የእርግዝና መከላከያ ክኒን በእርግጥ ሴቶችን የበለጠ እንዲጨነቁ ሊያደርግ ይችላል?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ሴቶች ስለ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች የጎንዮሽ ጉዳት በተለይም በስሜታቸው እና በአእምሮ ጤንነታቸው ላይ ሊያደርሱ ስለሚችሉት ጉዳት በጣም ያሳስባቸዋል።

ይህ ብቻም ሳይሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ የእርግዝና መከላከያ ላይ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች ከተለያዩ ወገኖች ይሰማሉ።

በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠራጩ እንዲህ ያሉ መረጃዎች ሚሊዮኖች ይቀባበሏቸዋል።

በእርግጥ ተገቢ የሆነ ስጋት ያላቸው ሴቶች የመኖራቸውን ያህል የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የእርግዝና መከላከያ ክኒኖች ያስከትላሉ ስለሚባሉት አእምሯዊ እና አካላዊ የጎንዮሽ ጉዳት የተሳሳቱ መረጃዎችን ሲያሠራጩ ይስተዋላል።

እነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ምንም እንኳን የሕክምና ዕውቀት የሌላቸው ቢሆኑም በድፍረት ሴቶች የእርግዝና መከላከያዎችን ሙሉ በሙሉ እንዲተዉ ያበረታታሉ።

የሚዋጡ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች የአንድ ሰው ሰብዕና እና ለሕይወት ያለው አመለካከት ሊለውጡ ይችላል ? እንደ ጭንቀት እና ድብርት ላሉ የአእምሮ ጤና ሁኔታዎች አስተዋጽዖ ያደርጋሉ ?

የእርግዝና መከላከያ ክኒን በ1960 በአሜሪካ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ላይ ሲውል፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ 1.2 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን አፍርቷል።

በወቅቱ እነዚህ ትንንሽ እንክብሎች ለሴቶች የፆታዊ ነፃነት እና የጥንካሬ ምልክት ተደርገው ተወሰዱ። ያልታቀደ እርግዝና ከሥራ ዕድገትም ሆነ ከትምህርት ያዘገየኛል ከሚል ፍርሃት ነፃ አውጥቷቸዋል።

ዛሬ የሚዋጥ የእርግዝና መከላከያ በዓለም ዙሪያ ላሉ 150 ሚሊዮን ሴቶች ወይም በግምት 16 በመቶ የሚሆኑ የእርግዝና መከላከያ ወሳጆች ምርጫ ነው።

ጥምር እንክብል (ኢስትሮጅን) እና ፕሮጄስትሮን (ሚኒ-ፒል የተሰኙ) ሁለት ዓይነት የእርግዝና መከላከያ ክኒኖች አሉ፤ ሁለቱም ከሰው ሰራሽ ሆርሞኖች የተሠሩ ናቸው።

ሁለቱም እርግዝናን ለመከላከል የሚሠሩት የማህጸን ጫፍ ፈሳሽን በማወፈር የወንድ የዘር ፍሬ እንቁላል ጋር በቀላሉ እንዳይደርስ በመገደብ ወይም ኦቫሪዎች እንቁላል እንዳይለቁ በማገድ ነው።

ይኹን እንጂ በሚዋጥ የእርግዝና መቆጣጠሪያ ውስጥ ያሉት ሆርሞኖች በሰውነት ላይ ብቻ ሳይሆን በሴቶች አእምሮ ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።

በስዊትዘርላንድ በሚገኘው የዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ባዝል የማህፀን እና ጽንስ ሐኪም እንዲሁም ሳይኮቴራፒስት የሆኑት ዶ/ር ዮሃንስ ቢትዘር "በአንጎል ላይ የሆርሞኖች ተጽዕኖ ውስብስብ ነው" ይላሉ።

"ለአንዳንድ ግለሰቦች ክኒኑ በአእምሮ ጤንነት ላይ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በሌሎች ደግሞ ብስጭት አልፎ ተርፎም ጭንቀት ሊፈጥር ይችላል።"

