ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጉግል እና ኦራክል በሙቀት ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ አጋጠማቸው
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ አብዛኛው የዩናይትድ ኪንግደም ክፍል ከፍተኛ በሆነ የሙቀት ማዕበል መመታቱን ተከትሎ ግዙፎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጉግል እና ኦራክል በለንደን የመረጃ ማዕከላቶቻቸው የአገልግሎት መቋረጥ አጋጥሟቸዋል።
ይህም ግዙፍ የመረጃ ማከማቻ ቋቶቻቸውን ለማቀዝቀዝ የሚያገለግሉ ስርአቶች ከመጠን ባለፈው የሙቀት ጫና ምክንያት ስራ በማቆማቸው ነው። ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ኦራክል ማክሰኞ ከ ቀኑ 10 ሰአት በፊት የሙቀት መጨመር ችግሮች መከሰቱን አስታውቆ ነበር።
እነዚህ ግዙፍ የመረጃ ቋቶች ከፍተኛ ሙቀት የሚያሚያመነጩ ሲሆን ይህም ከበጋው ሙቀት ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ የማቀዝቀዝ ሃይል ይፈልጋል።
"በደቡባዊ ዩናይትድ ኪንግደም ማለትም ለንደን ውስጥ ወቅቱን ያልጠበቀ ከፍተኛ ሙቀት መከሰቱን ተከትሎ በመረጃ ማዕከሉ ውስጥ ያሉ ሁለት ቀዝቃዛ ክፍሎች ከገደባቸው በላይ እንዲሰሩ በመገደዳቸው ስራ አቁመዋል" ሲል ኦራክል አስታውቋል።
ይህንንም ተከትሎ በመረጃ ማእከሉ ውስጥ ያለው የሙቀት መጠን በመጨመሩ አንዳንድ ስርዓቶችን እንደ ቅድመ ጥንቃቄ የመዝጋት እርምጃ መወሰዱንም አክሏል።
ኩባንያው በማግስቱ ረቡዕ ጠዋት አራት ሰአት ይፋ ባደረገው መረጃ ችግሩ እንደተፈታ ይፋ አድርጓል።
ተመሳሳይ ችግር ያጋጠመው የጉግል ክላውድ የለንደን የመረጃ ማዕከል በአንደኛው የድርጅቱ ህንጻ ውስጥ ከማቀዝቀዣ ጋር የተያያዘ ችግር መፈጠሩን ይፋ አድርጎ ነበር። በማሽኖች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እና ለረጅም ግዜ የመጥፋት አደጋን ለመከላከል ኩባንያው የተወሰኑትን ቀድሞ ማቆሙን ገልጿል።
ችግሩ ረቡዕ ጠዋት አንድ ሰአት ላይ አካባቢ መፈታቱን ያከለው ጉግል "የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ደንበኞቻችን ብቻ ላይ ችግሩ መስተጓጎል ፈጥሮ ነበር’’ ሲልም ገልጿል።
ባለሞያዎች እንደሚሉት እነዚህ ዘመናዊ የሆኑ ስርአቶች እንዲህ በቀላሉ የማይሰተጓጎሉ ብሎም አሁን ተቋማቱ እያጋጠማቸው ያለው ችግርም አስደናቂ እንደሆነ ይገልጻሉ።
እንዲህ ያሉ ሞቃት ቀናት በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ ባለሞያዎች ያስረዳሉ። ይህም ተጨማሪ የማቀዝቀዣ ስርአቶችን የሚጠይቅ ሲሆን ይህንን ለማድረግ ደግሞ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ይጠይቃል። ይህንን ተከትሎ የካርበን ልቀት መጠን የሚጨምር ይሆናል።
የአየር ንብረት ሳይንቲስቶች እነዚህ ሞቃታማ ቀናት እየበዙ እንደሚሄዱ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተጨማሪ አየርን የማይበክሉ መፍትሄዎችን ብሎም አነስተኛ ኃይልን በመጠቀም አነስተኛ ሙቀትን የሚያመነጩ የኮምፒተር ስርዓቶችን እየፈለጉ ነው።
ማይክሮሶፍት እ.ኤ.አ. በ 2020 በባሕር ውሃ በመከበብ ተጨማሪ ተፈጥሯዊ የማቀዝቀዣ ስርአትን ለመጠቀም በሚል ከኦርክኒ አቅራቢያ በሚገኘው የውሃ ውስጥ የመረጃ ማእከል ሙከራ ማድረጉ ይታወሳል።