በኬንያ ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ኡሁሩን እርሻ አቃጠሉ

በኬንያ ለተቃውሞ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቤተሰብ ንብረት የሆነ የእርሻ መሬት ላይ እሳት መስደዳቸው ተሰማ።

ተቃዋሚዎቹ ሰኞ መጋቢት 18/2015 ዓ.ም ይህንን ያደረጉት ከሳምንት በፊት በራይላ ኦዲንጋ በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ለተፈጠረው አጸፋዊ ምላሽ ነው ተብሏል።

ከናይሮቢ ወጣ ብሎ በሚገኘው የኡሁሩ የእርሻ መሬት ላይ የነበሩ በጎችንም ተቃዋሚዎቹ ሲሰርቁ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ተመልክቷል።በአካባቢው ፖሊስ ያልነበረ ሲሆን አንዳንዶቹም ሜንጫ ይዘው ነበር።

ሌሎች ተቃዋሚዎች ዛፎችን እየቆረጡ እንደነበር የቢቢሲ ጋዜጠኛ የተመለከተ ሲሆን በርካቶችም በአውቶብስ ተጭነው ነበር።

በእርሻ ስፍራው አቅራቢያ እንዲሁም በናይሮቢ በርካታ የንግድ ተቋማት ቀኑን ሙሉ ዝግ ሆነው ውለዋል።

ከተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ጋር ግንኙነት ያለው የጋዝ ፋብሪካም ጉዳት ደርሶበታል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አጋር የሆኑት ራይላ በኡሁሩ እርሻ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በመንግሥት በተቀጠሩ ዘራፊዎች የተደረገ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኬንያ መንግሥት በቀረበበት ክስ ላይ የሰጠው ምላሽ የለም።

ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ባደረገችው ኬንያ ውጤቱን ተከትሎ የሚነሳ ሁከትና ብጥብጥ አዲስ ነገር አይደለም።

ነገር ግን በፖለቲካ መሪዎች ንብረት ላይ ጥቃት መድረሱ አዲስ ስልት ነው ተብሏል።

በየሳምንቱ ሁለት ቀናት ሰኞ እና ሐሙስ እንዲደረግ በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ በትናንትናው ዕለት ቢያንስ አንድ ሰው ተገድሏል።

የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈው የራይላ መሰረት ነው በምትባለው ምዕራብ ኪሱሙ ሲሆን ተቃዋሚዎች ጎማ አቃጥለው ዋና ዋና መንገዶችን ዘግተው ነበር ተብሏል። የጸጥታ ኃይሎችም ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸው ተሰምቷል።

ተቃውሞው ከጀመረበት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ቢያንስ የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፏል።

የራይላ ከፍተኛ ድጋፍ ባለባት በናይሮቢዋ ኪቤራም ሰፈር ፖሊስ ድንጋይ በሚወረውሩ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።

ራይላ ኦዲንጋና እሳቸው የሚመሩት አዚሚዮ ላ ኡሞጃ የተባለው የፓርቲዎች ጥምረት መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለመግታት አልቻለም እንዲሁም ፕሬዚዳንት ሩቶ ያሸነፉበት ምርጫ የተጭበረበረ ነው በሚልም ነው ከወር በፊት ተቃውሞ የጠሩት።

ምንም እንኳን የምርጫ ውጤቱ በኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተረጋገጠ ቢሆንም ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል በየሳምንቱ ሰኞ እና ሐሙስ የሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎችን ጠርተዋል።