ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ የአርሰናሉን ወጣት ሲያስፈርም፤ ስፔናዊው አማካይ ሚኬል ሜሪኖ ከመድፈኞቹ ጋር ተስማማ
ማንቸስተር ዩናይትድ የአርሰናሉን ወጣት አጥቂ ቺዶ ኦቢ ማርቲንን ለመውሰድ ያደረገው ጥረት በስኬት መጠናቀቁ ተዘገበ።
የዝውውር ዜና ዘጋቢው ፋብሪዚዮ ሮማኖ ባለፈው ዓመት የውድድር ዘመን ለአርሰናል ከ18 ዓመት በታች ቡድን በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረው ታዳጊ ዩናይትድ መግባቱ ተረጋግጧል ብሏል።
የዴንማርክ ዜግነት ያለው ቺዶ ኦቢ ማርቲን በዩናይትድ ቀዳሚ ቡድን ውስጥ ተሰላፊ እንደሚሆን ማረጋገጫ ከተሰጠው በኋላ ቀያይ ሰይጣኖቹን ስለመቀላቀሉ ተገልጿል።
ዴይሊ ሜይል በዘገባው በ17 ጨዋታዎች 29 ጎሎችን ያስቆጠረው ወጣት በአርሰናል ዋና ቡድን ውስጥ ቦታ እንዳለው ማረጋገጫ ሳያገኝ በመቅረቱ ዩናይትድን ተቀላቅሏል ብሏል።
አርሰናል ከስፔናዊው አማካይ ሚኬል ሜሪኖ ጋር መስማማቱን ስፖርት ዞን አስነብቧል።
የ28 ዓመቱ አማካይ ከመድፈኞቹ ጋር ለአራት ዓመት በሚዘልቀው ውል መስማማቱ የተገለጸ ሲሆን፤ የሰሜን ለንደኑ ክለብ በቀጣይ ከሪያል ሶሲዳድ ጋር ንግግር ያደርጋል ተብሏል።
የቼልሲው አምበል ጋላገር ከምዕራብ ለንደኑ ክለብ ጋር ሊለያይ ተቃርቧል። ዘ ሰን ጋዜጣ እንደዘገበው ቼልሲ እና አትሌቲኮ ማድሪድ የኮነር ጋላጋር ዝውውር ለመፈጸም ተቃርበዋል።
ጋዜጣው ጨምሮ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር በአውሮፓ ዋንጫ ተሳታፊ የነበረው ጋላጋር ከእረፍቱ በኋላ በቀጥታ ወደ አትሌቲኮ እንደሚያቀና ጨምሮ ዘግቧል።
ስሚዝ ሮው የፉልሃም ዝውውሩ የተጠናቀቀ ይመስላል። ስካይ ስፖርት የአርሰናሉ አማካይ ኤሚል ስሚዝ ሮው ፉልሃንም ከመቀላቀሉ በፊት የጤና ምርመራ ለማድረግ ለንደን እንደሚገኝ አስነብቧል።
ፉልሃም ለስሚዝ ሮው ዝውውር 34 ሚሊዮን ፓዎንድ በሚደርስ ከፍያ ከአርሰናል ጋር ባለፈው ሳምንት መስማማቱ ተዘግቧል።
ሌላኛው የአርሰናል አጥቂ ኤዲ ኒኪቲያህ የፈረንሳዩን ማርሴ ሊቀላቃል እንደሚችል በስፋት እየተዘገበ ነው ።
ዘ ሰን ደግሞ ዩናይትድ ብራዚላዊው የክንፍ መስመር ተጫዋች አንቶኒን ለመሸጥ ፍላጎት አለው ሲል ዘግቧል። ዩናይትድ 81 ሚሊዮን ፓዎንድ ከፍሎ ከአያክስ ያስመጣው አንቶኒ ለቡድኑ ኪሳራ ሆኗል ተብሏል።
እንደ ዘ ሰን ከሆነ ዩናይትድ የክንፍ ተጫዋቹ ዋጋ ላይ ታላቅ ቅናሽ አድርጎ መሸጥ ይፈልጋል።
ፋብሪዚዮ ሮማኖ እስማኢል ሳር ከኦሊምፒክ ማርሴ ወደ ለንደኑ ክርስታል ፓላስ ተዘዋውሯል ብሏል።
የሌስተሩ ካሌቺ ኢሂያናቾ ደግሞ የስፔኑን ሴቪያ ተቀላቅሏል።