ከባድ አውሎ ነፋስ በመላዋ ኩባ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ አደረገ

በኩባ ያጋጠመው ከባድ አውሎ ነፋስ በመላው አገሪቱ ኤሌክትሪክ እንዲቋረጠ ምክንያት መሆኑን መንግሥት አስታወቀ።

በኩባ ከሚገኙ ከዋነኞቹ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች መካከል አንዱ የሆነው በከባድ አውሎ ነፋሱ ምክንያት ወደ አገልግሎት መመለስ ባለመቻሉ በአገሪቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተቋርጧል።

በአውሎ ንፋሱ 2 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ህንጻዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። በሦስተኛ ምድብ የሚቀመጠው እና ‘ኢያን’ የተሰኘው አውሎ ንፋስ በሰዓት 195 ኪሎ ሜትር የሚከንፍ ነው።

ትላንት ማክሰኞ የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ኃላፊ በኩባ ብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው 11 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ከኃይል ጋር የተቆራረጠበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ሥርዓቱ በመቋረጡ ነው ብለዋል።

የብሔራዊው ቴሌቪዢን ጣቢያው ጋዜጠኛ በአገሪቱ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለመኖሩን ገልጿል።

ከዋና ከተማዋ ሃቫና 100 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምተገኘው ማታንዛ የሚገኘው አንቶኒዮ ጉይትረስ የኤሌክትሪክ ማመንጫ በኩባ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ውስጥ እጅግ ወሳኙን ድርሻ የሚወስድ ነው። ነገር ግን ይህ ማመንጫ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን ተዘግቧል።

የማመንጫው ኤሌክትሪክ አለማቅረብ ደግሞ በመላው ኩባ መቶ በመቶ ኤሌክትረክ እንዳይኖር ምክንያት ይሆናል ተብሏል።

ታዋቂ የሆነው ፊንካ ሮቢና ሲጋራ አምራች በትምባሆ እርሻው ላይ በአውሎ ነፋሱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ፎቶ “ከባድ ጥፋት” ከሚል ጽሁፍ ጋር አጋርቷል።

የአየር ጸባይ ትምበያዎች በኩባ አንዳንድ አካባቢዎች ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር። 

ማይለን ሱዋራዝ የተባለች ነዋሪ አውሎ ነፋሱ ሰኞ ዕለት ያስከተለው አደጋ በሕይወቷ ከባዱን እንድታሳለፍ አድርጓታል።

“የቤታችን ጣሪያ ሙሉ በሙሉ ተገንጥሎ ሄዷል ማለት ይቻላል። ልጄ፣ ባለቤቴ እና እኔ የቀረው ጣሪያ እንዳይሄድ በገመድ አስረነዋል” ብላለች።

ጉዳት የደረሱባቸውን አከባቢዎች የጎበኙት የኩባ ፕሬዝዳንት ዲያዝ ካኔል በትዊተር ገጻቻው ላይ አገራቸው ከችግር በኋላ እንደምትነሳ ቃል ገብተዋል።