ቦሪስ ጆንሰን የካቢኔ አባሎቻቸው ሥራ መልቀቃቸውን ተከትሎ ጫና በረታባቸው

የዩናይትድ ኪንግም (ዩኬ) ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው አስተዳደራቸውን ተችተው ሥራ መልቀቃቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ እና የጤና ሚኒስትር የነበሩት ሳጂድ ጃቪድ በ10 ደቂቃ ልዩነት ሥራቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ተቺዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ሕይወት “አብቅቶለታል” ያሉ ሲሆን ሌበር ፓርቲ ደግሞ የቦሪስ ጆንሰን አስተዳደር በብልሹ አሰራር የተሞላ ነው ብሏል።

በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ እያለፉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 29/2014 ዓ.ም. ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በፓርላማ ይገኛሉ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የመተማመኛ ድምጽ የተሰጠባቸው ቦሪስ ጆንሰን፤ ምንም እንኳ ተቃውሞ ቢበዛባቸውም በሥልጣናቸው እንደሚቆዩ ገልጸዋል።

ሥልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው በለቀቁት ሁለቱ የካቢኔ አባላት ምትክም ሌሎች ፖለቲከኞችን ሾመዋል።

የጤና ሚኒስትር የነበሩት ሳጂድ ጃቪድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ብሔራዊ ጥቅምን ባማከል ሁኔታ አገር እየመራ አይደለም ሲሉ፤ የገንዘብ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ሕዝቡ መንግሥት አገሪቱን በአግባቡ እንዲያገለግል ይጠብቃል ብለዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የቦሪስ ጆንሰን ካቢኔ አባላት ሁለቱን ግለሰቦች በመከተል ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ወግ አጥባቂው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አንድር ሚሼል የቦሪስ ጆንሰን ጉዳይ “አብቅቶለታል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምንም እንኳ የምክር ቤት አባሉ ይህን ይበሉ እንጂ፣ አሁንም በርካታ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላት ድጋፋቸውን ለቦሪስ ጆንሰን እንደሰጡ ናቸው።

ከእነዚህም መካከል ቦሪስ ጆንሰንን በመተካታ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ የመሆን ዕድል አላቸው የሚባሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሯ ሊዝ ትረስ ይገኙበታል።

ሚንስትሯ፤ 100 ፐርሰንት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፌን እስጣለሁ ብለዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶሞኒክ ራብ እና መከላከያ ሚኒስትሩ ቤን ዋላስ በሥራቸው እንደሚቀጥሉ ከገለጹት መካከል ይገኙበታል።