ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስታርመር ዩኬ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና መስጠቷን ለማወጅ ተዘጋጅተዋል
ሰር ኪር ስታርመር እሁድ ከሰዓት ዩኬ ለፍልስጤም አገርነትን እውቅና መስጠቷን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐምሌ ወር እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነትን ማድረግ፣ የሁለት አገር መፍትሄ የሚያመጣ ዘላቂ ሰላም ማስፈን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ አቅርቦቱን እንደገና እንዲጀምር መፍቀድን ጨምሮ፣ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለባት፤ አለበለዚያ ዩኬ እርምጃውን በመስከረሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ትወስዳለች ብለው ነበር።
በብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ነው የተባለለት ይህ ውሳኔ ከዚህ ቀደም የነበሩ ተከታታይ መንግሥታት እውቅና የሰላም ሂደቱ አካል እና ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያመጣ በሚቻልበት ወቅት ላይ መሆን አለበት ሲሉ ቆይተዋል።
የዩኬ ውሳኔ ከእስራኤል መንግሥት፣ከታጋቾች ቤተሰቦች እና ከተወሰኑ ወግ አጥባቂዎች ጠንከር ያለ ትችትን አስተናግዷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ "ሽብርተኝነትን የሚሸልም" ነው ብለው ነበር።
ይሁን አንጂ የዩኬ ሚኒስትሮች ዘላቂ የሰላም ስምምነት እንዲቀጥል ለማድረግ የሞራል ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
የመንግሥት ምንጮች ባለፉት ሳምንታት እስራኤል በጋዛ የምትካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ እየተባባሰ መምጣቱን ገልፀዋል።
ከጋዛ የሚወጡ ምስሎች ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር "ልንታገሰው የማንችል" ያሉትን ረሃብን እና ውድመትን የሚያሳዩ ናቸው።
እስራኤል በጋዛ ከተማ እያካሄደች ያለችውን የምድር ዘመቻ እና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩትን በግዳጅ ማፈናቀል የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት "አሰቃቂ እና አውዳሚ" ሲሉ ገልፀውታል።
የተባበሩት መንግሥታት ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች ያለ ሲሆን እስራኤል በበኩሏ "የተዛባ እና ሐሰተኛ" ስትል ውድቅ አድርገዋለች።
ሚኒስትሮች እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ የምታደርገውን መስፋፋት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገ ወጥ ቢሆንም እንደቀጠለችበት ገልፀው ለፍስልጤም አገርነትን እውቅና ለመስጠት ቁልፍ ምክንያት ነው ብለዋል።
ዩኬ ፍልስጤምን አገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ይፋ ባደረገችበት ሐምሌ ወር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት እና አሁን የፍትህ ሚኒስትር የሆኑት ዳቪድ ላሚ ተቺዎች የፍልስጤም አገርነት ላይ ውሃ ይቸልስበታል ያሉትን አጨቃጫቂውን ኢ1 (E1) የሰፈራ ፕሮጀክት አንስተዋል።
አክለውም "የፍልስጤም አገርነትን እውቅና የመስጠት እርምጃ በዌስት ባንክ በተደጋጋሚ ያየነው የመስፋፋት ውጤት፣ በዌስት ባንክ ሰፋሪዎች ሲፈጽሙ ያየነው ጥቃት፣በሁለት አገርነት መፍትሄ ላይ እንቅፋት እንደሚሆኑ ያየናቸው ለመገንባት ፍላጎት እና እርምጃዎችን ያየናቸው ለምሳሌ ኢ1 ሰፈራ ናቸው" ብለዋል።
የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማሃሙድ አባስ በዚህ ወር መጀመርያ ላይ ከሰር ኪር ጋር በተገናኙበት ወቅት ዩኬ እውቅና ለመስጠት የገባችውን ቃል አድንቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሁለቱ መሪዎች ሐማስ በወደፊቱ የፍልስጤም መንግሥት ውስጥ ምንም ሚና እንደማይኖረው መስማማታቸውን አስታውቋል።
የኮንዘርቫቲቭ መሪ የሆኑት ኪሚ ባዴኖች የሁለት አገራት መፍትሔ በመካከለኛው ምሥራቅ ተግባራዊ ሆኖ ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በዚህ ሳምንት መጨረሻ በዘ ቴሌግራፍ ላይ በጻፉት ጽሑፍ ላይ ደግሞ "አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ ነች፤ ይህም ግልጽ ነው፤ ታጋቾቹ ሳይለቀቁ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና መስጠት ለሽብርተኝነት ሽልማት እንደመስጠት ነው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሐማስ ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው ለሰር ኪር ስታርመር በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ የቀሩት 48 ታጋቾች ሳይመለሱ ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳይወስዱ ተማጽነዋል።
በደብዳቤው ላይ እውቅና መስጠትዎትን መግለጽዎ "የምንወዳቸውን ሰዎች ወደ ቤታቸው የመመለስ ጥረት የበለጠ ያወሳስበዋል" ብለዋል።
"ሐማስ የዩኬን ውሳኔ እንደ ድል ቆጥሮ እያከበረው፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ገሸሽ እያደረገው ነው።"
በመንግሥት ውስጥ ያሉ ምንጮች ሚኒስትሮች ሐማስ ላይ በቀጣይ ሳምንታት ማዕቀብ ለመጣል ይነጋገራሉ ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሳምንት ዩኬን በጎበኙበት ወቅት እውቅና በመስጠቱ እንደማይስማሙ ተናግረዋል።
ሰር ኪር ስታርመር ለእስራኤል "በጋዛ የምታካሄደውን አስከፊ ዘመቻ ለማቆም ተጨባጭ እርምጃዎችን እንድትወስድ፣የተኩስ አቁም ለማድረግ፣ እንዲሁም ለዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት እና በሁለት አገርነት መፍትሄ ላይ እንድትስማማ" እስከ የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ድረስ ቀነ ገደብ ሰጥተው የነበረ ሲሆን ይህም በዚህ ሳምንት ይጠናቀቃል።
ሐምሌ ወር ላይ ሰር ኪር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ዘላቂ እና ሉዓላዊ የፍልስጤም መንግሥት ጋር ደህንነቷ የተጠበቀ እስራኤል" የመመስረት ዓላማ "ከመቼውም ጊዜ በላይ ጫና ውስጥ ነው" ብለዋል።
"መፍትሄው አደጋ ላይ በመውደቁ አሁን እርምጃ የመውሰጃ ጊዜው ነው።"
ፖርቱጋል፣ፈረንሳይ፣ካናዳ እና አውስትራሊያ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና እንደሚሰጡ የተናገሩ ሲሆን ስፔን፣አየርላንድ እና ኖርዌይ ባለፈው ዓመት እውቅና ሰጥተዋል።
ፍልስጤም ከተባበሩት መንግሥታት 193 አባል አገራት ውስጥ 75 በመቶ ያህል እውቅና ቢሰጧትም፣ ዓለም አቀፍ ስምምነት የተደረሰበት ድንበር፣ ዋና ከተማ እና ጦር የላትም።
እውቅና መስጠት በስፋት እንደ ትዕምርት የሚታይ ነው።