በሚዋጡ የእርግዝና መከላከያ ክኒኖች የ65 ዓመት ታሪክ ውስጥ የሕክምና ማስጠንቀቂያዎች እጅጉን ጥቂት ናቸው።

ለ40 ዓመታት ያህል በማህፀን እና ጽንስ ሕክምና የሠሩት ዶ/ር ቢትዘር ". . . በማህፀን እና ጽንስ ሕክምና ሥልጠና ውስጥ የአእምሮ ጤና ርዕስ ጉዳይ አይደለም፤ ይህ የተተወው ለሥነ-አእምሮ ሐኪሞች ነው" ይላሉ።

"ከዚህ በፊት ስለ ክኒኑ ስንወያይ ስለ ካንሰር፣ ደም መርጋት፣ መደበኛ ያልሆነ ደም መፍሰስ፣ የሰውነት ክብደት መጨመር እና የመሳሰሉትን እናወራ ነበር። የአእምሮ ጤና ጉዳይ አይካተትም ነበር" ይላሉ።

በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎችም ቢሆኑ ሊከሰቱ ስለሚችሉ የአእምሮ ጤና የጎንዮሽ ጉዳቶች ብዙ ምርምር ሳያደርጉ ቆይተዋል።

እኤአ ከ2016 ጀምሮ የዴንማርክ ተመራማሪዎች በጉዳዩ ላይ ጥናት ወረቀታቸውን ማሳተማቸውን ተከትሎ የአተያይ ለውጥ ተደርጓል ይላሉ ዶ/ር ቢትዘር።

የዴንማርክ ተመራማሪዎች በ14 ዓመታት ውስጥ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 34 የሆኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሴቶችን የአእምሮ ጤንነት ለመከታተል የአገሪቱን ብሔራዊ የጤና የመረጃ ቋት በርብረዋል።

አጥኚዎቹ ጥምር ክኒን መውሰድ የጀመሩ ሴቶች የሚዋጥ የእርግዝና መከላከያ ካልወሰዱት ጋር ሲነፃፀሩ ከስድስት ወራት በኋላ ጭንቀት የሚያስወግድ መድኃኒት የመውሰድ ዕድላቸው 70 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል።

ሚኒ ፒል የሚባለውን ክኒኑ ለሚጀምሩ ደግሞ ስጋቱ 80 በመቶ ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2023 ሌላ የተመራማሪዎች ቡድን በዩናይትድ ኪንግደም የሩብ ሚሊዮን ሴቶችን የጤና መዛግብት አገላብጠው ሲተነትኑ ተመሳሳይ ውጤት ላይ ደርሰዋል።

እነዚህ ሴቶች የእርግዝና መከላከያ ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በኋላ ፈጽሞ ከማይጠቀሙት ጋር ሲነጻጸሩ 71% ለጭንቀት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን አረጋግጠናል ነበር ያሉት በወቅቱ።

የዴንማርክ ጥናትን የመሩት በኮፐንሃገን ዩኒቨርሲቲ የማህፀን እና የጽንስ ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ኦይቨን ሊዲጋርድ "እነዚህን ምርቶች መጠቀም በመጀመር እና የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶችን በማዳበር መካከል አሳማኝ ጊዜያዊ ግንኙነት አለ" ይላሉ።

ይኹን እንጂ እነዚህ ሁለቱም "የቡድን ጥናቶች" ናቸው።

ይህም የሴቶችን ትላልቅ ቡድኖች መረጃ በመተንተን እና የሚዋጡ የእርግዝና መከላከያዎችን የሚወስዱትን የአእምሮ ጤና ውጤቶችን ካልወሰዱት ጋር በማነፃፀር የተሠራ ነው።

ይህ ማለት በእነዚህ ሁለት ነገሮች መካከል ግንኙነት መኖሩን መለየት ችለዋል፤ ነገር ግን መንስኤ እና ውጤት መኖሩን አይፈቱም።

ለምሳሌ በናሙናነት በተወሰዱት የሴቶች ቡድኖች መካከል አንዳንድ ቀደም ብለው የነበሩ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

በአእምሮ ጤና ሁኔታ እና በሚዋጥ የእርግዝና መከላከያ መካከል ያለውን ቁርኝት የሚቃረኑ ሌሎች ጥናቶችም አሉ።

በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች 26 ቀደም ያሉ ጥናቶችን ከገመገሙ በኋላ፣ በፕሮጄስትሮን የእርግዝና መከላከያ እና የመንፈስ ጭንቀት መካከል "አነስተኛ" ግንኙነት ብቻ አግኝተዋል።

በስዊድን ከ200 እስከ 340 በሚደርሱ ሴቶች ላይ በተደረገ ሌላ ምርምር ደግሞ፣ ተመራማሪዎች ድብልቅ ክኒን ወደ ድብርት ወይም ባስ ወዳለ ስሜት አይመራም በማለት ደምድመዋል።

በስዊድን ስቶክሆልም በሚገኝ ሆስፒታል የማህፀን እና ጽንስ ሐኪም የሆኑት ሄለና ኮፕ ካልነር የሚዋጥ የእርግዝና መከላከያ አእምሯዊ የጎንዮሽ ጉዳቶች ዙሪያ ያሉ የጥናት ውጤቶች ላይ የሚታየው ሰፊ ልዩነት ምክንያት የተጠኚዎቹ ባህሪ ነው ይላሉ።

ይህንን ሲያብራሩ የአዕምሮ ጤና ሁኔታ ብዙውን ጊዜ የሚለካው እንደ ግለሰቡ ሁኔታ መሆኑን በመጥቀስ ነው።

በተጨማሪም የተለያዩ ዓይነት ብራንዶች (ከ30 በላይ) መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ተመራማሪዎቹ የሚጠቀሙት የተለያየ ዘዴም ለውጤቱ መለያየት ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።

ዶ/ር ቢትዘር በበኩላቸው ተመራማሪዎች በጥናታቸው መጨረሻ ላይ የሚፈልጉት ነገር በግኝታቸው ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል።

ስውዲናዊቷ ዶ/ር ሶፊያ ዜተርማርክ በበኩላቸው በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ እንደ ሥነ ባህርይ (ጄኔቲክስ) እና የግለሰቡ መኖሪያ ከባቢ ምክንያቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ከእንደዚህ ዓይነት ጥናቶች ጋር ያለውን የመንስኤ እና የውጤት ግንኙነቶችን ማረጋገጥ ከባድ ነው ብለዋል።

ዶ/ር ሶፊያ በብሔራዊ የስዊድን ወመዘክር ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶችን የጤና መዝገብ ስትመረምር፣ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው እና ከስደተኛ ቤተሰብ የመጡ ሴቶች የሆርሞን የእርግዝና መከላከያ በሚወስዱበት ወቅት የበለጠ የስሜት ለውጥ እንደሚያጋጥማቸው አስተውላለች።

ሊዴጋርድ በበኩሉ ጥናቱን በሰፊው ዓውድ መረዳት እንደሚያስፈልግ ያብራራል።

"የሆርሞን የእርግዝና መከላከያ መጠቀም የጀመሩ አንዳንድ ሴቶች በአእምሮ ጤንነታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያጋጥማቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

"ነገር ግን ብዙ የአእምሮ ችግሮች የሚያጋጥሟቸው ከ 7 እስከ 8 በመቶው ብቻ መሆናቸውን መገንዘብም በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሴቶች በዚህ የተነሳ መድኃኒቱን መውሰድ ለማቆም ይገደዳሉ. . . እነዚህን ምርቶች የሚጠቀሙ አብዛኛዎቹ ሴቶች በአእምሯቸው ውስጥ ምንም ዓይነት መረጋጋት አይሰማቸውም።"

