ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ ድርቅ ባስከተለው ረሃብ 22 ሰዎች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸው ተገለጸ
በትግራይ ክልል ቆላ ተምቤን ወረዳ ያቄር ቀበሌ ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ከግንቦት ወር በኋላ 22 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።
በቀጣይ ሳምንታት እርዳታ የማይደርስ ከሆነ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሊያልቁ እንደሚችሉ የቆላ ተምቤን ወረዳ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጎይቶም ገብረ ሐዋርያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሰዎች በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸውን ላላፊው ጨምረው አስታውቀዋል።
108 ሺህ አካባቢ ነዋሪዎች ካሏት የቆላ ተምቤን ወረዳ ድርቅ ባስከተለው ረሃብ በከፋ ሁኔታ የተጠቃችው 4112 ነዋሪዎች ያሏት ያቄር የተሰኘችው ቀበሌ ናት።
ወረዳው በፊትም ቢሆን ድርቅ የሚያጠቃው አካባቢ ቢሆን በዘንድሮው ክረምት በተለየ መልኩ ዝናብ ባለመዝነቡ የተዘሩ ሰብሎች ለመብቀል ባለመቻላቸው የድርቁ መንስዔ እንደሆነ አቶ ጎይቶም ያስረዳሉ።
በአጎራባች ቀበሌዎችም እንዲሁ በድርቅ ስጋት ላይ ሲሆኑ፣ በክልሉ 170 ቀበሌዎች በድርቅ መጠቃታቸው ተነግሯል።
በቀበሌዋ ሦስት ጊዜ ሰብል ቢዘራም፣ 700 ሄክታር የሚሸፍን መሬት ሳይበቅል እንደቀረ ነው አቶ ጎይቶም የገለጹት።
በዚህም የተነሳ 22 ሰዎች በረሃብ ሲሞቱ ከ13 ሺህ በላይ ፍየሎች፣ ከ4500 በላይ በጎች፣ 900 አህዮች እና ከ185 በላይ ከብቶች ሲሞቱ እንዲሁም ከሁለት መቶ በላይ የንብ ቀፎዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።
ሞቱ እየቀጠለ እንደሆነ አጽንኦት የሰጡት አቶ ጎይቶም ፤ በተለይም ሕጻናት እና በዕድሜ የገፉ አዛውንት ረሃብን መቋቋም ስለማይችሉ "የሞት አፋፍ ላይ ነው ያሉት" ብለዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች መተዳደሪያቸው በግብርና እንዲሁም ከእንስሳት እርባታ ጋር ተያይዞ በዚህ የዝናብ እጥረት ከፍተኛ ቀውስ ማጋጠሙ ተገልጿል።
በተለይም ይህችን ቀበሌ ለየት የሚያደርጋት ምንም መንገድ የሌላት ከዋናው መንገድ ከስድስት ሰዓት በላይ በእግር ተጉዞ የሚደረስባት በመሆኑም የመጠጥ ውሃም ከወንዝ በመሆኑ ችግሩ መክፋቱን አቶ ጎይቶም ያስረዳሉ።
"በቅርበት ሕክምና ማግኘት አይችሉም። የተለያየ እርዳታ ለማግኘትም ሕዝቡ ፈተና ሆኖበታል። ይሄ ሁሉ ችግር ተደማምሮ ለሕዝቡ ካልደረስንለት ያልቃል" ሲሉ ገልጸዋል።
በቀበሌው ዙሪያ የሚገኙት ተከዜ እና ገረብ ግባ ወንዞች በዝናብ እጥረት ምክንያት በድርቅ ለተጠቃው ሕዝብም ሆነ እንስሶች የውሃ ምንጭ መሆን አልቻሉም።
"ወደ ታች ብንመለከት ምድር ነው፤ ቀና ብለን ብመለከት ሰማይ ነው። አህያዎቻችን አልቀዋል፤ ወንድ ልጆቻችንም እንዳያግዙን ሁሉም ወጥተው ሄደዋል" ሲሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለክልሉ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ከክልሉ የግብርና እና ገጠር ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በድርቁ ምክንያት 27 ሺህ ፍየሎች፣ በጎች፣ አህዮች እና ከብቶች ሞተዋል።
በረሃብ ጨቅላ አካላቶቻቸው ተመናምኖ እያለቀሱ ያሉ ሕጻናት፣ በረሃብ ጠኔ ተመትተው መንቀሳቀስ ያቃታቸው አዛውንት፣ የደከሙ ወጣቶች፣ እዚህም እዚያ የተረፈረፉ እንስሳት እና በድርቅ የተሰነጣጠቀ መሬት ምሥሎች እና ቪዲዮዎች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተጋሩ ይገኛሉ።
"ከሁለት ሦስት ቀናት በኋላ ሞት የሚጠብቃቸው ሁኔታ ላይ ነው ያሉት። ይሄንን እንደ ሰው ካልደረስንለት በአንድ ጊዜ ሊያልቁ ይችላሉ" ሲሉ አቶ ጎይቶም ያለው የከፋ ችግር አሳሳቢ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ወረዳዋ ለትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲሁም ክልሉ ለፌደራል መንግሥት ያለውን የረሃብ ቀውስ ሪፖርት ማድረጋቸውን አቶ ጎይቶም ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለአጋዥ ድርጅቶች ቢያሳውቁም እስካሁን ወደ ወረዳዋ የገባ እርዳታ የለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምናልባት ነገ እርዳታ ሊገባ እንደሚችል "ይሄንን በተስፋ" እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
እስካሁን በ'ሲድ ኢንተርፕራይዝ' 400 ኩንታል ጤፍ መላኩን ጠቅሰው ሆኖም እስካሁን ለሕዝቡ ጠብ ያለ እርዳታ እንደሌለ ገልጸዋል።
እስካሁን በወረዳዋ በጥቂት ወራት የሞቱ ሰዎች 22 መድረሳቸውን ተናግረው፤ ቀጣዮቹ ወራት የበለጠ ፈታኝ እንደሚሆኑ እና "እርዳታ ከሌለ ሕዝቡ ያልቃል" ሲሉ አሳስበዋል።
"በወረዳው ከዚህ ቀደምም ቢሆን በነሐሴ እና በመስከረም ወራት ችግር ይገጥማል፤ያለው ሕዝብ ራሱ የሚቸገርባቸው ወቅቶች ናቸው። በአሁኑ ወቅት ካለው ድርቅ ጋር ተያይዞ የሚበላውም ሆነ የሚጠጣው ይሟጠጣል። እናም የሚመለከተው አካል ሕዝቡ ካልተረዳ ከባድ መሆኑን ተገንዝቦ እንዲደርስለት" ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ድርቁ በሌሎች አጎራባች ስፍራዎች ተስፋፍቷል።
ከቆላ ተምቤን ወረዳ በተጨማሪ የላዕላይ ጸለምቲ አካባቢዎችም በከፍተኛ ድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በወረዳዋ ከሚገኙት መካከል በስድስቱ ቀበሌዎች በድርቅ መጠቃታቸውን የአካባቢው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የወረዳዋ የኢኮኖሚ ዘርፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምሸት ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በአጠቃላይ በወረዳዋ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ የዝናብ እጥረት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በከፋ ሁኔታ ሦስቱ ቀበሌዎች በድርቅ መጠቃታቸውን" አስረድተዋል።
በወረዳው ያሉ ቀበሌዎች ከግንቦት ጀምሮ ምንም ዓይነት ዝናብ ባለማግኘታቸው በተከሰተው ድርቅ ነዋሪው የሚመገበው እንዳጣ እና እንስሶችም እንዲሁ ለእጥረት ተጋልጠዋል።
ወረዳዋ በድህነት እና በምርታማነት ዕጦት ለዓመታት በእርዳታ ጥገኛ ከነበሩ አካባቢዎች ቢሆኑም የትግራይን ጦርነት ተከትሎ እርዳታ ቆሞ ነበር።
በፕሪቶሪያ ግጭትን የማስቆም ዘላቂ ስምምነት ጦርነቱ ቢቋጭም በጦርነቱ የተጎዱ በርካታ አካባቢዎች ተገቢውን እርዳታ እንዲሁም መሠረተ ልማቶች አልተሟሉላቸውም።
እስካሁን በወረዳዋ የሰው ሞት ባይከሰትም ድርቁ ባስከተለው የእንስሳት ሕመም እየተጠቁ መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ አለም እሸት 8 ሺህ 351 በግና ፍየል እንዲሁም 807 ከብቶች በሁለት ወራት ውስጥ መሞታቸውን አስረድተዋል።
የክልሉ የአደጋ እና ስጋት አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት 170 ቀበሌዎች በድርቅ መጠቃታቸውን አረጋግጧል።
ኮሚሽኑ ያቄርን ጨምሮ በድርቁ በከፋ በተጎዱ አካባቢዎች ለሁለት ወራት የሚሆን 1200 ኩንታል እህል እንደተላከ ኮሚሽነሩ ዶክተር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ከክልሉ የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ።