ልጆቻቸውን ካጡ በኋላ የፌስቡክ ኩባንያ ሜታን ተጠያቂ ለማድረግ የተነሱት እናቶች

ልጄ በስድስት ሳምንታት ውስጥ ምን ይመስላል? የመውለጃ ቀኔ መቼ ነው? የመጀመሪያ የሐኪም ቀጠሮዬን መቼ መያዝ አለብኝ?

እነዚህ ሴቶች እርጉዝ መሆናቸውን ሲያውቁ በበይነ መረብ ላይ የሚጠይቋቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ናቸው።

ሳሚ ክላክሰንም አንደኛዋ ናት። ምላሽ ለማግኘት ያደረገቸው ሙከራ ግን ብዙም ሳይቆይ እርጉዝ መሆኗን ከግምት በማስገባት ከእርግዝና ጋር የተያያዙ ማስታወቂያዎች ያነጣጥሩባት ጀመር።

ፅንሱ በመጨናገፉ ምክንያት ልጇን ስታጣም ግን ማስታወቂያዎቹ አልቆሙም።

ይህ የሆነው እአአ በ2021 ነበር። ሳሚ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ አራት ጊዜ እርግዝናዋ ተጨናግፏል።

"ማርገዜን ሳውቅ የእናትነት ስሜት ይሰማኛል" ብላለች ሳሚ። "ስለወደፊቱ ማቀድ ስጀምር ግን ሁሉም ነገር ስለሚስተጓጎል በጣም አስከፊ ይሆናል።"

እፍረቱ እና የመሸማቀቅ ስሜቱ ሳሚ የብቸኝነት ስሜት እንዲሰማት አድርጓታል።

ለድጋፍ በሚል ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ስትዞር ከሕፃናት ጋር በተያያዙ ማስታወቂያዎች ተሞልቶ መመልከቷን ታስታውሳለች። ይህም ከባድ ሆኖባት ነበር።

የኖቲንግሃምሻየር ብሊድወርዝ ነዋሪዋ ሳሚ ለአዕምሮ ጤንነቷ በሚል ከማኅበራዊ ሚዲያ ራሷን እንዳገለለች ትናገራለች።

እንደ ሳሚ ሁሉ ታንያ ኦካሮልም በፈረንጆቹ 2017 እርጉዝ መሆኗን ባወቀችበት ወቅት በርካታ ማስታወቂያዎችን ከፌስቡክ አግኝታለች።

"ይህ የሚያስጨንቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ይህ የሆነው ደግሞ የራሴ ለምላቸው ሰዎች ከመናገሬ በፊት ነበር" ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።

በመጋቢት ወር ታንያ ክስ ከመሰረተች በኋላ ፌስቡክ የግል መረጃን በመጠቀም በግለሰብ ተጠቃሚ ላይ ማስታወቂያዎችን ማነጣጠሩን ለማቆም ተስማምቷል።

የታንያ የክስ ጭብጥ ፌስቡክ ዒላማ ያደረገው በዩናይትድ ኪንግደም ቀጥተኛ ግብይት ትርጉም የተሸፈነውን ሲሆን ይህም ግለሰቦች የመቃወም መብት ይሰጣቸዋል ስትል ተከራክራለች።

'አሳፋሪ ማስታወቂያዎች'

ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታ፤ ማስታወቂያዎቹ ከግለሰቦች ይልቅ በትንሹ 100 ሰዎች ላይ በማነጣጠሩ ቀጥተኛ ማስታወቂያ ተደርጎ አይቆጠርም ብሏል።

የኢንፎርሜሽን ኮሚሽን ቢሮ (አይሲኦ) ግን በዚህ አይስማማም።

ታንያ ሜታ የግል ዳታዋን ለቀጥታ ማስታወቂያ ዓላማ መጠቀም ለማቆም ተስማምቶ እንደነበር ተናግራለች።

"ይህም ማለት ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ በፌስቡክ ላይ ያለውን አሣዛኝ፣ ወራሪ እና ዒላማ ያደረጉ ማስታወቂያዎችን ማጥፋት እችላለሁ ማለት ነው" ስትል ተናግራለች።

እሷ እና ጠበቃዎቿ እንደሚያውቁት ከሆነ በዩናይትድ ኪንግደም ካሉት ከ50 ሚሊዮን በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ግላዊ የሆኑ ማስታወቂያዎችን የማታገኘው ብቸኛዋ ሰው ነች።

ታንያ አክላም ሜታ መረጃቸውን ለቀጥታ ማስታወቂያ መጠቀሙን እንዲያቆሙ ተቃውሞ ያነሱ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች መኖራቸውን ተናግራለች። ይህም ተጨማሪ ክስ ሊመሰርትበት ይችላል።

ልጆቻቸውን አጥተው ከእርግዝና ጋር የተያያዙ ማስታወቂያዎች "በብዛት" ለሚደርሷቸው ሴቶች ግን ምንም ለውጥ አላመጣም።

የሱፎልክ ነዋሪዋ ሪሃነን ሎውሰን ለቢቢሲ እንደተናገረችው ማርገዟን ማወቋ ለእርሷ እና ለአጋሯ ማይክ "ተስፋ የሰጣቸው" ነበር።

ስም አስከማውጣትም ደርሰዋል።

"ፋንተስ ስንል ስም አወጣን" ስትል ሪሃነን ገልጻለች።

ሆኖም ሪሃነን እርግዝናዋ ተጨናገፈ።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በድጋሚ እርጉዝ መሆኗን አወቀች።

ልጁ ወንድ መሆኑን ከ20 ሳምንት በኋላ በአልትራሳውንድ ስካን አረጋገጠች። ሃድሰን ሲሉ ስም አወጡለት። ልጁ ሃይፖፕላስቲክ የተሰኘ የልብ በሽታ ነበረበት።

ሃድሰን በሕይወት አልተወለደም።

ክፉኛ የተጎዱት ጥንዶች ማኅበራዊ ሚዲያን ድጋፍ ለማግኘት ይጠቀሙበት ነበር። በበይነ መረብ የቃል ጨዋታዎችን አብረው ይጫወቱ ነበር።

ልጃቸውን ካጡ በኋላም ጥንዶቹ ከሕጻናት ጋር የተያያዙ ማስታወቂያዎች ያጋጥሟቸው ነበር።

"የእርግዝና መተግበሪያዎች ማሳወቂያዎችን ይልካሉ። የሕፃናት መደብሮች በማንፈልጋቸው ዕቃዎች ላይ ቅናሽ እንዳላቸው ይገልጻሉ" ብላለች ሪሃነን።

"ቴክኖሎጅ ማጣትን አይረዳም። ባልጠበቅነው ጊዜም የሌለንን ነገር ያስታውሰናል።"

'ፍቃድ ወይስ ክፍያ'

መስከረም መጨረሻ ላይ ሜታ በዩኬ ውስጥ ማስታወቂያዎችን ማየት ለማይፈልጉ ተጠቃሚዎች የደንበኝነት ምዝገባ አገልግሎት እንደሚጀምር አስታውቋል።

ይህም ማለት ማስታወቂያዎችን ላለማየት በወር 2.99 ፓውንድ ይከፈላል።

"ፈቃድ ወይም ክፍያ" በመባል የሚታወቀው የማስታወቂያ ሞዴል፤ የዲጂታል መድረክ ባለቤቶች ማስታወቂያ ከማይፈልጉ ተጠቃሚዎች ገቢ የሚያገኙበት አካሄድ ነው።

ሪሃነን ግን ይህም ችግሩን አይቀርፈውም ትላለች።

"እነሱ (ሜታ) ለተጠቃሚዎቹ የሚጨነቅ ከሆነ የሚያናድድ ይዘት እንዳያዩ ክፍያ መጠየቅ ምክንያታዊነት የጎደለው ይመስላል" ትላለች።

ከሦስት ዙር ያልተሳካ በሕክምና የማርገዝ (አይቪኤፍ) ሙከራ በኋላ ሄይሊ ዶው እና አጋሯ አንቶኒ መንታ ልጆች ማርገዛቸውን አወቁ።

በፍጥነትም ጠቃሚ ምክሮችን እና ሃሳቦችን ለማግኘት በበይነ መረብ የተቋቋመ የመንትያ ቡድኖችን እንዲቀላቀሉ ግብዣ ቀርቦላቸዋል።

ቀደም ሲል የስድስት ዓመት ሴት ልጅ ነበራቸው። ተጨማሪ ሁለት ልጆች ማግኘታቸው በጣም አስደስቷቸው ነበር።

ቀደም ሲል በተደረገ ስካን ግን ከሁለቱ መንትዮች መካከል አንዱ ከሳምንት በፊት መሞቱን ማረጋገጣቸው ደስታውን ወደ ሃዘን ቀየረው።

በቀጣዩ ቀጠሮ ደግሞ ሌኛው ልጅም የልብ ምት አልነበረውም።

"ተሰበርኩ" ብላለች።

ሄይሊ በበይነመረብ ድጋፍ ለማግኘት ሞክራለች። የእናቶች ልብስ፣ የእርግዝና ትራሶች እና የእርግዝና መከታተያ መተግበሪያዎች ማስታወቂያዎች ያጥለቀልቋት ጀመር።

ሄይሊ ከማኅበራዊ ሚዲያ መውጣቷ "አማራጭ አልነበረውም።"ተመሳሳይ ገጠመኝ ያላቸውንም ሴቶች አገኘች።

ፌስቡክ ላይ ተጠቃሚዎች ማየት የማይፈልጓቸውን እንደ ትግል እና ቸኮሌት ያሉ ማስታወቂያዎች ማስቀረት የሚችሉበት ምርጫ አላቸው።

ከእነዚህ አማራጮች መካከል እርግዝና አለመኖሩን ስታውቅ በጣም እንደ ደነገጠች ሄይሊ ትናገራለች።

አንዳንድ ማስታወቂያዎችን እንደማትፈልግ ብታሳውቀም ግን ከሦስት ሳምንታት በኋላ የእርግዝና ማስተዋወቂያዎቹን ማግኘት እንደጀመረች ተናግራለች።

እንደ ሪሃነን ሁሉ ሄይሊም የሚከፈልበት የደንበኝነት ምዝገባን አትደግፍም።

"የማይሠሩ የሚመስሉ ምርጫዎችን የመለወጥ አማራጮች እያሉ ለምን መክፈል አስፈለገኝ?" ብላለች።

ሳሚ፣ ሪሃነን እና ሄይሌ ማስታወቂያዎችን የማግኘት ልምዳቸው አስደንጋጭ አለመሆኑን የቀድሞው የሜታ ሠራተኛ አርተሮ ቤጃር ይገልጻል።

ከከፍተኛ አመራሮች አንዱ የነበረው አርተር "የአይፈለጌ መልዕክት (ስፓም) ምልክት ከምንም ጋር አይገናኘም" ብሏል።

"በአንዳንድ አጋጣሚዎች የድጋፍ ሪፖርቶች በጣም ብዙ በመሆናቸው እየተዘለሉ መሆኑን ደርሰንበታል።"

ከ2009 እስከ 2015 ለሜታ ሠርቷል። በ2023 ደግሞ ሜታ የተጠቃሚዎችን ደህንነት እየጠበቀ አይደለም ብሎ ስላመነበት ጉዳይ ለአሜሪካ ኮንግረስ መረጃ ሰጥቷል።

አርተሮ አክሎም "እንጨነቃለን ቢሉም ግን ብዙ ተጠቃሚዎችን ስለማግኘት ብቻ ነው የሚያሳስባቸው። ይህም ብዙ ገንዘብ ያስገኝላቸዋል። ይህ ሰበብ የሌለው ይመስለኛል። ሰብዓዊነት የጎደለው ነው።"

የሜታ ቃል አቀባይ በሰጡት ምላሽ "እነዚህን ስጋቶች በቁም ነገር እንይዛቸዋለን። ማስታወቂያዎች የሚደርሱበትን መንገድ ማሻሻላችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

"ስርዓቶቻችን በጣም ጠቃሚ ይዘትን ለመጋራት የተነደፉ ናቸው። ነገር ግን ፍፁም አይደሉም። አንዳንድ ማስታወቂያዎች የማይገቡ ወይም ያለቦታው ሊታዩ ይችላሉ። አሰራራችን ማጥራት ስንቀጥል ሰዎች ከተወሰኑ ምድቦች እንዲወጡ እናበረታታለን።"

"ያጠሁትን ሁሉ ያስታውሰኛል"

እነዚህ ማስታወቂያዎች ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆኑ አውቃለሁ።"

ልጄን ሊሊያናን በ2020 ወለድኩ።

ለ 40 ሳምንታት ካረገዝኳት በኋላ ከመወለጃዋ ሁለት ቀናት አስቀደም ብሎ ልቧ መምታቱን አቆመ።

ፊቷን፣ ክብደቷን እና ቆዳዋ ምን እንደሚመስል እንዲሰማኝ በማድረግ ጥቂት ውድ ሰዓታትን አሳለፍኩ።

"አጣሁዋት" ከሚለው ቃል ጋር ታገልኩኝ። ምክንያቱም እንደጠፉ ቁልፎች አላጣኋትም።

ሊሊያና ከሞተች ወዲህ ሴት እና ወንድ በፅንስ መጨንገፍ አጥቻለሁ። ሁሌም በእጄ የምይዛቸው የሁለት ሕፃናት እናት ነኝ እላለሁ። ሦስቱን ደግሞ በልቤ ውስጥ እይዛለሁ።

ለድጋፍ ለማግኘት ማህበራዊ ሚድያ ስቃኝ የሚስቁ ህጻናት፤ የህጸናት ዕቃዎች እና ደስተኛ ቤተሰቦች ሳይ ያጣሁትን ሁሉ ፊቴ ላይ ድቅን ያደርጋሉ።