ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን የሚገኘው ታሪካዊ መስጊድ በጥገና ወቅት ጉዳት ደረሰበት
ልዩ የሆነ የስነ-ህንጻ ጥበብ የተንጸባረቀበት በሚል የሚሞገሰው እና በ17ኛው ክፍለ ዘመን በኢራን ኢስፋሃን የተገነባው ሻህ መስጊድ በጥገና ወቅት ጉዳት እንደደረሰበት የኢራን ባለስልጣናት አመኑ።
የዩኔስኮ የአለም ቅርስ ተደርጎ የተመዘገበው ሻህ መስጊድ በኢራን ውስጥ እጅግ ውብ መስጊድ እንደሆነ ይነገርለታል።
እደሳው ከተጀመረ በኋላም መዛነፎች የታዩ ሲሆን የመስጊዱ መገለጫ ተደርገው ከሚታወቁት ክፍሎች ውስጥ የአበባ ምስሎቹ የማይመሳሰሉ መሆናቸውን በቅርቡ ከስፍራው የወጡ ምስሎች ያሳያሉ።
የኢራን ባለስልጣናትም የተፈጠረውን ጉድለት ያመኑ ሲሆን መፍትሄ ሊሰጣቸው የሚችሉ ናቸው ሲሉም ተከላክለዋል።
የፕሮጀክቱን እደሳ እየሰራ የሚገኘው ተቋም የፕሮጀክት ሃላፊ የሆኑት መህዲ ፓክዴል በበኩላቸው ስራው ገና አልተጠናቀቀም ሲሉ ተናግረዋል።
ለስራውም ጥቅም ላይ በሚውሉት የስካፎልዲንግ መዋቅሮች ማለትም ጠጋኞች የሚቆሙባቸው የመረገጫ መዋቅሮች፤ ብሎም በ54 ሜትር ከፍታ ያለው የመስጊዱ ጉልላት ያስከተላቸው ተግዳሮቶች መኖራቸውን ፓክዴል ተናግረዋል።
መስጊዱ የተገነባበት ወቅት የኢራን ሶስተኛ ከተማ ለሆነችው ኢስፋሃን ወርቃማ ዘመኗ ነበር ተብሎ በሚታመንበት ወቅት ነበር።
አስደናቂ በሆኑት ደማቅ ሰማያዊ እና ቢጫ ጥለት ባላቸው የሴራሚክ ንጣፎች የተሰራው መስጊዱ ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር ለኢራናዊያን ብሎም ለአለማቀፍ ጎብኚዎች በከፍተኛ ቁጥር ከሚጎበኙ ቦታዎች መካከል ነው።
"ተቆጣጣሪዎች እና ጠጋኞች በተለይም በጉልላቱ የላይኛወው ክፍል ላይ ጉዳቶች መድረሳቸውን አስተውለዋል" ሲሉ የከተማዋ የቅርስ ጉዳዮች ሃላፊ አሊሬዛ ኢዛዲ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። አክለውም "የጉልላቶቹን ንጣፎችን በአዲስ እንተካለን፣ ምክንያቱም የመርገጫው ክብደት ጫፋቸውን ስለጎዳው" ሲሉ ተናግረዋል።