ጠይቋል።

ሶማሊላንድ በግዛት አንድነት ላይ አልደራደርም በማለት የጸናች ሲሆን ላስ አኖድ፣ ሱል እና ሳናና ክልሎች የአገሪቱ ግዛት አካል ናቸው ብላለች።

የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ከቀናት በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸውን ቢገልጹም፣ ከቀናት በኋላ ሶማሊያ በጦር ኃይሏ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ሲሉ ከሰዋል።

ሶማሊያ ለቀረበባት ክስ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠችም።