የህንድ ዶክተሮች ከአራስ ልጅ ሆድ ውስጥ ሁለት የጨነገፉ ጽንሶችን አስወገዱ

የህንድ ሐኪሞች፤ የ20 ቀናት እድሜ ካላት ጨቅላ ልጅ ሆድ ውስጥ ያደጉ ሁለት "ጥገኛ መንታ" ጽንሶችን በተሳካ ሁኔታ አስወገዱ።

በጽንስ ውስጥ ሌላ ጽንስ የሚፈጠርበት የህክምና ሁኔታ እጅጉን ያልተለመደ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ እስካሁን በዓለም ዙሪያ የተመዘገቡት ኬዞች ከ200 ያነሱ ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥም በጣት የሚቆጠሩት በህንድ ያጋጠሙ ናቸው።

በእርግና የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የሚፈጠረው ይህ አይነቱ ሁኔታ፤ በአግባቡ ያላደገ ጽንስ በመንትያው ጽንስ ሲዋጥ የሚከሰት ነው። የተዋጠው ፅንስ በሕይወት ባይኖርም ከመንትያው ንጥረ ነገሮችን በመውሰድ እድገቱን ይቀጥላል።

አሁን በህንድ ያጋጠመው ሦስት መንትዮችን እርግዛ በነበረች እናት ላይ ነው። ሁለቱ ፅንሶች በቀሪዋ ህጻን ልጅ ሆድ ውስጥ ገብተው ማደግ እንደጀመሩ ተገልጿል።

ህክምናውን የመሩት የሕፃናት የቀዶ ጥገና ሐኪሙ አናንድ ሲንሃ፤ "ቀዶ ጥገናው ፈታኝ ነበር፤ ነገር ግን ሕፃኗ ጤነኛ ነች፤ በጥሩ ሁኔታ ላይም ትገኛለች" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ህክምናው የተደረገላት ጨቅላ ህጻን ከሆስፒታል የወጣችው ከአንድ ወር በፊት እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተሩ፤ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ችግር አለመፈጠሩን ገልጸዋል።

ኢንፌክሽን ወይም ሌሎች ችግሮች የህጻኗን ህይወት አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ በማንሳትም ከቀዶ ጥገናው በኋላ ያለው የማገገሚያ ጊዜ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2024 በህንድ በምትገኘው ኮልካታ ከተማ ውስጥ ከተወለደ የሦስት ቀን ሕፃን ሆድ ውስጥ ሁለት በአግባቡ ያላደጉ ፅንሶችን ለማስወገድ ቀዶ ጥገና ከተደረገ ከአንድ ቀን በኋላ የጨቅላው ልጅ ህይወት አልፏል።

በሰሞነኛው ሁኔታ ወላጆች የ20 ቀን ልጃቸውን በጉሩግራም ከተማ ወደሚገኘው 'ፎርቲስ ሚሞሪያል ሪሰርች ኢንስቲትዩት' የተባለ የህክምና ተቋም ያስገቡት ሐምሌ ወር ነበር።

ዶክተር አናንድ፤ "ሆዷ ተነፍቶ፣ ህመም እየፈጠረ ነበር፤ ፅንሶቹ ሆዷን እየተጫኑት ስለነበር ምንም ነገር መመገብ አትችልም ነበር" ሲሉ ጨቅላዋ ወደ ህክምና የመጣችበትን ሁኔታ አስታውሰዋል።

በተደረገ የስካን ምርመራ ሆዷ ውስጥ ሁለት እጢ የሚመስሉ ቅርጾችን እንደታዩ እና ኋላም እነዚህ ቅርጾች የከሸፉ ፅንሶች መሆናቸው እንደታወቀም ተገልጿል።

ሕፃኗ ሰውነቷ ውስጥ ውሃ ያልነበረ በመሆኑ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ስለነበረባት እና በቅድሚያ እድትረጋጋ መደረግ ስለነበረበት ቀዶ ጥገናው ወዲያውኑ ሊከናወን እንዳልቻለ ዶክተር አናንድ አስረድተዋል። ከሁለት ቀናት በኋላ ሁኔታዋ ሲሻሻል 15 ገደማ ዶክተሮችን የያዘ የህክምና ቡድን ቀዶ ጥገናውን እንዳከናወነም ተነግሯል።

"ቀዶ ጥገናው ሁለት ሰዓት ገደማ ወስዷል" ያሉት ዶ/ር አናንድ፤ ሕፃኗ ደካማ እና ደቃቅ በመሆኗ ልዩ መሣሪያ መጠቀም አስፈልጎ እንደነበርም አክለዋል።

በተጨማሪም ፅንሶቹ እንደ ጉበት፣ ኩላሊት እና አንጀት ካሉ የሰውነት ክፍሎች ጋር ተያይዘው ስለነበር፤ የሰውነት አካላቱ ወይም የደም ቧንቧዎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንደነበረበት ተገልጿል።

"በቀዶ ጥገናው ወቅት የህጻኗ የሙቀት መጠን ክትትል ይደረግ ነበር" ያሉት ዶክተር አናንድ፤ "በጣም ብዙ የደም መፍሰስ አለመኖሩን ማረጋገጥ ነበረብን" ሲሉም የተደረጉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ጠቅሰዋል።

በፅንስ ውስጥ ፅንስ መፈጠሩ ብዙውን ጊዜ የሚታወቀው በእርግዝና ወቅት በሚደረግ ምርመራ ነው። በአንዳንድ ጊዜያት ግን በሽታው በጨቅላነት ጊዜ ሳይታወቅ ካለፈ በአዋቂዎች ውስጥ ጥገኛ መንትዮች እንደሚገኙ ሐኪሙ አስረድተዋል።

በወቅቱ ካልተወገዱ በአግባቡ ያላደጉት ጽንሶች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ መጠናቸውም እየጨመረ እንደሚሄድም ተናግረዋል።

እነዚህ ጽንሶች አብዛኛውን ጊዜ ወደ ካንሰር ባይቀየሩም ለግለሰቡ ላይ ሌሎች ችግሮችን ሊያስከትሉ እና በዚህም የተነሳ መኖራቸው ሊደረስበት እንደሚችል ገልጸዋል።

የካቲት በተመሳሳይ የህንድ ሐኪሞች ማሃራሽትራ በተባለ ግዛት ውስጥ ከተወለደ የሦስት ቀን ሕፃን ሆድ ውስጥ ሁለት ፅንሶችን አውጥተው ነበር።