በእርግጥ ለአንዳንድ ሴቶች የሚዋጥ የእርግዝና መከላከያ ከማንኛውም የጎንዮሽ ጉዳቱ ጥቅሙ የበለጠ ሊሆን ይችላል።

ይህ የእርግዝና መከላከያ በጣም ውጤታማ ከመሆኑ በተጨማሪ ጥምር እና ሚኒ-ክኒን ሌሎች አወንታዊ የአካል ውጤቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ኮፕ ካልነር "የማህፀን ህመም (endometriosis)፣ ከባድ ደም መፍሰስ ወይም ከወር አበባ በፊት የሚመጣ ህመም ላለባት ሴት ክኒኑ በትክክል ህመሟን ለማሻል ይረዳል" ሲል ያስረዳል።

እርግዝና ራሱ፣ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ከፍተኛ የጤና ችግሮችን ሊያካትት ይችላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በርካታ ጥናቶች ባልታቀደ እርግዝና እና በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት መካከል ግንኙነት መኖሩን ደርሰንበታል ብለዋል።

የሕክምና ባለሙያዎች በተለያዩ አገራት ከተደረጉ ጥናቶች በመነሳት ከዚህ ቀደም የመንፈስ ጭንቀት ላጋጠማቸው ሴቶች የሚዋጥ የእርግዝና መከላከያን ለማዘዝ ይጠነቀቃሉ።

ኮፕ ካልነር "ከዚህ በፊት የመንፈስ ጭንቀት አጋጥሞሽ ከነበረ፣ ወይንም ተደጋጋሚ የመንፈስ ጭንቀት ካለብሽ ወይም ማንኛውም የሥነ አእምሮ ችግር ካለብሽ፣ ክኒኑን ስትወስጂ ድባቴ ሊያጋጥምሽ ይችላል" ሲል ያስጠነቅቃል።

እንደ ኮፕ ካልነር ያሉ ባለሙያዎች ራስን ማወቅ ቁልፍ መሆኑን ያሰምሩበታል።

ክኒኑን ለመጀመሪያ ጊዜ መውሰድ ስትጀምሪ ለጥቂት ወራት ስሜትሽን መከታተል አለብሽ። ወይም ከአንድ ብራንድ ወደ ሌላ መቀየር ይኖርብሻል።

የእርግዝና መከላከያዎች በስሜትሽ ላይ የሚያሳድሩትን ለውጥ ከተረዳሽ በአቅራቢያሽ ያለ የጤና ባለሙያን ከማነጋገር ወደ ኋላ አትበይ።

ዶ/ር ቢትዘር የተለያዩ የፕሮጄስትሮን ዓይነቶች እና ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በተለያየ መጠን እና ዝግጅት፣ ከኦስትሮጅን ጋር ተጣምረው መኖራቸውን በማንሳት ከእነዚህ መካከል ለአንድ ሰው የሚስማማውን ትክክለኛ እንክብል ማግኘት "ጥቂት ጥበብ ይጠይቃል" ይላል።

"በጣም ግለሰባዊ ሕክምና ነው" ሲልም ያክላል።

ከሚዋጥ የእርግዝና መከላከያ ውጪ፣ ሆርሞንን የማያካትቱ ወይንም አነስ ያለ መጠን ያላቸው ብዙ ሌሎች የእርግዝና መቆጣጠሪያ ዓይነቶች አሉ።

የወንድ ወይም ሴት ኮንዶም (ይህም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ለመከላከል ይረዳል)፣ በማህፀን ውስጥ የሚቀመጥ ሉፕ፣ በክንድ ላይ የሚቀበር እና ከ3 እስከ 5 ዓመት የሚያገለግል ኢምፕላንት፣ እንዲሁም ለሦስት ወይንም ለስድስት ወር በመርፌ የሚሰጥ መከላከያ እና የሴቶችን የዘር ፍሬ ወደ ማህፀን የምትወስደውን ቱቦ መቋጠር፣ ወንዶች ላይ ደግሞ የወንድ የዘር ፍሬ እንዳይተላለፍ መንገዱን መዝጋት ወይም በመቁረጥ (vasectomy) አማራጭ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች ናቸው።